7 ኤርትራዊያን ተጫዋቾች ካምፓላ አየር ማረፊያ ላይ ተሰወሩ

በዘንድሮ የሴካፋ ውድድር ላይ በኡጋንዳ የተሳተፈው የኤርትራ ብሔራዊ ቡደን አባላት

የፎቶው ባለመብት, የኡጋንዳ እግር ኳስ ፌዴሬሽን

የምስሉ መግለጫ,

በዘንድሮ የሴካፋ ውድድር ላይ በኡጋንዳ የተሳተፈው የኤርትራ ብሔራዊ ቡደን አባላት

ለሴካፋ የእግር ኳስ ውድድር ወደ ኡጋንዳ አምርተው ከነበሩ የኤርትራ ብሔራዊ እግር ኳስ ተጫዋቾች መካከል 7ቱ መሰወራቸው ተነገረ።

የሴካፋ ቃል አቀባይ ሮጀርስ ሙሊንደዋ ተጫዋቾቹ የጠፉት ውድድራቸውን አጠናቀው ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ኢንቴቤ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ከደረሱ በኋላ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ቃል አቀባዩ ጨምረውም "ከዚህ ቀደም የሚጠፉት ከሆቴላቸው ነበር። አሁን ግን አየር ማረፊያ ደርሰው 'ቼክኢን'እንደማድረግ፤ መኪና ተከራይተው ከሚጠብቋቸው ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን ተሰውረዋል" ብለዋል።

ኤርትራውያን እግር ኳስ ተጫዋቾች ለውድድር ከሃገራቸው ከወጡ በኋላ የመጥፋታቸው ዜና ይህ የመጀመሪያው አይደለም።

ባሳለፍነው ጥቅምት ወር ላይም ከ20 ዓመት በታች የሴካፋ ውድድር ላይ ለመሳተፍ ከሃገራቸው የወጡ አራት ኤርትራውያን ካረፉበት ሆቴል መጥፋታቸው ይታወሳል።

የሴካፋው ቃል አቀባይ ሮጀርስ ሙሊንድዋ ጥቅምት ወር ላይ አራቱ ኤርትራውያን እግር ኳሰኞች የጠፉበትን ሁኔታ ሲያስታውሱ፤ "በካምፓላ በርካታ ኤርትራውያን አሉ። ኤርትራውያኑ ካሸነፉበት ውድድር በኋላ ሆቴል ድረስ አብሮ በመሄድ ብዙዎች ድጋፋቸውን ሲሰጡ ነበር። ከዛ ተጫዋቾቹ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ተቀላቅለው ነው ከሆቴል የወጡት። እኛ የትኛው ተጫዋች የትኛው ደጋፊ መሆኑን መለየት አልቻልንም ነበር" ይላሉ።

የተጫዋቾቹን መጥፋት ሴካፋ ለኡጋንዳ መንግሥት፣ ለኡጋንዳ ስፖርት ፌዴሬሽን እና በኡጋንዳ ለኤርትራ ኤምባሲ ማሳወቁን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

7ቱ ተጫዋቾች ከሆቴል ሳይሆን አየር ማረፊያ ደርሰው ለምን እንደተሰወሩ ሲያስረዱ፤ "ከየሃገራቱ ጋብዘን የሴካፋ አዘጋጅ ኮሚቴ አባላት ያደረግናቸው ሰዎች።" አሉ የሚሉት ቃል አቀባዩ፤ በስም የሚጠቅሷቸው እና ከኤርትራ የመጡት ልዑክ የእግር ኳስ ባለሙያ ሳይሆኑ "የኤርትራ ከፍተኛ ፖሊስ አባል መሆናቸውን ተረዳን" ይላሉ።

እኚህ በስም የተጠቀሱት ግለሰብ ተጫዋቾቹ በሚያርፉበት ሆቴል አብረዋቸው ስለነበሩ ተጫዋቾቹ ከሆቴል መሰወር አለመቻላቸውን ተናግረዋል። "ውድድሩ እስኪያበቃ ድረስ ከሆቴሉ መውጣት ያልቻሉት ሲከታተላቸው ስለነበረ ነው" በማለት ይናገራሉ።

ኤርትራውያን ተጫዋቾች ለስፖርታዊ ውድድር ከሃገራቸው በወጡ ቁጥር የመጥፋታቸው ነገር እጅጉን እያሳሰበን ነው የሚሉት ሮጀር ሙሊንድዋ፤ "ይህ ከኤርትራም አልፎ ለቀጠናው እግር ኳስ አደጋ ነው" ይላሉ።

"እንደ ሴካፋ በኤርትራ እግር ኳስ ላይ ከፍተኛ ፍላጎት አለን። የኤርትራ እግር ኳስ በፍጥነት እያደገ ነው። ከ20 ዓመት የሴካፋ ውድድር ላይ የግማሽ ፍጻሜ ውድድር ሊደረግ በዋዜማ ዕለት ነው 4ቱ ተጫዋቾች የጠፉት። ከዚያም በኬንያ 1 ለ 0 ኤርትራ ተሸነፈች። ልጆቹ ባይጠፉ ኖሮ ውጤቱ ሌላ ሊሆን ይችል ነበር። በአሁኑም የሴካፋ ውድድር የፍጻሜ ተፋላሚዎች ነበሩ። በየግዜው መጥፋታቸው የኤርትራ መንግሥት ከሃገር እንዳይወጡ ያደርጋቸዋል። ይህ ደግሞ የእግር ኳስ ችሎታቸውን እንዳያሳድጉ ያደርጋል" በማለት ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

በየዓመቱ በርካታ ኤርትራውያን ወጣቶች የተሻለ ኑሮን ፍለጋ ከኤርትራ ወጥተው ይሰደዳሉ። 2016 ላይ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚጠቁመው ከአፍሪካ ሃገራቸውን ጥለው ከሚወጡ ወጣት አፍሪካውያኖች አብዛኛዎቹ ኤርትራውያን ናቸው።

በኤርትራ ውስን የፖለቲካ ነጻነት እና ማብቂያ የሌለው ብሔራዊ አገልግሎት ከሌሎች ምክንያቶች ጋር ተደማምሮ ወጣቶች ሃገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ እንደሚያደርጋቸው ይነገራል።

በጉዳዩ ላይ የኤርትራ የእግር ኳስ ፌደሬሽን አባላት ምላሽ እንዲሰጡን ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።