ካጋሜ ሴት እንድትተካኝ እፈልጋለሁ አሉ

ፖል ካጋሜ ንግግር ሲያደርጉ

የፎቶው ባለመብት, RBA

የሩዋንዳው ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ ሴት መሪ እንድትተካቸው እንደሚፈልጉ ተናገሩ።

በሩዋንዳ፣ ኪጋሊ ዛሬ የተጀመረው ብሔራዊ የውይይት መድረክ ላይ አገራቸው ሴቶችን ወደ አመራር በማምጣት ስኬታማ መሆኗንም ገልጸዋል። ሩዋንዳ በዘርፉ በዓለም አቀፍ መድረክ የሚያስከብራት ደረጃ ላይ እንደምትገኝም አክለዋል።

"ከመቶ በላይ አገሮች ውስጥ በተሠራ ዳሰሳ መሰረት ከመጀመሪያዎቹ አስር አገራት ዝርዝር ውስጥ ገብተናል። የመጀመሪያዎቹ አምስቶች ዝርዝር ውስጥ ለመግባት መሥራት እንደሚጠበቅብን ለማስታወስ እወዳለሁ" ብለዋል።

የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም፤ ዛሬ የጾታ ተዋጽኦ ክፍተትን በተመለከተ ባወጣው ሪፖርት፤ ሩዋንዳ ከ153 አገራት በዘጠነኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች። የመን በዝርዝሩ የመጨረሻው ደረጃ ተሰጥቷታል።

አገሪቱ ሴቶችን ማብቃት ላይ ለዓመታት ያፈሰሰችው ኃይል ውጤታማ በመሆኑ እንደተደሰቱም ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል። ሴቶች በንግድ፣ በጸጥታ ጥበቃና በፍትሕ ሥርዓቱ ያላቸው ተሳትፎ እንዲጨምር እንደሚፈልጉም አክለዋል።

2,000 ሰዎች በታደሙት ውይይት ላይ፤ "ሁሉም ቦታ እንድትኖሩ እፈልጋለሁ። የሰጣችሁኝን የአመራር ቦታ የምትረከበው ሴት እንድትሆን እመኛለሁ። ንግግሬን የሚያዳምጡ አዳራሹ ውስጥ ያሉ ወንዶች እንደማይቀየሙኝ ተስፋ አደርጋለሁ፤ ለነገሩ የነሱም ምኞት እንደኔ አይነት ሊሆን ይችላል" ሲሉ ተደምጠዋል።

የሩዋንዳ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 52 በመቶ የሴቶች ውክልና በመያዝ ግንባር ቀደም ሲሆን፤ ከ26 የካቢኔ መቀመጫ 14ቱ በሴቶች የተያዘ ነው። ሆኖም በፍትሕ እና በንግዱ ዘርፍ አሁንም የወንዶች የበላይነት ይስተዋላል።