የጃንሆይ ቮልስዋገን ዛሬ በቦሌ ትታያለች

አባትና ልጅ በቮልስ

የፎቶው ባለመብት, Volkswagen Ethiopia

የምስሉ መግለጫ,

አቶ ሀብታሙ ኤርሚያስ አባታቸው ቮልስ ነበራቸው። እርሳቸውም ከጉርምሳና ዕድሜያቸው ጀምሮ ቮልስ ነድተዋል። ወንድማቸውም ቮልስ ነው የሚነዳው። ማን ያውቃል? በፎቶ የሚታየው ልጃቸውም ቮልስ ይነዳ ይሆናል።

ዛሬ በቦሌ ጎዳና ቮልስዋገኖች ተግተልትለው ያልፋሉ፤ ከነሙሉ ክብርና ሞገሳቸው፡፡ በቁጥር 160 ይሆናሉ፡፡ ከነዚህ መካከል ቢያንስ አንዷ ታሪካዊ ናት፡፡ የጃንሆይ ቮልስ!

ለ46 ዓመታት ኢትዮጵያን ‹‹የሾፈሯት›› ጃንሆይ በመለዮ ለባሾቹ ከዙፋናቸው ሲገረሰሱ ከሞቀው ቤተ መንግሥት ‹‹ተሾፍረው›› የወጡት በዚች ቮልስዋገን ነበር፡፡

ያን ጊዜ ሾፌራቸው የነበሩት ጄኔራል ሉሉ እንግሪዳ ይባላሉ፡፡ እርሳቸው በሕይወት የሉም ዛሬ፡፡ ባለቤታቸው እማማ አጸደ ግን ቮልስዋገኗን ወርሰዋታል፡፡

ይቺ ቮልስ የታሪክ ድር እያደራች ዛሬም በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ሽር ትላለች፡፡ ምናልባት በመኪና ቋንቋ ‹‹ቀሪን ገረመው›› እያለችን ይሆን?

የፎቶው ባለመብት, Volkswagen Ethiopia, Micheal Getachew

የአዶልፍ ሂትለር ደ መኪና

እንደ ጎርጎሮሲያዊያኑ በ1930ዎቹ መጨረሻ አዶልፍ ሂትለር ቀጭን ትእዛዝ ሰጠ። የእርሱ ትእዛዝ ይፈጸማል እንጂ ወለም ዘለም የለም።

ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ የሚሸጥ፣ ማንም የአርያን ዘር ነኝ የሚል ኩሩ ጀርመናዊ ባልተጋነነ ዋጋ ሊገዛው የሚችል የደስተኛ ቤተሰብ መኪናን የሚወክል የተሽከርካሪ ፋብሪካ እንዲቆቋም አዘዘ፡፡

ይህን ቀጭን ትእዛዝ ተከትሎ አንድ በወቅቱ ግዙፍ ሊባል የሚችል የመኪና ማምረቻ ተቋቋመ።

ሆኖም ምርቱ በገፍ ከመጧጧፉ በፊት የ2ኛው የዓለም ጦርነት ተጀመረና ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር ተባለ። ቮልስ ሊያመርት የተባለው ፋብሪካም የጦር መሣሪያ ማምረት ያዘ።

የማያልፉት የለም ጦርነቱ ሂትለርን ይዞ አለፈ። የዓለም ጦርነቱ ሲያባራ በዓለም ዝነኛ ለመሆን እጣ ፈንታዋ የሆነች አንዲት መኪና ተመረተች፡፡

ለመኪናዋ ስያሜ ለመስጠት ብዙም ያልተቸገሩ የሚመስሉት አምራቾቿ ስሟን ቮልስዋገን አሏት። 'የሕዝብ መኪና' እንደማለት፡፡

ጢንዚዛ የመሰለችው ቮልስ መኪና ተወለደች። በምድር ላይ እንደርሷ በተወዳጅነት ስኬታማ ሆኖ የቆየ የመኪና ዘር የለም።

የአውቶሞቲቭ ተንታኞች ቮልስ ቢትልን ልዩ የሚያደርጋት በሀብታምና ሀብታም ባልሆነ ሕዝብ በእኩል መወደዷ ነው ይላሉ።

ምርቷ ሙሉ በሙሉ እስኪቆም ድረስ በጀርመን፣ በብራዚልና በሜክሲኮ 21 ሚሊዮን 529ሺህ፣ 464 ያህል ተመርተዋል። ስንት ሺዎቹ ወደኛ አገር እንደመጡ ግን በውል አይታወቅም።

"ቮልስዋገን ኢትዮጵያ" ማኅበር በሕግ ሲመሠረት አንዱ ሥራው የቆሙና በሕይወት ያሉ ቮልሶችን በትክክል መቁጠርና አባላትን መመዝገብ ይሆናል።

ይቺ ፈጣሪዎቿ "የሕዝብ" ያሏት የብዙኃን መኪና እኛ ዘንድ መጣችና የጥቂቶች ብቻ ሆነቸ፡፡ ቮልስ በአዲስ አበባ ጎዳና ገናና በነበረችበት ዘመን ቮልስና ዴክስ የነዳ የየሰፈሩ ፈርጥ ነበር። "ደህና ዋሉ ጋሼ" ተብሎ ቆብ ከፍ የሚደረግለት።

መኪና እንደ ቆሎ ከውጭ አገር በሚዘገንበት በዚህ ዘመንም ቢሆን ቮልስ ዐይነ ግቡ ናት። ምንም እንኳ አንዳንዶች ሊሳለቁባት ቢሞክሩም።

የፎቶው ባለመብት, BBC Amharic

የምስሉ መግለጫ,

ጃንሆይ ከቤተ መንግሥት በመለዯ ለባሾች የተሸኙባት ቮልዋገን

አቶ ሀብታሙ ኤርሚያስ ለምሳሌ ለ16 ዓመት ባሽከረከሯት ቮልስ ያልተባሉት ነገር የለም። በቀደም ለታ ለምሳሌ መገናኛ ጋር አንድ ዘናጭ ዘመነኛ መኪና የሚያሽከረክር ሰው መስኮት አውርዶ "አንተ ሰውዬ! ምናለ ይቺን ሸጠህ ደህና ጫማ ብትገዛ?" ብሏቸዋል። እርሳቸው ግን ውድድ ነው የሚያደርጓት።

አቶ ሀብታሙ ሰፈራቸው አንቆርጫ ነው። በርሳቸው ቮልስ ምክንያት የሰፈራቸው ታክሲ መዳረሻ "ቮልስ ግቢ" ተብሎ ነው ዛሬም ድረስ የሚጠራው። ታክሲ የሚጭነው። ኮተቤ ብረታ ብረት 02 ጋ ታክሲ ሲጭን "የቮልስ ግቢ" እያለ ነው።

የአቶ ሀብታሙ ሕጻን ልጆች ቮልሳቸውን "ቮልስ" ብለው አይደለም የሚጠሯት። ውቤ እያሉ ነው የሚያቆላምጧት። አቶ ሀብታሙ በአንድ የቻይና የነዳጅ አውጪ ኩባንያው ውስጥ ነው የሚሰሩት። ቻይኖቹ ራሱ ቮልሷን "ውቤ" ነው የሚሏት።

ታዲያ ለአቶ ሀብታሙ ቮልስ የኩራታቸው ምንጭ ብትሆን እንዴት ይገርማል?

የፎቶው ባለመብት, Volkswagen Ethiopia, Micheal Getachew

ጥሎባቸው አንዳንድ ነገሮች እንደ ዋይን ናቸው። እያረጁ ይጣፍጣሉ፡፡ ቮልስም እንዲያ ናት፡፡

ፈጣሪዋ አቶ ፈርዲናንድ ፖርሻ ቮልስን ሲነድፋት በጢንዚዛ ቅርጽ መሥሎ ነው፡፡ እነሆ ከዚያ ዘመን ጀምሮ ሁሌም ዝንጥ እንዳለች አለች፡፡ ደክርታም ዘናጭ ናት፡፡ ዕድሜ ተጭኗትም አፍላ ኮረዳ ነው የምትመስል፡፡

ለዚህም ይመስላል የቮልስ ወዳጆች እልፍ የሆኑት፡፡ እንዲያውም በብዙ አገራት ማኅበር አላቸው፡፡ የቀልድ ሳይሆን ሕጋዊ ማኅበር፡፡ ‹‹የቢትልስ ወዳጆች ማኅበር›› ይባላሉ፡፡ እኛም አገር ይህ እውን ሊሆን ተቃርቧል፡፡

ነገ የሚከፈተውን የቮልሶች አውደ ርዕይን ከሚያስተባብሩት አንዱ የሆነው ወጣት ሚካኤል ጌታቸው ነው እንዲያ የነገረን፡፡ ኸረ እንዲያውም አባላቱ ቮልሶቻቸውን እየነዱ ሱዳን ለመሄድ ሁሉ ያስባሉ፡፡

የቢትልስ ወዳጆች ማኅበር እዚያም አለ፤ ኻርቱም፡፡ በመላው ዓለም የቢትልስ ወዳጆች እንደቤተሰብ ነው የሚተያዩት፡፡ ኻርቱምና አዲሳባም እንዲሁ፡፡ ‹‹ወይ እነሱ ይመጣሉ፤ ወይ እኛ እንሄዳለን›› ይላል ሚካኤል፡፡

የሆነስ ሆነና፣ በቮልስ ካርቱም ድረስ ይኬዳል እንዴ? ቮልስ እንኳን የኡምዱርማንን በረሃ ልታቋርጥ ይቅርና መቼ የቸርችልን አቀበት ለመውጣት ወገቧ ጠና?

ሚካኤል ጌታቸው ሳቀብኝ፡፡ ቮልስዋገኖች እጅግ ፈጣን መኪኖች ናቸው ሲልም ሞገተኝ፡፡ ችግራቸው በሾፌሩ በኩል ያለ ባትሪ ነው፡፡ እሱ ከተጠገነ "ከቪ8 እኩል ይሮጣሉ" ይላል፡፡

"ጓደኞቼ ለቮልሶቻቸው የውድድር መኪና ሞተር ገጥመውላቸው እንዴት ክንፍ አውጥተው እንደሚበሩ ብታይ…!"

አልተዋጠልኝም፡፡

እንደኔ ሰፈራችን በነበሩ የቮልስ ባለቤት ሰውዬ የ'ግፉልኝ' ጥያቄ የተማረሩ አንባቢዎችም ሚካኤልን አያምኑትም። እሱም ይህን አላጣውም። ተጨማሪ ማስረጃ አቀረበው።

"ከ6 ወር በፊት ድንበር ሲከፈት አንድ ኤርትራዊ ሙሉ ቤተሰቡን ይዞ ከአስመራ አዲስ አበባ በቮልስ ዋገን እየነዳ ገብቷል "ሲል አስረዳኝ፡፡ ቤተሰቡ ሶደሬና ሐዋሳ ሽር ብትን ብሎ መመለሱን በፎቶ አስደገፈልን፡፡ ይሄ ማለት 1078 ኪሎ ሜትር ደርሶ መልስ ማለት ነው።

በ'ነርሱ የፌስቡክ ገጽ ያገኘነው መረጃ መሠረት ይህን ጉዞ ያደረጉት ሰው አቶ ኒኮዲሞስ ናቱ ይባላሉ። በአውሮጳ አቆጣጠር በ1996 ቮልስ ይዘው መጥተው ነበር፣ ወደ አዲስ አበባ። 2ኛው ጉዟቸው ከ25 ዓመት በኋላ የተደረገ ነው። የቮልሳቸው እድሜ ደግሞ 42 ዓመት አልፎታል።

የቮልስ ኢትዮጵያ አስተባባሪው አቶ ሚካኤል ጌታቸው እንደሚለው ቮልስ የጤና ክትትል ከተደረገላትና በሾፌር በኩል ያለው ባትሪዋ ከተቀየረላት ዕድሜዋ የማቱሳላ ነው፡፡

የፎቶው ባለመብት, Heritage Images

የምስሉ መግለጫ,

ቮልስዋገን ባለቤቶች መኪናዬ "ትኩሳቷ ተነሳባት" ሲሉ ቢሰሙም ሚካኤል በዚህ አይስማማም

የቮልስ ወዳጆች እንዴት ተገናኙ?

ዛሬ የሚገናኙት የቮልስ ባለቤቶች ብቻ አይደሉም። የቮልስ ጋራዥ ባለቤቶች፣ የቮልስ አካል መለዋወጫ ነጋዴዎች፣ የቮልስ ኤልትሪሻኖች ሁሉ አሉበት።

ለመሆኑ የቮልስዋገን ባለቤቶች እንዴት ይሆን የተገናኙት? እንዴት ተጠራሩ?

ምናልባት "ግፋልኝ እባክህ" ሲባባሉ በዚያው ተቀራርበው ይሆን? ምናልባት ቀይ የትራፊክ መብራት የቮልሳቸውን የልብ ትርታ ቀጥ ባደረገበት ቅጽበት "እኔን" ሲባባሉ በዚያው ተወዳጅተው ይሆን?

ነገሩ ሚካኤል ጌታቸውን ፈገግ አሰኝቶታል፡፡ የቮልስዋገኖችን ስም ለማጥፋት በቪትሶች የሚሰራጭ አሉባልታ አድርጎ ሁሉ ሳይወስደው አልቀረም፡፡

በነገራችሁ ላይ ቮልስዋገን አፍቃሪዎች ራሳቸውን ልክ እንደ አንድ "የፋሽን ጎሳ" መሰለኝ የሚመለከቱት፡፡ የእርስ በርስ ቅርርባቸው የሚያስቀናም የሚያስደንቅም ነው፡፡

አንድ ቮልስ ነጂ መንገድ ዳር እክል ገጥሞት ቢቆም ከማንም በፊት የሚደርሱለት ሌላ ቮልሳዊ ወንድሞቹ ናቸው፡፡ 'ስኮርት' ያቀብሉታል፣ 'ክሪክ' ያውሱታል፡፡

ይሄ የበዛ መቀራረብ ከምን የመነጨ ይሆን? ሲባል አቶ ሚካኤል ያው ቮልስዋገን ‹‹የሕዝብ መኪና›› ማለትም አይደል?›› ይላል፡፡ እንደ አንድ ሕዝብ እንቀራረባለን ማለቱ መሰለኝ፡፡ ይህን 'ቮልስወገናዊ' ፍቅር ብንለውስ።

የፎቶው ባለመብት, Mirrorpix

'ቮልስወገናዊ' ፍቅር

ቮልስ ፍቅር ያጎበጣት መኪና ትመስላለች። አንዳች አዚም አላት፤ የመወደድ፡፡ ሰዎች አንድ ጊዜ ቮልስ ከነዱ ገንዘብ ስላገኙ ብቻ ቮልሳቸውን አሳልፈው አይሰጡም፡፡

ከቤተሰብ ተማክረው፣ ወዳጅ ዘመድ ተሰብስቦ፣ ቤተሰብ ጉባኤ ተጠርቶ ...። እንጂ እንዳገለገለ ባልዲ በቀላሉ አይጥሏትም። የወለዱትን የመጣል ያህል የሚሆንባቸው ሁሉ አሉ።

ብዙዎች ቮልስን በቀላሉ ከልባቸው ማውጣት የማይሆንላቸው ግን ለምን ይሆን?

ቮልስ ብዙውን ጊዜ የቤተሰብ አባል ሆና ቁጭ ትላለች።

ሚካኤል ለዚህ የሚሰጠን ምሳሌ አንድ በቅርብ የተቀላቀላቸውን ወጣት ታሪክ በመግለጽ ነው፡፡

"ባለፈው የተዋወቅነው ወንድማችን" ይላል ሚካኤል "አባቱ የዛሬ 50 ዓመት የገዟትን ቮልስ ነው ይዞ የመጣው፡፡ ሴፌሪያን የሚባል ቮልስ መሸጫ ነበር ድሮ ሜክሲኮ ጋ፡፡ 00 (ጭራሽ ያልተነዱ) ቮልሶችን የሚሸጥ ኩባንያ ነበር። ከዚያ የተገዛችው መኪና ከትውልድ ስትተላለፍ ቆይታ እርሱ እጅ ገብታ እንዴት እንደምታምር…"

ቢቢሲ፡-የቤተሰብ አባል ነበረች በለኛ!

‹‹አዎና! ቮልሶች 'ሴንትመንታል ቫሊይዋቸው' ከፍተኛ ነው፡፡ እንዲያውም እኮ አንዳንድ ቤት ግቢ ውስጥ ቆመው ታያቸዋለህ፡፡ ዝገት እንዳይነካቸው ከፍ የሚያደርግ ድንጋይ ተነጥፎላቸው፤ በየቀኑ እየታጠቡ ግቢ ውስጥ ለዘመናት ቆመው ያሉ አሉ፡፡ የማይነዱ፡፡››

ደግሞ የድሮ ታርጋ ያላቸው አሉ፡፡ ሚካኤል እንዲያውም ወደ ፒያሳ ጳውሎስ በብዛት የምትነዳ ታርጋ ቁጥሯ የአማራ ክልል የሆነ 00001 መኪና እንዳለች አስተውሏል፡፡

"በዚያ ላይ ከርቫቸው ያምራል፤ በተለምዶ ደማቅ ቀለም ነው የሚቀቡት ከኋላ ብታያቸው ከፊት በሁሉም ጎናቸው ቆንጆ ናቸው፡፡" ይላል።

ነገ ለተጋባዦች ብቻ ክፍት በሚደረገውና ኮላብ ሲስተምስ ፒኤልሲ ጋር በመቀናጀት በተሰናዳው በዚህ የቢትልስ ቮልስ የእንትዋወቅ መርሐግብር በሺ የሚቆጠሩ ታዳሚዎች ይጠበቃሉ።

ከታዳሚዎቹ መካከል ታዲያ በእድሜ ገፋ ያሉና ቮልስን ለሩብ ክፍለ ዘመን ያሽከረከሩ ይገኙበታል።

የፎቶው ባለመብት, Heritage Images

የበዓሉ ግርማ ቮልስ

በአገራችን እንደ ቮልስ በታዋቂ ሰዎች የተዘወረ መኪና ይኖር ይሆን? በዚህ ዘመን እንኳ ኮሜዲያን ደረጀ ኃይሌ ብቻ ቀርቷል መሰለኝ።

ባይነዷቸውም ታዲያ የቮልስ ወዳጆች እልፍ ናቸው። ባለማቀፍ ደረጃ ዕውቋ ትውልደ ኢትዯጵያዊት ጸሐፊ መዓዘ መንግሥቴ ለምሳሌ ትዊተር ሰሌዳዋን ለጎበኘ የቢትልስ ወዳጅ መሆኗን ይመሰክራል፡፡

ከቀድሞዎቹ የሥነ ጽሑፍ ሰዎች ደግሞ በዓሉ ግርማ ይጠቀሳል፡፡

ከአገራችን አውራ ደራሲያን አንዱ የነበረው በዓሉ በሕይወቱ የመጨረሻ ዓመታት የሚያሽከረክራት ቮልስ ነበረችው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ውሉ ባ'ለየለት የደራሲው መሰወር ታሪክ ውስጥ ቮልስዋ አብራ ትነሳለች፡፡

በዓሉ ከተሰወረ ከጥቂት ቀናት በኋላ ቃሊቲ መንገድ ቆማ የተገኘቸው ይቺ ቮልስ በሞተር ፈንታ አንደበት ቢኖራት ኖሮ የዘመናት ምሥጢርን በገለጠችል ነበር።

የበዓሉ ቮልስ ግን የት ትሆን ያለችው?