አገራቸው ችግር ውስጥ ሳለች ሽርሽር የሄዱት የአውስትራሊያ ጠ/ሚ ይቅርታ ጠየቁ

ሞሪሰን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ሞሪሰን

ስኮት ሞሪሰን ሃዋዪ ነበሩ በዚህ ሳምንት። ለመዝናናት። ለአዲስ ዓመት ሽር ብትን ሊሉ። አገራቸው ግን በአንዳንድ አካባቢዎች አስቸኳይ ጊዜ አውጃለች። በታሪክ ከፍተኛ የተባለ ንዳድ መከሰትን ተከትሎ አገሪቱ በሰደድ እሳት ተያይዛ ሳለ ነው እርሳቸው ሽርሽር የሄዱት።

በትንሹ መቶ በሚሆኑ አካባቢዎች የእሳት አደጋ ሠራተኞች እሳት ለማጥፋት እየተዋደቁ ነው። እስካሁን ሁለት የእሳት አደጋ ተከላካዮች ሕይወታቸውን አጥተዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ አገሪቱ አጣብቂኝ ውስጥ በገባችበት ወቅት እረፍት መውጣታቸው ያስቆጣቸው የአገሬው ዜጎች ተቃውሟቸውን በሰልፍ ገለጸዋል። ስኮት ሞሪሰንም እረፍቴን ሳልጨርስ እመጣለሁ ብለዋል።

ከመስከረም ጀምሮ በአውስትራሊያ ሰደድ እሳት 8 ሰዎች ሞተዋል፣ ሰባት መቶ ቤቶች ተቃጥለዋል። እጅግ ሰፊ ደን በእሳት ተበልቷል።

የአገሬው ዜጎች ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ሹልክ ብለው ለሽርሽር መውጣታቸውን ተከትሎ በሃሽታግ የተጠፈነጉ የተቃውሞ መፈክሮችን ወደ ማህበራዊ ሚዲያ ይዘው ተቃውሟቸውን ገልጠዋል።

ከነዚህም መሀል #WhereisScoMo, #WhereTheBloodyHellAreYou የሚሉ ይገኙበታል።

የመንግሥት ባለሥልጣናት የጠቅላይ ሚኒስትሩ እረፍት መውሰድ ችግር የለውም ሲሉ አስተባብለዋል። ነገር ግን ለሽርሽር የሄዱበትን አገር ከመግለጽ ተቆጥበዋል። ህዋዪ ናቸው የሚለውን የቢቢሲ ዘገባን ቢሯቸው ከእውነት የራቀ ነው ሲል ተችቶታል።

ነገር ግን አርብ ዕለት በአንድ ራዲዮ ቀርበው ህዋዪ ነበርኩ ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ የት እንደነበሩ አምነዋል።

እረፍት ላይ ሆኜም የሰደድ እሳቱን ጉዳይ ቶሎ ቶሎ ስከታተል ነበር፤ ይቀር በሉኝ ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።

በአየር ንብረት ጉዳይ ሞሪሰን ለምን ይተቻሉ?

በርካቶች ሞሪሰንን በአየር ንብረት ለውጥ ዙርያ ዳተኛ ሲሉ ይተቿቸዋል።

ምንም እንኳ አገሪቷ በየጊዜው በሰደድ እሳት ቁምስቅሏን እያየች ቢሆንም ይህ እየሆነ ያለው በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ስለመሆኑ ለመናገር ፍቃደኛ አይደሉም፣ የሞሪሰን አስተዳደር።

የካርበን ልቀትን ለመቀነስ ከሚያመነቱና ቃላቸውን መጠበቅ ካቃታቸው አገራት ተርታ የምትመደበው አውስራሊያ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጭምር ዝቅተኛ ውጤት ነው የተሰጣት።

ሞሪሰን እንደሚሉት በካርበን ልቀት የአውስራሊያ ድርሻ 1.3 ብቻ ነው። ነገር ግን ሌሎች ገለልተኛ መረጃዎች ይህ ቁጥር ትክክል አይደለም ይላሉ። አውስትራሊያ እንዲያውም በከሰል ኃይል ላይ ጥገኛ ስለሆነች የካርበን ልቀት መጠኗ እጅግ ከፍተኛ ነው ይላሉ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የአውስራሊያ ሙቀት ስንት ደርሷል?

በታሪክ ከፍተኛ የሚባል ሙቀት ተመዝግቧል በአውስራሊያ። በአብዛኛው የአውስራሊያ ስቴቶች ሙቀቱ ከ45 ዲግሪ ከፍ ብሎ ነበር።

ሐሙስ ለታ ይህን ተከትሎ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እስከመታወጅ ደርሶ ነበር። ለ7 ቀናት የሚቆይ። ይህ የሙቀት መጠን እስከ ነገ ቅዳሜ ድረስ እንደሚዘልቅ ተሰግቷል።

በዚህ ሳምንት ብቻ በአውስራሊያ እጅግ ከፍተኛው የሙቀት መጠን ነው የተመዘገበው። የእሳት አደጋ ተከላካይ ባልደረቦች ሞትን ተከትሎ የእሳት አደጋ መሥሪያ ቤት እጅግ በአስቸጋሪ ወቅት የተከሰተ አሳዛኝ ዜና ነው ብሏል።

ሰደድ እሳቱ በአንድ ቦታ ብቻ 450ሺህ ሄክታር የሚሸፍን ጉዳት አድርሷል። ከዚህ የሚወጣው ጭስ ታዲያ አንዳንድ ከተሞችን ሸፍኗቸዋል። በቪክቶሪያና በሚልቦርንና በሲድኒ አደገኛ የሚባል ጭስ በመከሰቱ የጤና ስጋትን ደቅኗል።