የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስተዳደር እና የሠራተኛ ማህበር እሰጥ አገባ

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ሊቀ መንበር ካፒቴን የሺዋስ ፈንታሁን

የፎቶው ባለመብት, Edris Kelifa

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ውስጥ ከሚገኙት የሠራተኛ ማህበራት አንዱ ከአየር መንገዱ አስተዳደር ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብቷል።

በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ሁለት የሠራተኛ ማህበራት ይገኛሉ። እኚህም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር እና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ይሰኛሉ።

'ቀዳማዊ' የምትለዋን ቃል በውስጡ የያዘው የሠራተኛ ማህበር የተመሰረተው ከ58 ዓመታት በፊት ሲሆን፤ ተቋሙ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ተብሎ ሲቋቋም፤ የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ሰራተኞችን ለማካተት እና አዲስ አመራሮችን ወደ ፊት ለማምጣት በአዲሱ ስያሜ ከሠራተኛ እና ማህበራዊ ጉዳይ ሚንስቴር እውቅና ማግኘቱን የማህበሩ ዋና ጸሃፊ አቶ አብዱ ይመር ተናግረዋል።

ይህ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ቀዳማዊ መሠረታዊ ሠራተኛ ማህበር ከአሰሪው ጋር በቅን መንፈስ በመደራደር የሠራተኛውን መብት እና ጥቅም እያስከበረ መሆኑን ከትናንት በስቲያ የማህበሩ ሥራ አስፈጻሚ አባላት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።

የዚህ ማህበር ሥራ አስፈጻሚዎች ይህን ይበሉ እንጂ፤ የሌላኛው ማህበር ማለትም፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ሊቀ መንበር የሆኑት ካፒቴን የሺዋስ ፈንታሁን በዚህ ፈጽሞ አይስማሙም።

ካፒቴን የሺዋስ "ማህበሩ አጠቃላይ የሆነ ችግር አለበት" ያሉ ሲሆን፤ ቀዳማዊ የምትለዋን ቃል የሚጠቀውም ማህበር "ለሠራተኞች መብት እና ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻረ የነበረው ሚና እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። ዜሮ ነው ማለት ይቻላል" ይላሉ። ካፒቴን የሺዋስ እንደሚሉት ይህ ማህበር ከአስተዳደሩ ጋር ጥብቅ የሆነ ወዳጅነት ነው ያለው።

የአየር መንገዱ የኮርፖሬት የሰው ኃይል አስተዳደር ምክትል ፕሬዝደንት የሆኑት አቶ መሳይ ሽፈራው፤ የአየር መንገዱ አስተዳደር እና ቀዳማዊው ማህበር ጥብቅ ወዳጅነት አላቸው የሚለው ወቀሳ ትክክል እንዳልሆነ ይናገራሉ።

"ከዚህ ማህበር ጋር የተለየ ግንኙነት የለንም። አስተዳደሩ ለማንም አያዳለም። የተከለከሉት ነገር ካለ ሕጋዊ እንደመሆናቸው መጠየቅ ይችላሉ" ብለዋል።

ከቀዳማዊው ማህበር ጋር አስተዳደራቸው እስካሁን ከ10 በላይ ስምምነቶችን መፈረሙን ያስረዱ ሲሆን፤ "አዲስ ማህበር ገና አባላቶቹን መዝግቦ አሳውቆን፣ በአባላት ጉዳዮች ላይ ተነጋግረን፣ 50+1 ሆኖ ሲመጣ ነው ገና በመጀመሪያው ስምምነት ላይ የምንነጋገረው። ስለዚህ 57 ዓመት ከኖረው ማህበር ጋር ራሳቸውን ማወዳደራቸው ትክክል አይደለም" ይላሉ አቶ መሳይ።

አቶ መሳይ ጨምረውም፤ ማህበሩ ብዙ አስርት ዓመታት የተጓዘ እንደመሆኑ፤ በጊዜ ሂደት ውስጥ በቀዳማዊ ማህበሩና አስተዳደሩ መካከል የተገነባ ግንኙነት ሊኖር እንደሚችል ከጠቆሙ በኋላ ይህ ግን አስተዳደሩ ለቀዳማዊ ማህበሩ አድሎ ያደርጋል ማለት እንዳልሆነ ተናግረዋል።

"ሠራተኛው ይበደላል"

የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር ሊቀ መንበር ካፒቴን የሺዋስ፤ በአየር መንገዱ ሠራተኞች ላይ በተለየ ደግሞ በእርሳቸው ማህበር አባላት ላይ አግባብ ያልሆኑ ጫናዎች እና አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንደሚወሰዱ ይናገራሉ።

ካፒቴን የሺዋስ እኚህ እርምጃዎች ከማስፈራሪያ እስከ ከሥራ ማገድ እንደሚደርሱ የሚናገሩ ሲሆን፤ ለዚህም ማሳያ የሚሆኑ እርሳቸው አግባብ አይደለም የሚሉትን ሁለት አስተዳዳራዊ እርምጃ የተወሰደባቸውን ሠራተኞች እንደ እማኝነት አቅርበዋል።

ለግላዊነት ሲባል ስሙን የማንጠቅሰው የአየር መንገዱ አብራሪ እና የሠራተኛ ማህበሩ አባል የሆነ ግለሰብ፤ የማህበሩ አባላት አባል በሆኑበት የቴሌግራም ቡድን ውስጥ በሰጠው አስተያየት ከሥራው ታግዷል።

ይህ አብራሪ ከሥራ የታገደበት ደብዳቤ ላይ በቴሌግራም ቡድኑ ላይ የሰጠው አስተያየት የአየር መንገዱን አስተዳደር የማይወክል ሐሰተኛ እና ዝና የሚያጎድፍ መሆኑን በመጥቀስ በሁለት ቀናት ውስጥ በጽሑፍ ምላሹን እንዲሰጥ እንዲሁም የድርጅቱን መታወቂያ በአስቸኳይ እንዲመልስ ይጠይቃል።

አቶ መሳይ ለዚህ ምላሸ ሲሰጡ፤ "አንድ ሠራተኛ ቅሬታ ካለው ቅሬታውን የሚያቀርብበት አግባብ አለው። ከዚህ ቀደም ማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀምን በተመለከተ የላክነው ሰርኩላር አለ። በዚያ መሰረት የድርጅቱን እና የአስተዳደሩን ክብር የሚነካ ነገረ እንዳያደርጉ በላክነው ማስጠንቀቂያ መሰረት ነው እርምጃውን የወሰድነው" ብለዋል።

ካፒቴን የሺዋስ አስተዳደሩ በሠራተኞች ላይ የሚያደርሰውን ጫና እንደማሳያነት ካቀረቡት ማስረጃዎች መካከል ሌላኛው፤ የአንድ አብራሪ ቤተሰብ አባል ስለ አየር መንገዱ ፌስቡክ ላይ በጻፉት አስተያየት ምክንያት አብራሪው የሶስት ዓመት ጥቅማ ጥቀሙን እንዲያጣ የተደረገበትን ደብዳቤ ዋቢ ነው።

በስም የማንጠቅሰው የአብራሪው እናት አየር መንገዱ በነጻ በሰጠው የአየር ቲኬት በረራ ካደረጉ በኋላ ሻንጣቸው ይጠፋል። በዚህ ደስተኛ ያልሆኑት ሌላ የቤተሰብ አባል ቅሬታቸውን ፌስቡክ ላይ ይገልጻሉ። ከዚያም አየር መንገዱ በካፒቴኑ በኩል የቤተሰብ አባሉ አየር መንገዱን በተመለከተ የጻፉትን አስተያየት እንዲያነሱ አስደርጓል። ቀጥሎም አብራሪው የሶስት ዓመት የቲኬት ጥቅማ ጥቅሙ እንዲታገድ ተደርጓል።

ይህ የእግድ ደብዳቤ ተፈርሞ የወጣው በአቶ መሳይ ሽፈራው ነው።

"እኔ ነኝ ደብዳቤውን የጻፉኩት፤ በወቅቱ ካፒቴኑንም አነጋግሬዋለሁ፤ ድርጅቱ ለሠራተኛው ነጻ ቲኬት የመስጠት ግዴታ የለበትም። እንደ ጥቅም ነው የሚሰጠው። እንደ የራስ ቤት መደረግ የነበረበት ሻንጣውን እንዴት አድርገን እናገኘዋለን በሚለው ላይ ነው መነጋገር የነበረብን። ይህም ውሳኔ የተወሰነው ነጻ ቲኬት የምንሰጥበትን ፖሊሲ መሰረት በማድረግ ነው" ብለውናል።

የፎቶው ባለመብት, Capitain Yeshiwas

ከዚህ በተጨማሪ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሠራተኞች መሠረታዊ ማህበር በአየር መንገዱ ላይ ከሚያቀርባቸው ክስ መካከል፤ የማህበሩ አባላት ከደሞዛቸው ተቆራጭ ሆኖ ወደ ማህበሩ አካውንት እንዲገባ ፈቃዳቸውን ቢሰጡም አስተዳደሩ ግን ይህን ተፈጻሚ ለማድረግ እምቢተኛ ሆኗል የሚለው ይገኝበታል።

ካፒቴን የሺዋስ "እያንዳንዱ አባል ከደሞዜ ተቆራጭ ሆኖ ወደ ማህበሩ ገቢ ይደረግ ብሎ የፈረመበትን ወረቀት ይዘን ወደ አየር መንገዱ የሰው ሃብት አስተዳደር ብንሄድም አየር መንገዱ ደሞዝ አልቆርጥም በማለት ሕግ የጣለበትን ኃላፊነት አልተወጣም" ይላሉ።

አቶ መሳይ ለዚህ ምላሽ ሲሰጡ፤ "ይህ እውነት አይደለም። አባላት መዝግበው ዝርዝር አቅርበውልናል። ከሰራተኛው ላይ ደሞዝ ለመቁረጥ ህጋዊ ፍቃድ የሚሰጠው ሰራተኛው ብቻ ነው። ይህ ደግሞ ሰራተኛው ራሱ ከደሞዜ ቆርጠህ አስገባ ሲለኝ እንጂ ማህበሩ ስላለ አይደለም" ይላሉ።

አቶ መሳይ ጨምረው እንደተናገሩት፤ ከማህበሩ ሊቀ መንበር የደረሳቸው የአባላት ዝርዝር እንጂ ሊቀ መንበሩ እንደሚሉት አባላት ከደሞዛቸው ተቆራጭ እንዲሆን የፈቀዱበት ደብዳቤ አይደለም።

ካፒቴን የሺህዋስ በሊቀ መንበርነት የሚመሩት የኢትዮጵያ አየር መንገድ መሠረታዊ የሠራተኛ ማህበር 4900 በላይ አባላት እንዳሉት የገለጹ ሲሆን፤ ከሌላኛው ማህበረ እና ከአየር መንገዱ አስተዳደር ጋር ስለሚገኙበት ሁኔታ ነገ ማለትም አርብ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡ ተናግረዋል።