የካራቴ ጥበበኛው የብሩስ ሊ ልጅ በቻይና የ30 ሚሊዮን ዶላር ካሳ ጠየቀች

ብሩስ ሊን የሚመስለው ንግድ ምልክት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዝነኛው ማርሻል አርት ጥበበኛ ብሩስ ሊ ሴት ልጅ የሚመራ አንድ ኩባንያ ፈጣን ምግቦችን በማቅረብ የሚታወቅ ሌላ ኩባንያ ላይ ክስ አቅርቧል።

የብሩስ ሊ ሴት ልጅ ሻነን ሊ እንደከሰሰችው ከሆነ ሪል ኩንጉፉ የሚባለው በቻይና ግዙፍ ከሚባሉት የፈጣን ምግቦች አቀነባባሪ አንዱ የሆነው ምግብ ቤት የአባቴን ምስል ሳያስፈቅድ ለንግድ ምልክትነት ተጠቅሞበታል ብላለች።

ሻነን ሊ ይሄ ሪል ጉንጉፉ የተባለው ግዙፍ የምግብ ቤቶች ሰንሰለት የአባቷምን ምስል በቶሎ እንዲያነሳና እስካሁንም ላደረሰው ኪሳራ ካሳ እንዲሆን 30 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፍል ጠይቃለች።

ሪል ጉንጉፉ የሚባለው የፈጣን ምግቦች ኩባንያ በበኩሉ በሰጣት ምላሽ "የአባትሽን ምስል የተጠቀምኩት እኮ የቻይና ባለሥልጣናት ፈቅደውልኝ ነው" ብሏታል።

ምስሉ አንድ ጠቆር ያለ ጸጉር ያለው ካራቲስት በማርሻል አርት እንቅስቃሴ ላይ ሆኖ የሚያሳይ ነው። ያ ሰው ብሩስ ሊን ይመስላል።

ሪል ኩንጉፉ የፈጣን ምግብ አብሳይና አቅራቢ ድርጅት ለክሱ በሰጠው ምላሽ ይህን የንግድ ምልክት የሰጠን የብሔራዊ ንግድ ምልክቶች ኤጀንሲ ሲሆን እጅግ ፈታኝና አስቸጋሪ የምርመራ ሂደትን ታልፎ የተሰጠን ምልክት ነው። ላለፉት 15 ዓመታትም ስንጠቀምበት ነበር። አሁን ምን አዲስ ነገር ኖሮ ነው የምትከሺን ብሏታል፣ የብሩስ ሊን ሴት ልጅ።

መቀመጫውን ጓንዡ ያደረገው ይህ የፈጣን ምግብ አቅራቢ ድርጅት የተመሠረተው በፈረንጆቹ በ1990 ሲሆን በቻይና ብቻ 600 ቅርንጫፎች አሉት።

ብሩስ ሊ ኢንተርፕራይዝ ደግሞ የዝነኛውን የብሩስ ሊን ምስሎች ለገበያ በማቅረብና የማስታወቂያ ፍቃድ በመስጠት የሚተዳደር ኩባንያ ነው።

በዚህ ኩባንያ ድረ ገጽ እንደተመለከተው ኩባንያው የዝነኛውን የብሩስ ሊ ፍልስፍናና የማርሻል አርት ጥበብ ለዓለም ማድረስ፣ በሰው ልጆች ዘንድ መልካም መነቃቃትን መፍጠር፣ በጎ ስሜትን ማብዛት እንዲሁም ለዓለም አንድነትና ፍቅር መሥራት ላይ ያተኩራል።

የብሩስ ሊ ሴት ልጅ ያቀረበችውን ክስ የቻይና ባለሥልጣናት ተገቢውን ትኩረት ሰጥተው ያጤኑታል ተብሎ ይጠበቃል። ምክንያቱ ደግሞ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቻይና ለአእምሮ ንብረት ጥበቃ ልዩ ትኩረት እየሰጠች ስለመጣች ነው።