በማኅበረሰቦች መካከል ሰላም ለመፍጠር የቴሌቪዥን ጣቢያ የከፈተችው አዲሷ ሚኒስትር

ፊልሰን አብዱላሂ አህመድ
የምስሉ መግለጫ,

ፊልሰን አብዱላሂ አህመድ

ወይዘሮ ፊልሰን አብዱላሂ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ሆና ተሹማለች።

መጋቢት 3/2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕጩነት ቀርበው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሹመታቸው ከጸደቀው ሚኒስትሮች መካከል ለእንዲህ አይነቱ ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊነት ከበቁት መካከል አዲሷ የሆነችው ወ/ሮ ፊልሰን በማኅበረሰቦች መካከል መግባባትን ለመፍጠር የሚሰራ የቴሌቪዥን ጣቢያን መስርታ ስትሰራ ቆይታለች።

የ29 ዓመቷ ወ/ሮ ፊልሰን እስካሁን በኢትዮጵያ ውስጥ በሚኒስትርነት የኃላፊነት ቦታ ላይ ካገለገሉ ወጣት ተሿሚዎች መካከልም የምትጠቀስ እንደሆነም ይነገራል።

ከጥቂት ወራት በፊት ስለእራሷና ስለቴሌቪዥን ጣቢያዋ ከቢቢሲ ጋር ያደረገችወን ቆይታ እነሆ. . .

ፊልሰን አብዱላሂ አህመድ የተወለደችው ከሶማሌ ወላጆቿ በጅግጅጋ ሲሆን እድገቷ በአዲስ አበባ፤ የከፍተኛ ትምህርቷን ያጠናቀቀችው ደግሞ በእንግሊዝ ነው።

ከጥቂት ዓመታት በፊት በኦሮሞ እና በሶማሌ ክልል ተወላጆች መካከል በተከሰተው ግጭት የበርካቶች ህይወት ማለፉ እጅጉን እንደሚያሳዝናት ፊልሰን ትናገራለች።

በተለይም ሐምሌ 27 2010 ሶማሌ ክልል በተከሰተው ሁከት በርካቶች ከተገደሉ በኋላ ህዝቡን ለማረጋጋት ከሌሎች ጋር በመሆን ወደ ጅግጅጋ ማቅናቷን ፊልሰን ትናገራለች።

በሁለቱ ህዝቦች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማርገብ የኦሮሞ እና የሶማሌ ተወላጅ ከሆኑ ከ300 በላይ የሆኑ ወጣቶች በማስተባበር 'የይቅርታ እና የአንድነት መድረኮችን' ስታዘጋጅ እንደነበረ ታስታውሳች።

ከአዲስ አበባ እና ጅግጅጋ በተጨማሪ ሁለቱን ክልሎች በሚያዋስኑ ከተሞች ላይ ሰዎች ችግሮቻቸውን በውይይት እንዲፈቱ የሚያስችል የተለያዩ የውይይት መድረኮችን ማዘጋጀታቸውን የምታስረዳው ፊልሰን፤ "በትልቋ ኢትዮጵያ ትንሿን ሶማሌ እና ኦሮሚያ ይዘን ነበር የምንቀሳቀሰው" ትላለች።

እሷ ስታስተባበር በነበረው ህዝብን ከህዝብ ለማቀራር በተደረገው ጥረት ውስጥ ተሳታፊ የነበሩት ወጣቶች በሙሉ በበጎ ፍቃድ ተሳታፊ እንደነበሩ ትናገራለች።

የፎቶው ባለመብት, FILSON ABDULAHI AHMED

የምስሉ መግለጫ,

የቴሌቭዥን ጣቢያው በተመረቀበት እለት

በወቅቱ ወደተለያዩ ከተሞች እየተጓዙ የውይይት መድረኮችን ከማዘጋጀት ጋር ተያይዞ የነበረውን የደህንነት ስጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት "የሥራነውን መለስ ብዬ ሳስበው ደግሜ መስራት የሚቻለኝ አይመስለኝም" የምትለው ፊልሰን፤ የተፈለገውን ውጤት ማምጣት መቻሉ እንደሚያስደስታት ትናገራለች።

በአሁኑ ሰዓት በሁለቱ ክልል አዋሳኝ ድንበሮች ላይ ግጭቶች እርቀው ሰላም ስፍኖ ስትመለከት፤ 'ይህ ሰላም እንዲሰፍን የእኛ አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም' እያለች ለእራሷ እንደምትነግር ፊልሰን ትጠቅሳለች።

"የግጭቱ መንስዔ የመረጃ እጥረት ነው"

ፊልሰን ወንደማማች በሆኑት በሶማሌ እና ኦሮሞ ህዝቦች መካከል ብዙ ችግር ላሳከተለው ግጭት መንስዔው ከሆኑት ነገሮች መካከል የትክክለኛ የመረጃ እጥረት አንዱ ነው ትላለች።

ለዚህም መፍትሄ ይሆን ዘንድ ኑሮዋን ከመሰረተችበት እንግሊዝ ወደ ጅግጅጋ በመመለስ ትክክለኛ የሆነ መረጃ የሚያቀብል የቴሌቪዥን ጣቢያ ለማቋቋም መወሰኗን ታስረዳለች።

"ለሶማሌ ክልል በጣም ከሚያስፈልጉት ነገሮች አንዱ ሚዲያ ነው። በዚህ ክልል ከፍተኛ የሆነ የመረጃ እጥረት አለ። ያለው ሚዲያ አንድ ነው እሱም በመንግሥት የሚተዳደር ነው" የምትለው ፊልሰን፤ "ለህዝብ የቆመ፤ ህዝብ የሚናገርበት ሚዲያ ለማቋቋም ወስኜ ነው 'ነበድ' ቲቪን የመሰረትኩት" ትላለች።

'ነበድ' በሶማሊኛ ሰላም ማለት ነው። ይህ ነበድ የተሰኘው የሳተላይ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሶማሊኛ ቋንቋ ስርጭቱን ከጀመረ ጥቂት ወራት የተቆጠሩ ሲሆን በይፋ የተመረቀው ግን ከአምስት ወራት በፊት [ታኅሳስ] ነው።

የቴሌቪዥን ማቋቋም ቀላል እንዳልነበር የምትናገረው ፊልሰን፤ ከፊቷ ተደቅኖ የነበረው ውጣ ውረድ ግን የቴሌቪዥን ጣቢያውን ከማቋቋም እንዳላገዳት ትናገራለች።.

"የቴሌቪዥን ጣቢያውን በመመስረት ሂደት ውስጥ የመጀመሪያው አስቸጋሪ ነገር የነበረው፤ የቴሌቪዥን ጣቢያውን ለማቋቋም ድጋፍ ለማግኘት ሰዎችን ሳማክር 'የመንግሥት እጅ የሌለበት ነጻ ሚዲያ ነው' የሚለውን ሃሳብን በርካቶች ለመቀበል ተቸግረው ነበር።"

"የግል ነው፣ የእናንተ ነው። ችግራችሁን የምትናገሩበት የቴሌቪዥን ጣቢያ ነው። መንግሥት ይሰማችኋላ ብዬ ሳስረዳ ብዙ ጊዜ ወስዶብኛል" ትላለች።

የፎቶው ባለመብት, FILSON ABDULAHI AHMED

የምስሉ መግለጫ,

የቴሌቭዥን ጣቢያው በተመረቀበት እለት

ከዚህ በተጨማሪ ለቴሌቪዥን ጣቢያው መመስረት የሚያስፈልገውን ገንዘብ ከማሰባሰብ እስከ የሰው ኃይል ምልመላ ድረስ ያለው ውጣ ውረድ ቀላል የማይባል ፈተና እንደሆነ ታስረዳለች።

"በመጨረሻም ግን ተቋቁሞ ስመለከት ከፍተኛ የደስታ ስሜትን ፈጥሮብኛል። ነበድ በሶማሌ ክልል የመጀመሪያው የግል የቴሌቪዥን ጣቢያ ሲሆን፤ እኔን ደግሞ የመጀመሪያዋ ወጣት ሴት የቴሌቪዥን ጣቢያ ኃላፊ አድርጎኛል በዚህም ኩራት ይሰማኛል" ብላለች።

በሶማሊኛ ቋንቋ ስርጭቱን የጀመረው የቴሌቪዥን ጣቢያው ዜናና የመዝናኛዎች ፕሮግራሞች እንደሚኖሩት እንዲሁም ዋና ዓላማው ህዝብን ከህዝብ ማቀራረብ እንደሆነ ትናገራለች።

'የሶማሌዎች ተሳትፎ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ'

ፊልሰን በአገር አቀፍ ደረጃ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የሶማሌ ክልል ተወላጆች ያላቸው ተሳትፎ አነስተኛ ነው ትላለች።

ይህም ቀላል በማይባሉ የክልሉ ተወላጆች ዘንድ የመገለል ስሜት እንደፈጠረባቸው ታስረዳለች። "ቀላል በማይባሉ ሰዎች ዘንድ 'ኢትዮጵያዊ ነኝ' የሚለውን ስሜት ያለመቀበል ዝንባሌ አለ" የምትለው ፊልሰን፤ ይህ አይነት ስሜት ለመቀየር መንግሥት እስከታች ድረስ ወርዶ የተለያዩ ሥራዎችን መስራት እንዳለበት ትናገራለች።

"ከሶማሌ ክልል አልፈው ለአገር የሚጠቅሙ በጣም ብዙ የተማሩ ምሁራን አሉ። እነሱን የሚያሳትፍ ሥርዓት መኖር አለበት" በማለት ከወራት በፊት የተናገረችው ፊልሰን አሁን የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ሚኒስትር ሆና ተሹማለች።