ጃኖ ባንድ በኤርትራ እንዳይዘፍን የተደረገው ሙዚቃ አለ?

የጃኖ ሙዚቃ ቡድን አባላት

የፎቶው ባለመብት, Jano band offical/Instagram

ወደ ኤርትራ የሙዚቃ ሥራዎቹን ለማቅረብ ከተጓዘው የባህል ቡድን መካከል አንዱ የሆነው 'ጃኖ ባንድ' መድረክ ላይ ሥራውን እያቀረበ እያለ እንዲያቋርጥ መደረጉን በተለያዩ የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኀን ሲገለጽ ተሰምቷል።

የሙዚቃ ባንዱ ሥራውን እንዲያቋርጥ የተደረገው 'ይነጋል' የሚለውን ሥራውን እያቀረበ እያለ እንደሆነ የተነገረ ሲሆን፤ ይህ የሆነውም በምጽዋ ከተማ በነበረው የሙዚቃ መድረክ ላይ እንደነበረ አንዳንዶች ጠቅሰው መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

የባንዱ አባል የሆነው ጊታሪስት ሳሙዔል አሰፋ እንዲሁም የባንዱ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሳሙዔል ተፈራ ለቢቢሲ እንደገለጹት "ይህ አሉባልታ ሐሰት ነው።"

አቶ ሳሙዔል ተፈራ ለቢቢሲ እንዳስረዱት በኤርትራ ለጃኖ ባንድም ሆነ ለአጠቃላይ የልዑካን ቡድኑ የነበረው አቀባበል እጅግ በጣም የተለየ ነበር።

"የሚያለቅሱ ሁሉ ነበሩ" ያሉት አቶ ሳሙዔል የጃኖ ባንድ በልዑካን ቡድኑ ውስጥ የተካተተው በኤርትራዊያኑ ጥያቄ እንደነበር ገልፀዋል።

ምጽዋ በነበረን የሙዚቃ መድረክ ላይ በርካታ ሙዚቀኞች ሥራቸውን አቅርበዋል የሚለው ጊታሪስት ሳሙዔል፤ ከእነርሱ በፊት የነበሩት ድምጻዊያን ረዥም ሰዓት በመውሰድ ሥራቸውን ማቅረባቸውን ይናገራል።

የጃኖ ባንድ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሳሙዔል በበኩላቸው "የሙዚቃ ድግሱ ሲቀርብ የነበረው በጄኔሬተር ስለነበር እና ቡድኑ ሥራውን ያቀረበው መጨረሻ ላይ በመሆኑ እንዳይቋረጥባቸው በሚል እንጂ ሌላ ምክንያት እንደሌለው" ይገልፃሉ።

አቶ ሳሙዔል አሰፋ በበኩላቸው ባንዱ ወደ መድረክ ሲወጣ ያላቸው ሰዓት አጭር ስለሆነ ሙዚቃ እንዲቀንሱ እንደተነገራቸው በማስታወስም፤ ከያዙት 19 ሥራ 13ቱን ማቅረባቸውን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

" 'ይነጋል' የሚለውን ሥራችንን አቅርበን 'ዳሪኝ' የሚለውን ጀምረን እያለ እንድናቋርጥ ተነግሮናል። ምክንያቱም የነበርንበት አካባቢ ከመሸ በኋላ [በከፍተኛ ድምጽ] መረበሽ ስለማይቻል እንደሆነም ሰምተናል" ብሏል።

ሳሙዔል አክሎም ሙዚቃቸውን ባቀረቡበት ስፍራ ሁሉ የሕዝቡ አቀባበል ደስ ይል እንደነበር በማስታወስ እነርሱም በሕዝቡ አቀባበልና በሥራቸው ደስተኛ እንደነበሩ ገልጿል።

በየሄድንበት ሁሉ ፈንዲሻ እየተበተነ የመሪ አቀባበል ነው የተደረገልን ያሉት ደግሞ ሥራ አስኪያጁ ናቸው።

ጃኖ ባንድ በኤርትራ ታዋቂ ነው ያሉት ሥራ አስኪያጁ፤ በአሥመራ የሚገኙ የሙዚቃ ፕሮሞተሮች ዳግመኛ መጥተው ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ እንደጠየቋቸው እነርሱም በድጋሚ ለመሄድም ሀሳቡ እንዳላቸው ገልፀዋል።

የጃኖ ባንድ አባላት በአሥመራ በነበራቸው ቆይታ በነጻ የሙዚቃ ሲዲያቸውን መስጠታቸውንና በቆይታቸው ደስተኛ እንደነበሩም ጨምረው አስረድተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Yemane G. Meskel/Twitter

የኢትዮጵያ የሙዚቃ ልዑክ ወደ ኤርትራ ያቀናው ባለፈው ሳምንት ታኅሣሥ 6 ቀን 2012 ዓ. ም ሲሆን ከስድሳ በላይ አባላትን ይዟል።

የኢትዮጵያ የባህል ቡድን በኤርትራ ሦስት ከተሞች የሙዚቃ ትርዒቱን እንደሚያቀርብ ቀድሞ የተነገረ ቢሆንም በምጽዋና በአሥመራ ብቻ ማቅረቡን ለማወቅ ችለናል።

ልዑካን ቡድኑ አባላት ከውጭ ጉዳይ፣ ከባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴሮች፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ ከታዋቂ ድምፃዊያንና ከጃኖ ባንድ የተወጣጡ ነበሩ።

በትናንትናው ዕለት በአሥመራ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ባዘጋጀው የእራት ግብዣ ላይ የመጨረሻ ሥራቸውን ማቅረባቸውንም የጃኖ ባንድ ሥራ አስኪያጅ ጨምረው ተናግረዋል።

የኤርትራ ስፖርትና ባህል ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ዘመዴ ተክሌ ለኤርትራ መገናኛ ብዙኀን እንዳሉት "በሁለቱ አገራት የሚደረገው የባህልና የኪነ ጥበብ ልውውጥ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በማዳበርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ ይረዳል።"

ኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ወ/ሮ ብዙነሽ መሰረት በበኩላቸው፤ ይህ ጉብኝት ባለፈው በኤርትራ የባህል ቡድን የተጀመረው ቀጣይ ምዕራፍ እንደሆነ በመግለጽ በሁለቱ አገራት መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ከዚህ ባላይ ሊያድግና ቀጣይነት ሊኖረው ይገባል ብለዋል።

ቡድኑ የሙዚቃ ሥራውን በአሥመራና ምጽዋ ያቀረበ ሲሆን፤ በዛሬው ዕለት ወደ ኢትዮጵያ ተመልሷል።

ከዚህ በፊት የኤርትራ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ባህርዳር፣ አዳማ፣ ሀዋሳ እንዲሁም አዲስ አበባ ላይ የሙዚቃ ሥራዎቹን ማቅረቡ ይታወሳል።