ቦይንግ ዋና ስራ አስፈፃሚውን ቢያሰናብትም በ737 ማክስ ላይ ስጋቶቹ እንዳሉ ናቸው

Dennis Muilenburg

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቦይንግ ዋና ስራ አስፈጻሚውን፣ዴኒስ ሚሌንበርግ፣ በድርጅቱ ላይ ያለውን እምነት ለመመለስ በሚል ከስራ ማባረሩ ይታወሳል። ኩባንያው ይህንን ውሳኔ ያሳለፈው ሁለት 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ ከተከሰከሱ እና ከ340 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ካጡ በኋላ ነው።

ከእነዚህ አውሮፕላኖች መከስከስ በኋላ ቦይንግ ከደህንነት ይልቅ ትርፍን አስቀድሟል በሚል ወቀሳዎች ሲቀርቡበት ነበር።

ቤተሰቦቻቸውን በአውሮፕላን አደጋው ያጡ ሰዎች የስራ አስፈጻሚውን ከስራ መሰናበት ቢዘገይም ትክክለኛ እርምጃ ነው ብለዋል።

ነገር ግን ቦይንግ የተሰናበቱትን ዋና ስራ አስፈጻሚ ረዥም ጊዜ ባገለገሉት የቦርድ አባሉ ለመተካት መወሰኑ አሁንም ጥያቄዎች እንዲነሱ አድርጓል።

አዲሱ ሥራ አስፈጻሚ ዴቪድ ካልሆን፣ ኩባንያውን በቦርድ አባልነት ከ2009 ጀምሮ ያገለገሉ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የዋና ሥራ አስፈፃሚ ኃላፊነቱን እና ፕሬዚደንት ሆነው እንዲያገለግሉ መሾማቸው ታውቋል።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ቁጥር 302 ሚስቱን ያጣው ፓል እንጆሮጌ " የስራ አስፈፃሚው ሚሌንበርግ መባረር የሚያስደስት ቢሆንም አሁን ግን ድርጅቱ አስተዳዳሪዎቹን የሚመርጥበትን መስፈርት መለስ ብሎ መመልከት አለበት" ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።

አክሎም " ካልሆን ለቦታው የሚመጥን ሰው አይደለም" ብሏል።

ሌላኛዋ በኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ አባቷን ያጣችው ዚፖራ ኩሪያ ደግሞ ሚሌንበርግ መተካት የነበረበት "ከረዥም ጊዜ በፊት" መሆኑን ተናግራ፤ ነገር ግን ለአውሮፕላኖቹ መከስከስ ኃላፊነት የሚወስዱ ሌሎች ሰዎችም መኖር አለባቸው ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

አክላም "አሁን የድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መልቀቅ እንዳለባቸው ይሰማኛል" ብላለች።

የተደረጉ ለውጦች

ቦይንግ ሁለት 737 ማክስ አውሮፕላኖቹ በአምስት ወራት ልዩነት ከተከሰከሱ በኋላ ከግራም ከቀኝም ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገበት ነው። የቦይንግ ምርት የሆኑት ሁለት 737 ማክስ 800 አውሮፕላኖች መከስከሳቸውን ተከትሎ ለዘጠኝ ወራት ያህል ሞዴሉ እገዳ ተጥሎበትም ቆይቷል።

ኩባንያው በዚህ እያለቀ ባለው የፈረንጆች ዓመት በሽያጭም በብቃትም ምርጡ የተባለውን አውሮፕላን አየር ላይ ለማዋል እቅድ የነበረው ቢሆንም የአሜሪካ ተቆጣጣሪው መስሪያ ቤት በፍጥነት ወደ በረራ እንዲገባ ምስክርነቱን እንደማይሰጠው አስታውቋል።

ባለፈው ሳምንት ቦይንግ ምርቶቹን እንደሚያቋርጥ ማስታወቁ ይታወሳል።

ድርጅቱ አርብ እለት ወደ ዓለም አቀፉ የሕዋ ማዕከል ሊያመጥቀው የነበረው መንኮራኩር የቴክኒክ ችግር ገጥሞት ሌላ ፈተና ውስጥ ወድቆም ነበር።

በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ እያለ የተሾሙት ዴቪድ ካልሆን የዋና ሥራ አስፈፃሚ ኃላፊነቱን ይዘውና ፕሬዚደንት ሆነው ከፈረንጆቹ ጥር 13 ጀምሮ ማገልገል ይጀምራሉ።

ላውረንስ ኬልነር ደግሞ የድርጅቱ የቦርድ ኃላፊ ሆነው ሊያገለግሉ እንደሚችሉም ተነግሯል።

"የዳይሬክተሮች ቦርድ፤ በካምፓኒው ላይ በራስ መተማመንን ለመመለስ፣ ወደፊት ተጠናክሮ ለመቀጠል እንዲሁም ከደንበኞች፣ ተቆጣጣሪዎች እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች ጋር ያለንን ግንኙነት ለማጠናከር፤ አመራር መቀየር አስፈላጊ እንደሆነ ወስኗል" ሲል ቦይንግ በመግለጫው ምክንያቱን አስቀምጧል።

በድርጅቱ አዲስ አመራር ሥር፤ ቦይንግ ከፌደራል አቪየሽን ባለሥልጣን [FAA] እንዲሁም ከተቆጣጣሪዎች እና ደንበኞች ጋር ግልፅ የሆነ፣ ውጤታማና የተቀላጠፈ ኮሚዩኒኬሽን እንዲኖረው የሚያስችል አሰራርም እንደሚያሻሽል አክሏል።

ድርጅቱ ይህንን ለውጥ ቢያደርግም በዋሺንግተን የሚገኙ የድርጅቱ ቀንደኛ ተቺዎች ግን አሁንም ኩባንያው ለለውጥ ባለው ቁርጠኝነት ላይ ጥያቄ አለን እያሉ ነው።

ማይክል ስቱሞ በኢትዮጲያ አውሮፕላን አደጋ ሴት ልጁን አጥቷል፤ ማይክል በአደጋው ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ግለሰቦች ቦይንግን እንዲገዳደሩት በሚል አሰባስቧቸዋል። የዋና ስራ አስፈጻሚውን ከስራ መነሳትም አስመልክቶ " ቦይንግን ያክል ኩባንያ ወደ ደህንነትና ፈጠራ የሚያንደረድር አንድ መልካም እርምጃ" ብሎታል።

ቀጣዩ እርምጃ መሆን ያለበት ደግሞ " ከአቅማቸው በታች የሚሰሩ ወይንም ችሎታ የሌላቸውን በረካታ የቦርድ አባላቱን እንዲለቅቁ ማድረግ ነው" ሲል ይናገራል።

"የፍት ዌር ችግር"

ኤምካስ (ማኑቨሪንግ ካራክተርስቲክስ ኦግመንቴሽን ሲስተም) ለሚለው ምህጻረ ቃል ነው። ይህ ሲስተም አውሮፕላኑን የሞተሩ ክብደትና የተቀመጠበትን ቦታ ምክንያት አድርጎ እንዳይቆምና እንዳያጋድል ያደርገዋል።

ይህም አውሮፕላኑ ሽቅብ በሚወጣ ጊዜ የሚያሳየውን ዝማሜ ተከትሎ ሚዛኑን እንዲያስጠብቀው ለማድረግ የተሠራ ነበር።

ነገር ግን የኢንዶኒዢያው ላየን አውሮፕላን ምርመራ ውጤት እንዳመላከተው ይህ ሴንሰር አውሮፕላኑ በአፍጢሙ እንዲደፋ የሚያደርግበት ሁኔታ አለ። ይህም የሚሆነው ሚዛኑን ለመጠበቅ የሚልከው መልዕክት (ሲግናል) እርስበርሱ የሚጣረስ በመሆኑ ነው።

ይህም ከአብራሪዎቹ ቁጥጥር ውጭ የሚሆን ነገር ነው። የተከሰከሰው የኢንዶኒዢያ አየር መንገድ ከ20 ጊዜ በላይ የአውሮፕላኑ አፍንጫ ቁልቁል እንዲያዘምና እንዲምዘገዘግ አድርጎታል።

አሁን ቦይንግ አድሼዋለሁ የሚለው ሶፍትዌር በአውሮፕላኑ አፍንጫ የምትገኘው ሴንሰር እርስበርሱ የሚጣረስ ምልእክት ካስተላለፈ ኤምካስ የተሰኘውን መቆጣጠሪያ ልክ እንደ ኤሌክትሪክ ባልቦላ ራሱን በራሱ እንዲያጠፋ የሚያደርግ ነው።