ዶናልድ ትራምፕን ከዝነኛው ፊልም ማን ቆርጦ ጣላቸው?

ትራምፕ በሆም አሎን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

ትራምፕ ጎልማሳ ሳሉ ሆም አሎን ላይ ተውነዋል

በፈረንጆች ገና ዙርያ ከሚያጠነጥኑና በሚሊዮኖች ዘንድ ከማይረሱ ፊልሞች አንዱ 'ሆም አሎን' የተሰኘው ፊልም ነው። ፊልሙ የ8 ዓመት ሕጻን በቤተሰቦቹ ተዘንግቶ ለብቻው በፍርሃት ውስጥ ሆኖ የቆየባቸውን ቀናት የሚተርክ ነው።

ታዲያ በዚህ ሆም አሎን 2 በተሰኘው ፊልም ላይ የአሁኑ አወዛጋቢ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ይተውኑበት ነበር።

ትራምፕ የአገር ቤት ፊልም ጥበበኞች አስተኔ ገጸ ባሕሪ የሚሉትና ፈረንጆቹ (cameo appearance) ብለው የሚጠሩት በአንድ ፊልም ላይ ውልብ ብሎ የመታየት ያህል ኢምንት ሚና ያለው ቦታ ነበራቸው።

ታዲያ የካናዳው ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ሲቢሲ ይህን ፊልም ከሰሞኑ ሲያስተዋውቅ እርሳቸው የሚታዩበት ቦታ ላይ ቆረጥ ሳያደርጋቸው አልቀረም።

የጣቢያው ቃል አቀባይ ቸክ ቶምሰን እንደሚሉት 120 ደቂቃዎች በሚረዝመው ፊልም 8 ደቂቃ ያህሉ ተቆርጦ ወጥቷል። ይህ የተደረገው ግን ዛሬ ሳይሆን በፈረንጆቹ 2014 ነው። ያን ጊዜ ደግሞ ትራምፕ ገና ወደ ሥልጣንም አልመጡም ብለዋል።

ዶናልድ ትራምፕ ተቆርጠው አልተጣሉም፤ የፖለቲካ ትርጉም ሊሰጠውም አይገባም ብለዋል።

ይህ አርትኦት የተሠራበት ፊልም በያዝነው የፈረንጆች የመጨረሻ ወር ላይ ለዕይታ ቀርቧል። ሆኖም የትራምፕ አድናቂዎች የካናዳ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያን ሲወርዱበት ነው የከረሙት።

የትራምፕ የበኩር ልጅ ትራምፕ ጁኒየር ትናንት ሐሙስ ለት በትዊተር ሰሌዳው ላይ ድርጊቱን "ቀሽም" ሲል አውግዞታል።

በትንሽ በትልቁ አወዛጋቢ አስተያት በመስጠት የሚታወቁት ትራምፕ በበኩላቸው ሐሙስ በድርጊቱ ተሳልቀዋል። "እኔ የሌለሁበት ሆም አሎን ፊልም መቼም አይጥምም" ሲሉ።

ከዚህም አልፈው ከካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር የነበራቸውን አለመግባባት መዘው በማውጣት ለማሾፍ ሞክረዋል። የርሳቸው ሚና በፊልሙ ከተቆረጠ በኋላ ትራምፕ እንዲህ ጽፈዋል።

"ይሄ ጀስቲን ቲ ለናቶና ለንግድ ገንዘብ ስላስከፈልኩት (የተወንኩበትን ክፍል እየቆረጠ) እየተበቀለኝ ሳይሆን አይቀርም"

ትራምፕ ከሰሞኑ በጉዳዩ ላይ ዘርዘር ያለ አስተያየት ሲሰጡ እንዲህ ብለዋል።

"እውነት ነው ሆም አሎን 2 ላይ ተውናለሁ። በየዓመቱ ብዙ ሰዎች ይህን ነገር ያነሱታል። በተለይ በክሪስማስ ሰሞን። በተለይ ትንንሽ ልጆች ሲያገኙኝ በፊልም አውቅኻለሁ ይሉኛል። እነሱ በፊልም እንደሚያውቁኝ በቴሌቪዥን አያውቁኝም"

ትራምፕ ይቀጥላሉ፦ "ነገር ግን ፊልሙ ምርጥ ፊልም ነበር። ያን ጊዜ ወጣት ነበርኩ። በዚያ ፊልም ላይ በመታየቴ ኩራት ይሰማኛል"

ትራምፕ አስተኔ ገጸ ባሕሪ (የውልብታ ሚና) ባላቸው ፊልሞች ሲተውኑ ሆም አሎን 2 ብቸኛው አይደለም። 'ዙላንደ'ር እና 'ጎስትስ ካንት ዱ ኢት' በተሰኙ ሌሎች ፊልሞችም ውልብ ብለው የመጥፋት ያህል ይተውናሉ።

በዚህ ሆም አሎን 2 ፊልም ላይ ትራምፕ በኒውዮርክ ፕላዛ ሆቴል ትንሹን ልጅ (ዋና ገጸ ባሕሪውን) አቅጣጫ ሲያመላክቱት ይታያሉ። ፊልሙ በሚቀረጽበት በዚያ ዘመን ትራምፕ የሆቴሉ ባለቤት ነበሩ።