በሞጣ በደረሰው ጥቃት 27 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለፀ

የሞጣ ከተማ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Mass Media agency

በምሥራቅ ጎጃም ሞጣ ከተማ ቤተ እምነቶች ላይ ጥቃት አድርሰዋል የተባሉ 27 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገ መሆኑ ተገልጿል።

የምሥራቅ ጎጃም ዞን ፖሊስ መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ዋና ኢንስፔክተር አያልነህ ተስፋዬ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በጥቃቱ የተጠረጠሩ እስካሁን ድረስ 27 ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ማህበረሰቡ ጥፋተኞችን እየጠቆመ በመሆኑ ቁጥሩ ሊጨምር እንደሚችል ተናግረዋል።

በፖሊስ የተያዙት ተጠርጣሪዎችም እንደተያዙበት ቅደም ተከተል ወደ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ መደረጉንም ዋና ኢንስፔክትር አያልነህ ጨምረው ገልፀዋል።

የተጠርጣሪዎቹ ቁጥርም ሊጨምር ስለሚችል አዳዲስ ሰዎች በቁጥጥር ስር የሚውሉ ከሆነም ምርመራ በማድረግና ሕጉ በሚያዘው መሰረት ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ይደረጋል ብለዋል።

በሞጣ ከተማ ሁኔታዎች መረጋጋታቸውን የተናገሩት ዋና ኢንስፔክተር አያልነህ፤ በከተማዋም ያለው ጥበቃም መጠናከሩን ተናግረዋል።

የክልሉ ፖሊስ ከልዩ ኃይል ጋር በመሆንም የሞጣ ከተማን ወደነበረችበት መረጋጋት ለመመለስ እየተሰራ ነው ያሉት ኢንስፔክተር፤ በተፈጸመው ወንጀል ዙሪያ የምርመራ ሥራውም፣ የማረጋጋት ሥራውም ሆነ ሕዝብ ለሕዝብ የማገናኘት ሥራውን ጎን ለጎን እየተካሄዱ መሆናቸውንም አስረድተዋል።

ትምህርት ቤቶች፣ የመንግሥት ቢሮዎች ተከፍተዋል በማለት ምናልባት የተቃጠሉ ሱቆች አካባቢ ያሉት ካልሆነ በስተቀር ሁሉም ወደ መደበኛው ሕይወቱ ተመልሷል ሲሉ አረጋግጠዋል።

ከክስተቱ ቀደም ብሎ አንዳንድ ግለሰቦች በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በከተማዋ ግጭት ሊቀሰቀስ እንደሚችል ለከተማው ፖሊስ ጥቆማ ቢያቀርቡም ፖሊስ ጥቆማውን ቸል በማለቱ ጥፋት መድረሱን በተመለከተ ለቀረበው ወቀሳም ምላሽ ሰጥተዋል።

ዋና ኢንስፔክተር አያልነህ እንዳሉት "ይህንን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚመላለሱ መረጃዎችን እኛም አይተናቸዋል፤ ነገር ግን ምንም በጽሁፍም ሆነ በቃል ተደራጅቶ የቀረበ ጥቆማና መረጃ አልነበረም" ብለዋል።

አርብ ማምሻውን በአማራ ክልል፣ በምሥራቅ ጎጃም ዞን ሞጣ ከተማ የሚገኘው ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን፣ ጀሚዑል ኸይራት ታላቁ መስጊድ እና አየር ማረፊያ መስጊድ ላይ ቃጠሎ መድረሱን የአካባቢው ነዋሪዎች በወቅቱ ለቢቢሲ ተናገረዋል።

ከዚህ በተጨማሪም በከተማዋ ውስጥ በሚገኙ ሆቴሎች እንዲሆም ሌሎች የንግድ ተቋሞች ላይም ጉዳት መድረሱንም በስልክ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎቹ ገልጸውልናል።

የአማራ መገናኛ ብዙኃን፤ የአማራ ክልል እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሼህ ሰኢድ አሕመድን ጠቅሶ እንደዘገበው ደግሞ አራት መስጊዶች የተቃጠሉ ሲሆን፤ ሱቆችና ሌሎች ድርጅቶችም ተዘርፈዋል።

የኢትዮጵያ ሐይማኖት ጉባኤ አባላትና የአማራ ክልል ሐይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት ሞጣ ከተማ ላይ የደረሰውን አውግዘው ወደ ስፍራው በማቅናት ከነዋሪዎች ጋር እንደሚወያዩና የተለያዩ ድጋፎችን እንደሚያደርጉም አስታውቀው ነበር።