ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሊያድኑት የነበረው ለገሰ ወጊ ማን ነበረ?

አቶ ለገሰ ወጊ

የፎቶው ባለመብት, Bilisuma Legese

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ከ11 ዓመት በፊት የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) የምዕራብ ዕዝ መሪ በነበረው ለገሰ ወጊ ላይ መንግሥት ሊፈጽም አቅዶት የነበረውን ጥቃት በተመለከተ ለግንባሩ አመራር መረጃ አቀብለው እንደነበር ከተሰማ ሰነባብቷል።

ኦነግም በወቅቱ ባወጣው መግለጫ የአሁኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ከጥቃቱ ቀደም ብለው በግንባሩ የጦር መሪ ላይ ሊፈጸም ስለታቀደው ጥቃት መረጃ በውጪ ለሚገኙት አመራሮች መስጠታቸውን አረጋግጧል።

ለገሰ ወጊ የተገደለው ከ10 ዓመት በፊት ሲሆን ግድያው እንዴት እንደተፈጸመ በጊዜው ዘጋቢ ፊልም ተዘጋጅቶ በመንግሥት መገናኛ ብዙኀን ተላልፎ እንደነበር ይታወሳል።

ለመሆኑ ለገሰ ወጊ ማን ነው? ስንል ቤተሰቡን ጠይቀናል።

የለገሰ ወጊ ውልደትና ድገት

በ1960 የተወለደው ለገሰ ወጊ፤ በአሁኑ ምዕራብ ሸዋ ዞን ሺኖ ወረዳ ኩዩ ጊጪ ቀበሌ ገበሬ ማህበር መወለዱን ባለቤታቱ ወ/ሮ ወይንሸትና ታላቅ ወንድሙ አቶ በቀለ ወጊ ይናገራሉ።

ለገሰ ወጊ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በተወለደበት አካባቢና ኢንጪኒ ውስጥ የተማረ ሲሆን 11ኛ ክፍልን ለመማር ደግሞ ወደ አዲስ አበባ መጣ።

ለገሰ የ11ኛ ክፍል ትምህርቱን በማቋረጥ በ1970ዎቹ ውስጥ በመካኒክነት ሙያ ሰልጥኖ ወደ ሥራ ተሰማርቶ ነበር።

ከመካኒክነት በተጨማሪ ወደ ድሬዳዋና ሌሎች ከተሞች በመንቀሳቀስ ጨርቃ ጨርቅና ሸቀጣ ሸቀጣ በማምጣት ይሸጥ እንደነበር ወ/ሮ ወይንሸት ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ወደ ትጥቅ ትግል እንዴት ገ?

የለገሰ ወጊ ባለቤት ወ/ሮ ወይንሸት ጌታሁን አሁን ከልጆቻቸው ጋር ኑሯቸውን በኖርዌይ አድርገዋል። ከለገሰ ጋር ከድሬዳዋ አዲስ አበባ እየተመላለሰ በሚነግድበት ወቅት ነበር ትዳር የመሰረቱት።

ወ/ሮ ወይንሸት ውልደታቸውም ሆነ እድገታቸው አዲስ አበባ፣ አዲስ ከተማ ነው። ከትዳር አጋራቸውም ሦስት ልጆችን ማፍራታቸውን ይናገራሉ።

ለገሰ ወጊ ለነጻነት የነበረው ከፍተኛ ስሜት በልጆቹ መጠሪያ ስም ላይ ይንጸባረቃል። የመጀመሪያ ልጁን በኦሮምኛ 'ቢሊሱማ' ብሎ ከሰየመ በኋላ ሦስተኛ ልጃን ደግሞ በአማርኛ 'ነጻነት' ሲል ተመሳሳይ ትርጉም ያለው ስም ሰጥቷል።

ለገሰና ባለቤቱ ትዳር ከመሰረቱ በኋላ ኑሯቸውን ያደረጉት እዚያው አዲስ ከተማ ነበር። ለገሰ የሚያስበውን ነገር መፈፀም የሚፈልግ ሰው እንደነበር ታላቅ ወንድሙም ሆኑ ባለቤታቱ ይናገራሉ።

ለገሰ ወጊ ሁለተኛ ልጁ [ፍሬህይወት] ተወልዳ ጡት ሳትጥል ሦስተኛ ልጁ ተረግዛ እያለ ነው ወደ ትግል ያቀናው።

ቤት ውስጥ አብረው ሳሉ በሀገሪቱ ውስጥ ስለሚካሄደው ጉዳይ በማንሳት ያወራ ነበር ሲሉ የሚያስታውሱት ወ/ሮ ወይንሸት፤ "አልፎ አልፎ ወደ ትግል መግባትም እንዳለበት ይነግረኝ ነበር" ብለዋል።

1982 ታህሳስ 23 ከቤት ወጣ። ያኔ ታዲያ ባለቤታቱ ወ/ሮ ወይንሸት ለገሰ ወደ ወለጋ ንግድ ጀምሮ ስለነበር ወደዚያው እንደሄደ ነበር የሚያውቁት። ከሳምንት በኋላ ለገና እመጣለሁ ስላለ ቤት ያፈራውን አዘገጃጅተው መጠበቃቸውንም ያስታውሳሉ።

ለገሰ ባሉት ቀን ብቅ ሳይል ቀረ። መጥፋቱም በሚያውቁት ሰዎችና በቤተሰቡ መካከል በስፋት ተወራ። ይጓዝበት የነበረው መኪና ተመትቷል የሚሉ ወሬዎች ይሰሙም ነበር። በወላጆቹና በባለቤቱ መካከል ጭንቀት ነገሰ።

እናትና አባቱ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ፎቶውን በመያዝ ወደ ወለጋ ለፍለጋ ሄዱ። ለሁለት ወር ያህል ፈለጉት፤ ሊያገኙት ግን አልቻሉም።

ወ/ሮ ወይንሸት ሦስተኛ ልጃቸውን ወልደው አራስ ቤት ሳሉ ለገሠ ለባለቤቱ በአንድ ወጣት በኩል የእጁን ሰዓትና ደብዳቤ ላከላት። ደብዳቤው ወደ ትግል መቀላቀሉን የሚገልጽ ነበር።

"ወደ ትግል ገብቻለሁ፤ ፈጣሪ ፈቃዱ ከሆነ በድል እንመለሳለን። በጸሎትሽ አስቢኝ" የሚለው ይህ ደብዳቤ ስለ ቤተሰብ ደህንነት ስለልጆቻቸውና ስለራሱ ካወራ በኋላ "የሚወለደው ልጅ ወንድም ሆነ ሴት 'ነጻነት' ብለሽ ሰይሚልኝ" የሚል ተማጽኖን ያዘለም እንደነበር ባለቤታቱ ወ/ሮ ወይንሸት ያስታውሳሉ።

ከዚያ በኋላ አልፎ አልፎ ደብዳቤ ይልክ ስልክም ይደውል ነበር የሚሉት ቤተሰቦቹ ለረዥም ጊዜ ድምጹ ጠፋባቸው፤ ቤተሰብም ተስፋ ቆረጠ።

የፎቶው ባለመብት, Social media

የምስሉ መግለጫ,

"የሚወለደው ልጅ ወንድም ሆነ ሴት 'ነጻነት' ብለሽ ሰይሚልኝ

ከ16 ዓመት በኋላ ስልክ...

ለገሰ ወጊ በትጥቅ ትግል ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች ውስጥ ማለፉን የድርጅቱ መረጃ ያሳያል። ከተራ አባልነት ተነስቶ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር የምዕራብ ዕዝ ጦር አመራር እስከ መሆን ደርሶ ነበር።

ደርግ ከስልጣን ሲወገድ ለገሰ ገና የኦነግ ካድሬ የነበረ ሲሆን ኦነግ ከሽግግር መንግሥቱ ከወጣ በኋላ በቀጥታ ወደ ትጥቅ ትግል መግባቱ ይነገራል።

በእነዚህ ዓመታት ውስጥ በምዕራብ ኦሮሚያ ከመንግሥት ወታደሮች ጋር ከሚካሄዱ ውጊያዎች ጋር ተያይዞ የለገሰ ስም በተደጋጋሚ ይነሳ ነበር።

ለወ/ሮ ወይንሸት አቶ ለገሰ አሉበት ከሚባለው አካባቢ መጣን የሚሉ ሰዎች ደህንነቱን እየነገሯቸው በደብዳቤም ሆነ በስልክ ሳይገናኙ ዓመታት አለፉ። በኋላ ግን ድንገት ስልክ ደወለ። ወ/ሮ ወይንሸት "ለገሰ አዲስ አበባ ከሚገኘው ቤቱ በወጣ በ16 ዓመቱ ስልክ ደወለ" ይላሉ። ቤተሰብም ተደሰተ።

ልጆቹ አድገዋል፣ ጡት የሚጠቡት ትምህርት ቤት ከገቡ ከርመዋል። የሚታዘሉት በእግራቸው መሄድ ከጀመሩ ቆይተዋል። ልጆቹ የአባታቸውን መልክ፣ ድምጽ እንዲሁም ጣዕም ፈጽሞ አያውቁም። የመጀመሪያ ልጁ ቢለሱማ "ትንሽ ትንሽ ብቻ አስታውሰው ነበር" ትላለች።

"ከዚያ በኋላ በሳምንትም በ15 ቀንም ይደውል ነበር" ይላሉ ወ/ሮ ወይንሸት።

በስልክ ስለቤተሰብ ስለልጆች ከማውራት ባሻገር ትግል ላይ መሆኑን ብቻ ይነግራቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ልጆች አባታቸውን ሲናፍቁ 'መቼ ነው የምትመጣው?' ብለው ሲጠይቁ የለገሰ መልስ ሁሌም ተመሳሳይ ነው፤ "እመጣለሁ ብሎ ሸንግሎን አያውቅም" ትላለች ቢሊሱማ።

ልጆች እንዲመጣ ይወተውታሉ፤ በስልክ ላይ ያለቅሱ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ለልጆቻቸው "የሕዝብ አደራ ተቀብሎ ስለወጣ መምጣት አንደማልችል ንገሪያቸው" ይል እንደነበር ያክላሉ።

ወ/ሮ ወይንሸት "ልጆቼን ባህላቸውን አስተምረው እንዲያሳድጓቸው ለኦሮሞ ሕዝብ አደራ ሰጥቻለሁ፤ ለፈጣሪ አደራ ሰጥቻለሁ" ይል እንደነበር ይናገራሉ።

አንድ ቀን አቶ ለገሰ ደወለ። ልጆች ስልኩን ከበው እናት ሲያዋሩ፣ ፍሬሕይወት ወረቀትና እስክቢርቶ ይዛ እንድትመጣ እንደነገሯት ቤተሰቡ ያስታውሳል። "ይህንን ቀን ወሩንና ዓመተ ምህረቱን ጽፋችሁ በሚገባ ያዙ፤ ታሪክ በጊዜው ራሱ ያወጣዋል" ብለው ቀንና ዓመተ ምህረት አጻፏቸው።

ፍሬሕይወት ቀኑንም ዓመተ ምህረቱንም በሚገባ ብትጽፍም ጊዜ ጊዜን እየወለደ ሲመጣ ቀኑም ተረሳ፤ የተጻፈውም ወረቀትም ጠፋ። እናም ዛሬ ድረስ ያቺ ቀን ምን የተፈጠረባት እንደሆነች ለማወቅ እንደጓጉ አሉ።

ይኼኔ ደግሞ ቢልሱማ ድንገት ተነስታ ሱዳን ገባች። ሱዳን እያለች ኤርትራ ያሉ የኦነግ አመራሮችን ስልክ አፈላልጋ በመደወል መልዕክት ትልክ ጀመር። በእነርሱ በኩል ያለችበትን ያወቀው ከአባቷ ጋር ከሱዳን ሊቢያ ከተሻገረችም በኋላ፣ ጣሊያን ገብታም ይደዋወሉ እንደነበር ታስታውሳለች።

ለገሰ ዘወትር ተእንደሚያደርገው ለቤተሰቦቹ አዲስ አበባ ስልክ ደውሎ ከትግሉ ስፍራ እንዲወጣ እንደተነገረው ወ/ሮ ወይንሸት ያስታውሳሉ።

ነገር ግን ትዕዛዙን ተቀብሎ ለመውጣት አሻፈረኝ እንዳለ ይነገራል። ለምን ሲባልም ከጠባቂዎቹ ጋር እየወጡ ሳለ በሰማይም በምድርም ጥይት እየዘነበባቸው በርካቶች መሰዋታቸውን እንደገለጸላቸው ያስታውሳሉ።

ከተረፉት ጠባቂዎቹ ጋር ወደ ምሽግ ከተመለሰ በኋላም "ፈጣሪ ነፍሴን ለመቼ እንዳቆያት አላውቅም" ማለቱን የሚናገሩት ወ/ሮ ወይንሸት ይህንን ያላቸው በሐምሌ ወር ውስጥ እንደሆነ ያስታውሳሉ።

ከዚህ በኋላም የስልክም ሆነ የደብዳቤ መልዕክት መቋረጡን ይናገራሉ።

ቢሉሱማ ግን አባቷ ከመገደሉ ከ15 ቀን ቀደም ብሎ ማውራታቸውን ትናገራለች። ያኔ ሁሌም ሐሙስ ሐሙስ እናወራ ነበር የምትለው ቢልሱማ ለምን እንደማይመጣ በጠየቀችው ቁጥር "እናንተን ለኦሮሞ ሕዝብ ሰጥቻለሁ፤ የሕዝብ አደራ ትቼ መምጣት አልችልም" ይሉ አንደነበር ታስታውሳለች።

የለገሰ ወጊ መገደል

ጥቅምት 26 2001 ዓ.ም ለሊቱን ተገድሎ ጥቅምት 27 2001 ዓ.ም ማታ ዜና ላይ መገደሉ ተናገረ። እርሳቸው ቤታቸው ውስጥ ብዙ ጊዜ ቴሌቪዥን ከፍተው እንደማያዩ የተናገሩት ወ/ሮ ወይንሸት ጎረቤት የሞቱን ዜና አረዳቸው።

ወዲያውም ቴሌቪዥን ሲከፍቱ የእለቱ ዜና አንባቢ የባለቤታቸው ምስል እየታየ የሞቱ ዜና ይናገራል። "ማልቀስም አልቻልንም" ይላሉ ወ/ሮ ወይንሸት።

ከዚህ በኋላ የነበረው ስሜት ከባድ አንደነበር፣ ሲያስታውሱት እንኳ የሚረብሻቸው መሆንን ያስረዳሉ። "በአጭር ቃል አልቅሶ እርም ማውጣት ከባድ ሆነ" ይላሉ።

በማህበራዊ ህይወትም ፈተና ውስጥ ወደቁ። አንገታቸውን ቀና አድርገው መሄድ ከበዳቸው።

በወቅቱ ስለለገሰ ወጊ መገደል በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተነገረውን መረጃ እውነትነት የኦነግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ሚካኤል ቦረን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በወቅቱ የመንግሥት መግለጫ ለገሰ በአካባቢው ገበሬ መገደሉን የተናገረ ቢሆንም፤ አቶ ሚካኤል ግን የተገደለው በመንግሥት ወታደሮች በተወሰደበት እርምጃ መሆኑንና "ገበሬው ከጎናችን ነበር" ሲሉ ያስተባብላሉ።

"ለገሰ በተለያዩ ጊዜ በተፈጸመበት ጥቃት ብቻውን ቀርቶ ነው ሰው ቤት የገባው" ይላሉ አቶ ሚካኤል ሁኔታውን ሲያስታውሱ።

አብረውት በተለያየ ጦርነት ላይ እንደተሳተፉ የሚናገሩት አቶ ሚካኤል፤ ለገሰ ጎበዝ ታጋይ እንደነበር ይመሰክራሉ። ተዋግቶ የሚያዋጋ ነበር በማለትም "እንኳን በሕዝብና በደጋፊዎቹ በጠላቶቹም በትልቅነቱ ይታወቃል" ብለዋል።

ወ/ሮ ወይንሸት ባለቤታቸው ሽፍታ እየተባለ፣ እንደ አጥፊ እየታየ ልጆቻቸውን ባሳደጉበት አዲስ ከተማ መኖር ከባድ ሆነባቸው። በዚህም ምክንያት በብዛት ቤተክርስቲያን ማሳለፍና ብቸኝነት አጠቃቸው።

ፖሊስ ቤታቸው ላይ ብርበራ አካሄደ። እርሳቸውንም ልጃቸውንም አቅራቢያ ፖሊስ ጣቢያ ወስዶ አሰራቸው። የቤታቸው ስልክ ተቋረጠ። ይኼኔ ልጆቻቸውን ሰብስበው ወደ ኬኒያ ተሰደዱ፤ ከዚያም ኖርዌይ ገቡ።

የለገሰ መልዕክተኞች

ለለገሰ መልዕክት የሚያደርሱላቸው ሁለት ሰዎች እንደነበሩ ልጃቸው ቢሉሱማና ባለቤታቸው ወ/ሮ ወይንሸት ያስታውሳሉ። በመጀመሪያ አንድ ወጣት ልጅ ነበር ይላሉ። በኋላ ላይ ግን እርሱ ዳግመኛ ቢመጣ እንኳ ምንም አይነት መልዕክት አትቀበሉት ብሎ በስልክ እንደነገራቸው ያስታውሳሉ።

ከዚያ በኋላ በእድሜ ከፍ ያሉ አዛውንት መልዕክት ያመጡላቸው ጀመር። ከደብዳቤ ጋር የለገሰን ፎቶ ሲያመጡ ከእነርሱ ደግሞ የናፍቆት ደብዳቤያቸውንና የቤተሰብ ፎቶ ይወሰስዱላቸው ነበር።

እኚህን ሰው አባ ፊጣ እያሉ ይጠሯቸው እንደነበር የምትናገረው ቢሊሱማ፤ ሁሌም ከአባታቸው የሚላከውን ምስል ካዩ በኋላ ለመደበቅ ወደ ቤተሰቦቻቸው ቤት ኢንጪኒ ይልኩት አንደነበር ታስታውሳለች።

ቢሉሱማ፤ አባ ፊጣ ወደ ቤታችን የሚመጡት ከመሸ ነው በማለት ለገሰ መልዕክት ከእርሳቸው ውጪ ከማንም እንዳይቀበሉ እንደነገራቸው፣ ቢጠየቁ ደግሞ ምንም እንደማያውቁ እንዲናገሩ እንዳሳሰባቸው ታስረዳለች።

"እንፈራ ነበር፤ ድንገት ቤታችን በፖሊስ ተበርብሮ ቢገኝብን ብለን እንሰጋ ነበር።"

በመጨረሻም አባ ፊጣ ላይም ክትትል መደረግ እንደተጀመረ ሰሙ። አባ ፊጣም "በቃ አታስቡ፤ ሰላም ነው፤ እኔ ዳግመኛ አልመጣም" ብለው ተለየአቸው።