የዘረፈውን ገንዘብ 'መልካም በዓል' እያለ የበተነው አዛውንት በቁጥጥር ስር ዋለ

ዴቪድ ኦሊቨር

የፎቶው ባለመብት, Colorado Springs Police

ሰኞ ምሳ ሰዓት ላይ በኮሎራዶ ወደሚገኘው የአካዴሚ ባንክ የ65 ዓመቱ አዛውንት ያመሩት እንደ 'ገና አባት' ስጦታ ይዘው ቸር እየተመኙ በዓሉን ለማድመቅ አልነበረም።

ለመዝረፍ ነው።

ባንኩን ከዘረፉ በኋላ ጎዳና ላይ በመውጣት "መልካም በዓል፤ መልካም ገና'' እያሉ ገንዘቡን መበተን።

ምናልባት በአእምሯቸው ውስጥ የገና አባትን ለሚጠብቁ ምንዱባን ልድረስላቸው ብለው ይሆናል። ይህ ግን ከእርሳቸው ቃል አልተረጋገጠም።

ጢማሙን አዛውንትና ተግባራቸውን ያዩ ለኮሎራዶ ጋዜጠኞች ቃላቸውን ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል።

" ባንኩን ዘርፎ ከወጣ በኋላ ገንዘቡን በየአቅጣጫው አርከፈከፈው"

ፖሊስም " ነጭ ጢማም አዛውንት" ሰኞ ምሳ ሰዓት ላይ በኮሎራዶ አካዴሚ ባንክን ዘርፏል ሲል አስረድቷል።

የዓይመን እማኙ አክለው " 'መልካም ገና' እያለ ገንዘቡን ከቦርሳው እያወጣ በተነው።" ብለዋል።

ሁኔታቸውን ለተመለከተ ባንክ የሚዘርፉ ሳይሆን እርዳታ የሚጠይቁ አዛውንት ይምሰሉ እንጂ እርሳቸው ግን ፊቴ ቢያረጅም ልቤ አላረጀም ያሉ ይመስላል።

ባንኩን ከዘረፉ በኋላ፤ ገንዘቡን እንደቄጤማ ጎዳናው ላይ ጎዝጉዘው ወደ ስታር ባክስ ቡና መሸጫ ሄዱ። አንድ ወፍራም ቡና እንደወረደ ለማለት አልነበረም።

ፖሊስ ለመጠበቅ። ፖሊስ እንዳልጠፋብህ እዚህ ተቀምጫለሁ ዓይነት ነው።

ፖሊስ ካቴናውን እያቅጨለጨለ መጥቶ ከወሰዳቸው በኋላ ቁጥር ሰጥቶ ስም አስፍሮ ፎቶ አንስቶ እስር ቤት ወርውሯቸዋል።

በወቅቱ በዚያ መንገድ ላይ እግር ጥሏቸው የተገኙ መንገደኞች እጃቸው የቻለውን ያህል ሰብስበው አልወሰዱም። ይልቅስ አንድ ሁለት ብለው ቆጥረው ለተዘረፈው ባንክ መመለሳቸው ታውቋል።

ኮሎራዶ ፖሊስ ተጠርጣሪውን ግለሰብ ስሙ ዴቪድ ዋይን እንደሚባል ገልጾ እድሜው 65 ነው ካለ በኋላ፤ ማንም አልረዳውም ወንጀሉን ብቻውን ነው የፈፀመው ብሏል።