በምሥራቅ ሐረርጌ የቢላል መስጂድንና ራጉዔል ቤተ ክርስትያንን የሚያሰሩት ካህን

መላዕከ ሕይወት ቆሞስ አባ አክሊለ ማርያም
አጭር የምስል መግለጫ "ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ብሆንም ለአንድ ሐይማኖት ብቻ ብቆም እግዚአብሔርን ራሱ ያሳፍረዋል"

መላዕከ ሕይወት ቆሞስ አባ አክሊለ ማርያም፣ በምሥራቅ ሐረርጌ በቀርሳ ወረዳ የላንጌ ቅዱስ ራጉዔል ቤተ ክርስትያንና የቢላል መስጂድን ያሰራሉ።

የአገልግሎት ስፍራቸው በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት ሰንዳፋ በኬ ማርያም መሆኑን የሚናገሩት ካህን በምሥራቅ ሐረርጌ የሚገኝ መስጂድንና ቤተ ክርስቲያንን በእኩል ቆመው ያሳንጻሉ።

የሚያገኛቸውን ሙስሊምና ክርስቲያን በእኩል ለቤተ እምነቶቹ ማሰሪያ ሲጠይቁ ግር ይል ይሆናል። እርሳቸው ግን ታሪክ አጣቅሰው ከቅዱሳት መጻህፍት አመሳክረው ኃላፊነታቸው የሁሉም ምዕመናን፤ በሙስሊሙም በክርስቲያኑም ወገን፤ መሆን እንዳለበት ያስተምራሉ።

ከምሥራቅ ሐረርጌ መምጣታቸውን የሚሰማ የመጀመሪያ ጥያቄው በአካባቢው የሚገኙ ክርስትያኖችና አብያተ ክርስትያናት ሁኔታን ነው። እርሳቸው ደግሞ የላንጌ አካባቢ ሕዝብን ፍቅር ተናግረው አይጠግቡም።

በመስጅዶች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት የሚያወግዙ ሰልፎች ተካሄዱ

'ተዋዶ ያለበት እስላም ክርስቲያኑ'

በ2007 ዓ.ም ሐረር የቁልቢ ገብርዔል ገዳምን ለመሳለም በሄዱበት ወቅት ከቁልቢ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኘውን የላንጌ ቅዱስ ራጉዔል ቤተ ክርስትያንን መመልከታቸውን ያስተውላሉ።

በአካባቢው ያሉ ክርስትያኖች ኑሯቸው ከእጅ ወዳፍ መሆኑን አካባቢው ዝናብ አጠር በመሆኑ የዓመት ቀለባቸውን በዓመት አንዴ የሚጥለውን ዝናብ ጠብቀው እንደሚያመርቱ ይረዳሉ።

"በጎጃም ማርያም ቤተክርስቲያን ለመስጊድ 3ሺ ብር ረድታለች' ተባልኩኝ" ሐጂ ዑመር ኢድሪስ

የአካባቢው ክርስትያኖች የሚያመልኩበት ቤተ ክርስትያን ደግሞ እርጅና ተጭኖት እየፈረሰ ነው። ስለዚህ እዚያው ቆይተው ለማሰራት ይወስናሉ። በዚያ ቆይታቸው በከተማዋ ውስጥ የሚገኘውን ላንጌ ቢላል መስጂድ ተመለከቱ።

የቤተ ክርስቲያኑም ሆነ የመስጂዱ መልክ የአካባቢው ማህበረሰብን ይመስላል። የገንዘብ አቅም በሌለበት አካበባቢ ቤተ እምነቶችም ድሃ ናቸው። ሲፈርሱ የሚያስጠግን ቢያዘሙ የሚያቀና ይቸግራል።

አባ አክሊለ ማርያም የላንጌ ቅዱስ ራጉዔል ቤተክርስትያንን አዲስ አበባና አካባቢዋ ከሚገኙ ክርስትያን ወገኖች ገንዘብ በመጠየቅ እያሰሩ ግንባታውም በጥሩ ሁኔታ እየሄደ መሆኑን አስተዋሉ።

አጭር የምስል መግለጫ በምሥራቅ ሐረርጌ ለሚገኘው የላንጌ ቢላል መስጂድ

አንድ ዓመት ባልሞላው ጊዜ ውስጥ በ500 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው የቤተ ክርስትያን ሕንጻ እንዲሁም በቅጽር ግቢው ውስጥ ለሌሎች አገልግሎቶች የሚውሉ ሕንጻዎች ተሰርተዋል።

ይህንን እያሰሩ በቅርብ ርቀት የሚገኘው የቢላል መስጂድን ተመለከቱ። መስጂዱ በሚገባ አልታነጸም፤ እድሳት ይፈልጋል። በአካባቢው የሚገኙ ሙስሊሞችን አገኙ።

በአካባቢው ያሉ ሙስሊም ወገኖች ኑሮ ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር ተመሳሳይ ነው። ክርስትያኖችና ሙስሊሞች በአካባቢው በተመሳሳይ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ነው የሚኖሩት። ሁለቱም ሰማይ ቀና ብለው አይተው፣ መሬት የሰጠቻቸውን ለቅመው የሚኖሩ አርሶ አደሮች ናቸው።

አባ አክሊለ ማርያም ሰዎች ለእናንተ እንዲያደርጉላችሁ የምትሹትን፣ እናንተም አድርጉላቸው የሚለውን መንፈሳዊ ቃል በመከተል እርሳቸውም መስጂዱን ለማሰራት መወሰናቸው ይናገራሉ።

የቅዱስ ራጉዔል ቤተ ክርስቲያን በእምነበረድ ታንጾ ከጎኑ የቢላል መስጂድ በእድሳት እጦት አዝሞ ማየት አልሆነላቸውም።

በእምነት ክርስትያን ቢሆኑም ከክርስትና አስተምህሮ መካከል አንዱ የሆነው የሰው ልጅን በሙሉ በእኩል ማገልገል በመሆኑ መስጂዱንም ለማሰራት መወሰናቸው ይናገራሉ።

ሁለት እምነቶችን በአንድ ጣራ ለአስርታት ያሳደሩ ጥንዶች

በዚህም የተነሳ ለእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ማመልከቻ በመጻፍ ለሙስሊም ወንድሞችም መስጂድ ለማሰራት እንደሚፈልጉ ጠየቁ።

የእስልምና ጉዳዮችም እንዲህ አይነቱ ተግባር በኢትዮጵያ ውስጥ እስልምና በገባ ወቅት የነበረ መሆኑን በማስታወስና በማድነቅ የድጋፍ ደብዳቤ ለአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች እንደጻፉላቸው ይናገራሉ።

የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች በበኩሉ በአዲስ አበባ ለሚገኙ መስጂዶች በአጠቃላይ የድጋፍ ደብዳቤ ከጻፈላቸው በኋላ ከሙስሊሙ ማህበረሰብ ገንዘብ ማሰባሰባቸውን ይናገራሉ።

አጭር የምስል መግለጫ በምስራቅ ሐረርጌ የሚገኘው ቅዱስ ራጉዔል ቤተክርስትያን

አባ አክሊለ እንደሚናገሩት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከአዲስ አበባ የሙስሊም ማህበረሰብ በተሰበሰበ ገንዘብ በላንጌ የሚገኘው መስጂድን መሰረት የማስገንባት ሥራ ተከናውኗል።

ይህንን ተግባራቸውን ማከናወን የጀመሩት መስከረም 2011 ዓ.ም ላይ ሲሆን ደብዳቤ ተጽፎላቸው ወደ ሥራ የገቡት ደግሞ ጥቅምት 2/2011 ዓ.ም መሆኑን ያስታውሳሉ።

እርዳታ የማሰባሰብ ሥራውን የጀመሩት ፒያሳ ከሚገኘው ኑር መስጂድ መሆኑን የሚናገሩት አባ አክሊለ፤ የመስጂዱ የበላይ ጠባቂና አስተዳዳሪ ኡስታዝ መንሱር ከፍተኛ ድጋፍ እንዳደረጉላቸው ይገልፃሉ።

አባ አክሊለ በላንጌ የሚገኘውን መስጂድ ሲያሰሩም ሆነ ቤተ ክርስቲያኑ ሲያስገነቡ በእኩል ክትትል እንደሚያደርጉ ገልፀው ቤተ ክርስቲያኑ ፎቅ ስለሆነ መስጂዱም ፎቅ መሆን አለበት በሚል ሀሳብ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በሞጣ የተፈጠረው ምንድን ነው?

መስጂዱ የምድር ቤት ግንባታው ተሰርቶ መጠናቀቁንና የላይኛውን ክፍል ግንባታ ለማስጀመር ገንዘብ አጥሮ በድጋሚ የእርዳታ ድጋፍ ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ መጥተው ከሀገር ውስጥም ሆነ ከውጪ ከሚገኙ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት ገንዘብ እያሰባስቡ እንደሆነ ይናገራሉ።

እርሳቸው ክርስቲያን ሆነው መስጂዱን ለማስገንባት በእምነት ገንዘባቸውን የሚሰጡ ሙስሊሞች መኖራቸው የሚያሳየው ምን እንደሆነ አባ አክሊለ ሲናገሩ፣ ዛሬም በሕዝቦች መካከል ያለ መተሳሰብና አብሮ የመኖር ባህል ጠንካራ መሆኑን ነው ይላሉ።

ለሰሚም ሆነ ለተመልካች የእርሳቸው ድርጊት ኢትዮጵያና እስልምና ያላቸውን ግንኙነት እንደሚያሳይ በመግለጽ፣ ሙስሊሞች ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት የተደረገላቸው መልካም አቀባበል ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ በርካታ ትምህርት እንደሚሰጥ ያስረዳሉ።

አጭር የምስል መግለጫ መላዕከ ሕይወት ቆሞስ አባ አክሊለ ማርያም በምስራቅ ሐረርጌ ዞን በቀርሳ ወረዳ ላንጌ ከተማ ለሚያሰሩት ቢላል መስጂድ ገንዘብ ለማሰባሰብ የድጋፍ ደብዳቤ ተጽፎላቸዋል

በኃይማኖትም መጻህፍት ያለው መንፈሳዊ ቃል ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰቡ በመኖር የገነባነው መዋደድና አብሮ የመኖር ባህል ለዚህ ተግባር ጠንካራ አጋዥ እንደሆናቸው ይናገራሉ።

በድርጊታቸው የሚያገኟቸው ሰዎች ደስተኛ መሆናቸውን በማንሳትም እርሳቸውም በሙስሊም ወንድሞቻቸው ተግባር ልባቸው መነካቱን ይገልጻሉ።

"ሰው ሊደሰት የሚችለው ሰውን ሲያገለግል ነው" በማለት በመስጂድ የሚያደርጉትም አገልግሎት ደስታን እንደሚሰጣቸው ያስረዳሉ።

"ምንም እንኳ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አገልጋይ ብሆንም ለአንድ ሐይማኖት ብቻ ብቆም እግዚአብሔርን ራሱ ያሳፍረዋል" በማለት ሁሉን በእኩል ማገልገል ተገቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ይናገራሉ።

በኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አባል የሆኑት ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ ስለመላዕከ ሕይወት ቆሞስ አባ አክሊለ ማርያም ሲናገሩ "በካህኑ ጥያቄ መሰረት የድጋፍ ደብዳቤ ጽፈንላቸዋል። እስካሁንም ከመቶ ሺህ ብር በላይ ለመስጂዱ ግንባታ ተሰብስቧል" ሲሉ መስክረዋል።

የእርሳቸውንም ተግባር በተመለከተ ሲያስረዱ "ይህ በጎ ድርጊት የሚያሳየን ሁሌም ሕዝቡ አንድ መሆኑንና ሳይለያይ ለመደጋገፍና ለመረዳዳት ያለውን ጽኑ ፍላጎት ነው" ብለውናል።

በምሥራቅ ሐረርጌ በቀርሳ ወረዳ የላንጌ ቅዱስ ራጉዔል ቤተ ክርስቲያን ባለሁለት ፎቅ ሕንፃው ማለቁን፣ ቤተክርስቲያኑም ጉልላቱ ላይ መድረሱን አጥሩም መሰራቱን ይናገራሉ። መስጂዱም አልቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ ጠንክረው እንደሚሰሩ ይገልፃሉ።

ምሥራቅ ሐረርጌ በቀርሳ ወረዳ እና በኩርፋ ጨለኬ ወረዳዎች የነበሩ ግጭቶችንና ስጋቶችን በማንሳትም በላንጌ ህዝበ ሙስሊሙ ከክርስቲያኑ ጎን በመቆም አብሮ የመኖር ባህሉንና ትስስሩን ጠብቆ ይህንን ወቅት ማለፉን ያስረዳሉ።

በከተማው የሚገኙ ነዋሪዎችና ቤተ ክርስቲያናትን በጽኑ ተጋድሎ ከጥቃት መከላከላቸውን ይመሰክራሉ።

የእርሶ መሳሪያ ሚዲያ ፕሌይ ባክን ማጫወት ኣልተቻለም።
በምሥራቅ ሐረርጌ በቀርሳ ወረዳ የላንጌ ራጉዔል ቤተ ክርስትያንና የቢላል መስጂድን በአንድነት የሚያሰሩት ካህን

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ