የሰው ልጅ 'ትርፍ' ኩላሊቱን ቢሸጥ ምን ችግር አለው?

የሰው ልጅ የሰውነት አካልን የያዘ ከረጢት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ባተሌው ኩላሊታችን አልሠራም ብሎ የለገመ ለታ ሕይወት መጨለም ትጀምራለች። ሥርዓት ይዛባል። አስፈሪ የጤና እክል ነው የሚከተለው።

መልካሙ ነገር የሕክምና ሳይንስ በየጊዜው አዳዲስ አማራጮችን ይዞ መምጣቱ ነው።

አንድ ከሕክምና ሳይንስ ያልወጡ ኢኮኖሚስት በኩላሊት ጉዳይ ገናና ናቸው። ኧረ እንዲያውም ኖቤልን ወስደዋል።

ፕሮፌሰር አልቪን ሮት ይባላሉ።

በተቀረው ዓለም በርካታ ሰዎች የኩላሊት ንቅለ ተከላ ቢያስፈልጋቸው ከዘመድ ወዳጅ ውጭም ቢሆን ኩላሊት የማግኘት ዕድላቸውን ያሰፉት እኚህ ኢኮኖሚስት ናቸው።

የኩላሊትን ቅብብሎሽን ለማሳለጥ ያስችላል ብለው የወጠኑት ንድፈ ሐሳብ ላይ ላዩን ሲታይ ቀላል ይመስላል። ነገር ግን በውጤቱ ሲለካ የመቶ ሺዎችን ሕይወት የታደገ ነው።

ኢኮኖሚስቱ ፕሮፌሰር አልቪን ይህንን ጽንሰ ሐሳብ ይዘው ባይመጡ ኖሮ ይህን ጊዜ ብዙ ሺህ የኩላሊት ሕሙማን ወይ ኩላሊት እጥበት ላይ ነበሩ አልያም ደግሞ ሞተዋል።

ነገሩ እንዲህ ነው፤

ኩላሊትን መለገስ ሌላ የሰውነት አካልን ከመለገስ ፈጽሞ የሚለይበት ሁኔታ አለ። አንዱ ልዩ የሚያደርገው የሰው ልጅ በአንድ ኩላሊት በጤና መኖር መቻሉ ነው።

እርስዎ ለሚወዱት ሰው ኩላሊት መለገስ ፈለጉ እንበል። እንዳው ታማሚው ከለጋሹ ጋር የቤተሰብ አባል ስለሆነ ብቻ ኩላሊቱ ሄዶ ይገጥማል ማለት አይደለም።

ስለዚህ የእርስዎ መልካም መሆን ብቻ ወዳጅዎን ከሞት አይታደገውም ማለት ነው።

ኢኮኖሚስቱ ፕሮፌሰር አልቪን ግን ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ መላ መቱ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

እንበልና ሁለት ቤተሰቦች ኩላሊት ለመለገስ መጥተው ሁለቱም ኩላሊታቸው ለሚለግሱት የእኔ ለሚሉት ሰው ሳይገጥም ሲቀር እንዲቀያየሩ ይደረጋል። ስለዚህ ለጋሾች በሙሉ እንዲሰባሰቡ ይደረጉና አልገጥም ያለው ለሌላ ለማያውቀው የቤተሰብ አባል እንዲለግስ ይደረጋል።

በዚህ ዘለግ ያለ የልውውጥ ሰንሰለት ሁሉም ቤተሰብ፣ ሁሉም ለጋሽ፣ ሁሉም ተቀባይ ደስተኛ ሆነው ይሄዳሉ ማለት ነው።

በቅርቡ ለምሳሌ በአሜሪካ 70 ለጋሾች በዚህ የልግስና ሰንሰለት በመጠቀም ቤተሰቦቻቸውን ታድገው ሄደዋል።

ኩላሊትን መሸጥ በመላው ዓለም ወንጀል ነው። ምናልባት ወንጀል ያልሆነው በኢራን ብቻ ነው። ሕገ ወጥ የሆነበት አንዱ ምክንያት ደግሞ ክቡሩን የሰው ልጅ ባለጸጎች ነፍስ ያለው ሸቀጥ እንዳያደርጉትም ጭምር ነው።

ነገሩ ሕጋዊ መልክ አንዲይዝ ቢደረግ ገንዘብ ያላቸው አገራት ገንዘብ ከሌላቸው አገራት ከሚያስመጧቸው ጥሬ እቃዎች ጋር ክቡሩን የሰው ሆድ እቃና የሰውነት አካልም ይጨምሩበት ነበር። ከዚህ ውስጥ አንዱ የሚሆነው ደግሞ ኩላሊት ነው።

"እርግጥ ነው ኩላሊት የገንዘብ ተመን እንዲወጣለት አንፈልግም" ይላሉ ፕሮፌሰር አልቪን። ቢቢሲ ፕሮፌሰሩን የእርሳቸው ጽንሰ ሐሳብ ያመጣውን ዕድል እንዲያብራሩለት በጠየቃቸው ጊዜ ያስረዱት፤ በአሜሪካ ብቻ በዚሁ ዘዴ በየዓመቱ አንድ ሺህ ተጨማሪ ኩላለሊት ለጋሾች መገኘታቸውን በመጥቀስ ነው።

ይህ ውጤታማ ሐሳብ ነው ፕሮፌሰሩን በ2012 በኢኮኖሚክስ የኖቤል ተሸላሚ ያደረጋቸው።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

አሜሪካ ውስጥ የኩላሊት እጥበት እጅግ ውድ ዋጋን ከማስወጣቱ ጋር ተያይዞ በድሀ አገር ለሚገኙ ለጋሾች ገንዘቡ ቢሰጥ አይሻልም? የሚል ክርክር ይነሳል።

ኩላሊት ልውውጥን የማትፈቅደው ጀርመን

የቢቢሲ ዘጋቢ እኚህን የኖቤል ሎሬት በጀርመን አግኝቷቸው ነበር፤ ለዚሁ ጉዳይ በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ለመታደም ነበር የተገኙት።

ጀርመን ከበለጸጉ አገሮች መሀል የኩላሊት ልውውጥን ሕገ ወጥ ያደረገች ብቸኛ አገር ናት።

"አንዳንድ ውሳኔዎቻችንን፣ አንዳንድ አካሄዶቻችንን ከጊዜው ጋር እንዲራመዱ ማድረግ ይኖርብናል" ይላሉ የጀርመንን ውሳኔ የሚቃወሙት የኖቤል ሎሬት፤ ጀርመን ውሳኔዋን እንድታጤነው ነው የሚያሳስቡት።

የጀርመን የጤና ሚኒስትር በበኩላቸው ለቢቢሲ እንደተናገሩት በጉዳዩ ዙርያ ሕዝባዊ ውይይቶችንና ክርክሮችን የማሰናዳት ሐሳብ አለ። ነገሩ ዝግ አይደለም። ሕዝበ ውሳኔ ይፈልግ ይሆናል። ብቻ ሕዝቡ ሊከራከርበት ይገባል ይላሉ።

የኖቤል ሎሬቱ ፕሮፌሰር ጀርመን በነገሩ ላይ የያዘቸው አቋም ከምን እንደመነጨ ይረዳሉ።

"የሰውነት አካል ኮንትሮባንድ(ህገወጥ ሽያጭ) እንዳይጀመር ለመከላከል የወሰደችው ጥብቅ አቋም እንደሆነ እረዳለሁ።..."

"ጀመርኖቹ እንዴት መሰለህ ያሰቡት፤ እኔ ኩላሊቴን ልሰጥህ ስመጣ አንተ ባለጸጋ፣ እኔ ደግሞ ደሀ ሆኜ አማራጭ በማጣት ያደረኩት ሊሆን ይችላል በሚል ነው። እኔ ግን ወንድምህ ከሆንኩ ከልቤ ፈቅጄ ያደረኩት ነገር አድርገው ስለሚያስቡት ፍቃደኛ ይሆናሉ።"

ፕሮፌሰሩ ይህ ሁኔታ መለወጥ እንዳለበትም ያምናሉ፤ "እንዴት መዳን የሚችል ሰው በቢሮክራሲ ጥልፍልፍ ምክንያት ሕይወቱን ያጣል?"

የፎቶው ባለመብት, NOBEL

የምስሉ መግለጫ,

ኢኮኖሚስቱ ፕሮፌሰር ኤልቪን ሮት በፈረንጆቹ 2012 ኖቤል ሽልማት ላይ

የኩላሊት ገበያ

ፕሮፌሰር አልቪን ሮት የኩላሊት ግብይት በጊዜ ሂደት መልክ ይዞ መጀመሩ እንደማይቀር ይተነብያሉ። ኩላሊት ለጋሾች ተገቢውን ክፍያ እንዲያገኙ የሚደረግበት መንገድ መከፈቱ አይቀሬ ነው ሲሉ ይሞግታሉ።

ነገሩ አከራካሪ ነው። እርሳቸውም ይህን አላጡትም። እንዲያውም እርሳቸው የነገሩንን አከራካሪነት ሲያነሱ ልክ አሜሪካ በቬትናም ጦርነት ጊዜ በግዴታ ስለመዝመትና በፈቃደኝነት ስለመዝመት የነበረውን የጦፈ ክርክርን ነው የሚያስታውሳቸው።

ፕሮፌሰሩ መጪውን ዘመን ሲያስቡ አንድ ኩላሊቱን በገንዘብ የሚሸጥ ዜጋ እንደ 'ጀግና' የሚቆጠርበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም ብለው ያስባሉ።

መንግሥትም ከነዚህ 'ጀግኖች' የሰበሰበውን ኩላሊት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ የሚያድልበት ዘመን ይመጣል ብለውም ያምናሉ።

በዚህ መንገድ ኩላሊት ከድሆች ለሀብታም የሚሸጥ ሳይሆን ልክ ሌላ የሰውነት አካል በመንግሥት የጤና ሥርዓት ለዜጎች በሚለገስበት መንገድ፤ ኩላሊትም ከፍቃደኞች ተገዝቶ ሥርዓቱን ጠብቆ የሚለገስ አንድ የሰውነት አካል እንጂ ሌላ አይሆንም ይላሉ።

ፕሮፌሰር ይህን ይበሉ እንጂ ለኩላሊት የዋጋ ተመን ማውጣት በሕክምና ውስጥ ላሉትም ሆነ ከዚያ ውጪ ለሆኑት የሚዋጥ ሐሳብ አይደለም።

በአንድ ወቅት በሙከራ ደረጃ ሊተገበር የነበረ ሂደት ነበር። ይኸውም በተለያዩ ዓለማት የሚኖሩ ኩላሊት ተቀባዮች ከኩላሊት ለጋሾች ጋር እንዲጣመሩ እተደረገ የተቀባዮችን ዕድል ማስፋት ነው።

ይህም በኩላሊት የልውውጥ ሰንሰለት በርካታ ሰዎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ነበር ሐሳቡ።

በውጤቱም ከፍተኛ ገቢ ያላቸው አገሮች ዝቅተኛና መካከለኛ ገቢ ካላቸው አገሮች የሚመጡ ኩላሊት ለጋሾችን ወጪያቸውን ይሸፍናል።በዚያውም ሐብታሞቹ ምርጫቸው ይሰፋል፣ ድሆቹም ወጪያቸውም ምርጫቸውም ይሰፋል።

ይህ ሐብታሞች ድሆችን የሚያድኑበት [ኢላማ የሚያደርጉበት] የልውውጥ ሰንሰለት ለአጭር ጊዜ ከተሞከረ በኋላ የዓለም የጤና ድርጅት ውድቅ አድርጎታል።

ፕሮፌሰር አልቪን ግን "ይህ ውድቅ መደረግ ያልነበረበት ጥሩ ሐሳብ ነበር ይላሉ።" የእርሳቸው ነጥብ የሚሽከረከረው በአንድ ኩላሊት መኖር እየተቻለ ሁለት ኩላሊት ይዞ መቆየትን ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው። የእርሳቸው ነጥብ ለጋሾች እያሉ ተቀባዮች መሞታቸው ላይ ነው።

"አሁንም ማፈር ያለብን እኛ በፈጠርነው የቢሮክራሲ ጥልፍልፍ ምክንያት መኖር የሚችሉ ሰዎች እየሞቱ በመሆኑ ነው።"