በቡርኪናፋሶ ጂሃዲስቶች ባደረሱት ጥቃት በርካታ ሴቶች ተገደሉ

የቡርኪናፋሱ ወታደር በሶኡም ቅኝት እያካሄደ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

በቡርኪናፋሶ የእስላማዊ ቡድን አባላት እንደሆኑ የተጠረጠሩ ታጣቂዎች በወታደራዊ ካምፕ በከፈቱት ጥቃት 35 ሰዎች ተገድለዋል ሲሉ የሀገሪቱ ባለስልጣናት ተናግረዋል።

ከተገደሉት ሰዎች መካከል አብዛኛዎቹ ደግሞ ሴቶች መሆናቸው ታውቋል።

በሀገሪቱ ሰሜናዊ ሶኡም አውራጃ ማክሰኞ ዕለት በተከፈተ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ 7 ወታደሮች ሲገደሉ 80 ታጣቂዎችም ሞተዋል ብለዋል። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ሮች ማርክ የሁለት ብሔራዊ የሐዘን ቀን አውጀዋል።

እስካሁን ድረስ የትኛውም ቡድን ለጥቃቱ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ አላለም።

ከዚህ ወር ቀደም ብሎ አንድ ታጣቂ በቡርኪናፋሶ ምስራቃዊ ክፍል በሚገኝ ቤተ ክርስትያን ውስጥ በከፈተው ተኩስ 14 ሰዎች መገደላቸው ይታወሳል። እ.አ.አ. ከ 2015 ጀምሮ የጂሃዲስቶች ጥቃት በቡርኪናፋሶ እየጨመረ መጥቷል።

ከዚህ ቀደም በሰላማዊቷ የምትታወቀው ቡርኪናፋሶ ከማሊ ወደ ግዛቷ በገቡ የእስላማዊ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ ጥቃት እየደረሰባት ትገኛለች።

ቡርኪናፋሶ ከማሊ ጋር በሚያዋስናት ድንበር አካባቢ እስላማዊ ታጣቂዎች ስፍራውን የሚቆጣጠሩት ሲሆን በዚህ አካባቢም በተደጋጋሚ ግጭቶች ይከሰታሉ።

እስላማዊ ታጣቂዎች በቀጠናው ያላቸው እንቅስቃሴ እየጨመረ በመምጣቱ አሁን ደግሞ በቡርኪናፋሱ ያላቸውን ተጽዕኖ እያሰፉ ነው።