የናይጄርያ ፍርድቤት የወሲብ ሥራ በወንጀል አያስጠይቅም አለ

ሴተኛ አዳሪዎች ጥቃት ይደርስባቸዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የናይጄሪያ ፍርድቤት ከሰሞኑ አነጋጋሪ ውሳኔን አስተላልፏል።

እስካሁን በውል የወጣ የወሲብ ሥራን የሚከለክል ሕግ አገሪቱ ስለሌላት የወሲብ ሥራ ከአሁን በኋላ ወንጀል አይደለም ብሎታል።

የናይጄርያ ፍርድቤት ለወሲብ ሥራ ሕጋዊ እውቅና ሲሰጥ ይህ ለመጀመርያ ግዜ ነው።

የአቡጃ ከፍተኛ ፍርድቤት ከ2017 ጀምሮ በወሲብ ንግድ በመሰማራታቸው ታስረው የነበሩ 16 ሴቶች ካሳ እንዲከፈላቸው አድርጓል።

ሴቶቹን ወክሎ ሲከራከር የነበረው ባባቱንዶ ጃኮብ የተባለ ጠበቃ ለቢቢሲ እንደተናገረው የጸጥታ አባላት የወሲብ ንግድ ላይ ተሰማርተዋል በማለት የሴተኛ አዳሪዎችን ቤት ሰብረው በመግባት የሴቶቹን መብት ጥሰዋል ብሏል።

የሕግ ባለሞያዎች እንደሚሉት እንደዚህ ዓይነት የሕግ ውሳኔዎች ሰፊ ሕዝብ ላላት ናይጄሪያ ትርጉሙ በቀላሉ የሚታይ አይሆንም።

የወሲብ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሴተኛ አዳሪዎች በጸጥታ ኃይሎች መታሰር በናይጄሪያ የተለመደ ተግባር እንደሆነ ነው የሚነገረው።

ባለፈው ግንቦት ብቻ ከ60 በላይ ሴቶች ከወሲብ ሥራ ጋ በተየያዘ አቡጃ ውስጥ ለእስር ተዳርገዋል።

አብዛኞቹ ሴቶችም ተዘርፈናል፣ ተጎድተናል በህዝብ ፊትም ተዋርደናል ሲሉ ቅሬታቸውን ያቀርባሉ።