ቡርኪናፋሶ፡ 'ተዋዶ ያለበት እስላም ክርስቲያኑ'

አፎሳቶና ዴኒስ ልጃቸውን አቅፈው

የፎቶው ባለመብት, CLAIR MACDOUGALL

የምስሉ መግለጫ,

አፎሳቶና ዴኒስ ልጃቸውን አቅፈው

የፈረንጆች ገና ላይ የተፈጸመው አሰቃቂ የቤተክርስቲያን ጥቃት የዓለም ሚዲያ ካሜራውን ቡርኪናፋሶ ላይ እንዲያጠምድ አድርጎታል። የቡርኪናፋሶ ታሪክ ግን ይህ አልነበረም።

እንዲያውም ያቺ አገር ይበልጥ የምትታወቀው በሙስሊም-ክርስቲያን አብሮ የመኖር የዳበረ ልምዷ ነበር።

ቡርኪናፋሶ ሙስሊሞች የሚበዙባት አገር ናት። ከክርስቲያን ወንድሞቻቸው ጋር የሚተቃቀፉ፣ ክርስቲያን እህቶቻቸውን የሚወዱ ሙስሊሞች የሚበዙባት አገር። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ጽንፈኞች እያመሷት ነው።

ለምሳሌ ሰሞኑን እንኳ በገና ዋዜማ 30 ሰዎች እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ ተገድለዋል። ያውም ቤተ ክርስቲያን ውስጥ። ብዙዎቹ ታዲያ ሴቶች ናቸው። ይህን ጥቃት የፈጸሙት ጽንፈኛ ጂሃዲስቶች እንደሆኑ እየተነገረ ነው።

ከዚያ ቀደም ብሎ ከሁለት ወራት በፊት በአንድ መስጊድ ላይ ጥቃት ተፈጽሞ 15 ሰዎች ተገድለው ነበር።

መገናኛ ብዙኀን በነዚህ ጥቃቶች ዜና ተጋርደዋል። "የቡርኪናፋሶ እውነተኛ መልክ ግን ይህ አልነበረም" ትላለች ኡጋዱጉን የጎበኘቸው ባልደረባችን ክሌር ማክዱጋል።

እንዲያውም ቡርኪናፋሶ ታሪኳ የሚያስቀና ነበር። ሙስሊምና ክርስቲያን በፍቅር አንድ ማዕድ የሚቋደስባት፣ በፍቅር የሚወዳጁበት ብሎም ሦስት ጎጆ የሚመሠረትባት አገር ነበረች።

የፎቶው ባለመብት, CLAIR MACDOUGALL

የምስሉ መግለጫ,

ልጃቸው አይሪስ የገና አባትን ፎቶ ይዛ

"እንዲያው..." ትላለች ክሌር... "ከቡርኪናፋሶ ሕዝብ 23 ከመቶው ከሙስሊምና ክርስቲያን አማኞች በተፈጠረ ጋብቻ የተገኘ ነው።"

ክሌር ይህንን የቡርኪናፋሶን የሃይማኖት አብሮነት ለማሳየት አንድ ኦጋዱጎ የሚገኝ ቤተሰብን መጎብኘት ብቻ በቅቷታል፤ እንዲህ ታስቃኘናለች።

የአምስት ዓመቷ አይሪስ ኦስኒያ ኦታራ ያደገችው በካቶሊክ እምነት ተከታዩ አባቷ ዴኒስ ኦታዋ እና በሙስሊሟ እናቷ አፎሳቶ ሳኖ እየታቀፈች ነው።

ገናን በድምቀት ታከብራለች። ኢድ ሲደርስ ደስታዋ ወደር የለውም።

እንዲያውም ኡጋዱጉ በሚገኘው ቤታቸው ከተሰቀሉት ፎቶዎች አንዱ እሷ ትንሽዬ ልጅ ሳለች አባቷ የገና አባት ጋር ቆሞ የሚያሳይ ምስል ነው።

አባቷ የክርስትና አስተምህሮትን ሊያሰርጽባት ሲሞክር እናቷ በበኩሏ ስለ ኢስላም መሠረታዊ ቀኖናዎች ታብራራላታለች።

"ወደ መስጊድ ስሄድ አብራን ነው የምትሄደው፤ እሁድ እሁድ ደግሞ ከአባቷ ጋር ቤተክርስቲያን ትሳለማለች" ትላለች እናት አፎሳቶ።

የፎቶው ባለመብት, CLAIR MACDOUGALL

የምስሉ መግለጫ,

አፎሳቶ በቀን አምስት ጊዜ ሶላት ትሰግዳለች

እናት አፎሳቶ በቀን አምስት ጊዜ ሶላት ትሰግዳለች። ጁምአ ጁምአ ግን ሁልጊዜም ከልጇ አይሪስ ጋር መስጊድ ይሄዳሉ።

ልጇ አይሪስ ዘወትር ጠዋት ጠዋት የማለዳ ጸሎት ለማድረስ (ሱብሂ ሶላት) በጊዜ ከእንቅልፏ ትነሳለች። ይህ የሶላት ጊዜ ለብዙዎች ቀላል የሚባል አይደለም።

"ኢስላም የታጋሾች ሃይማኖት ነው፤ የመቻቻል እምነት ነው፤ ሌሎች ሰዎችን ባሉበት ሁኔታ መቀበል የሚችል እምነት ነው" ትላለች።

ቤት ውስጥ አይሪስ ኢስላማዊ መጻሕፍትን ታነባለች። ከእነዚህ ኢስላማዊ መጻሕፍት ጎን ታዲያ መዝሙረ ዳዊት ተቀምጧል።

ዴኒስና አፎሳቶ ላለፉት ስድስት ዓመታት አብረው ኖረዋል። የተገናኙት ከቡርኪና ፋሶ 2ኛ ከተማ ቦቦ ዲላሶ 55 ኪሎ ሜትር ርቃ በምትገኝ ገጠራማ ቀበሌ ነበር።

በተገናኙ በዓመቱ ለመጋባት ወሰኑ። ሠርጉ ታዲያ ኢስላማዊም ክርስቲያናዊም ነበር።

"ልንጋባ ስንወስን ተቃውሞ አልደረሰብንም አልልሽም" ይላል ዴኒስ። የዴኒስ አባት መጀመርያ አካባቢ ነገሩን ተቃውመውት ነበር። በኋላ ግን ይሁና አሉት።

የፎቶው ባለመብት, CLAIR MACDOUGALL

የምስሉ መግለጫ,

አፎሳቶ፣ ዴኒስና ልጃቸው አይሪስ ቤታቸው በር ላይ

"መጀመርያ አካባቢ ነገሩ በጣም የተወሳሰበ ነበር። እንዲያውም አባቴ ብዙም ችግሩ አልታየውም፤ ከእርሱ በላይ እናቴ ናት የተንገበገበችው" ትላለች እናት አፎሳቶ።

በተለምዶ ወንዱ ክርስቲያን ከሆነና ሚስት ሙስሊም ከሆነች የሴቷ ቤተሰቦች ተቃውሞ ያነሳሉ።

ለዚህም ይመስላል ዛሬም ድረስ የፎሳቶ እናት ጋብቻቸውን ያላጸደቁላቸው።

በርካታ የቡርኪናፋሶ ቤተሰቦች ከክርስቲያንና ሙስሊም ጋብቻ የተገኙ ናቸው።

በዚያች አገር በአመዛኙ ሙስሊሞች ቤተክርስቲያን፤ ክርስቲያኖች መስጊድ ለመግባት አይከለከሉም።

ቡርኪናፋሶ በዚህ በሃማኖት ተከባብሮና ፍቅር በመኖር እንደ ተምሳሌት የምትታይ አገር ናት።

አፎሳቶ ለምሳሌ በርካታ ክርስቲያን ጓደኞች አሏት። በገና ቤተክርስቲያን ባትሄድም ቅሉ ከእናትና አባቷ ጋር ገናን ማክበሯ አልቀረም።

ኡጋዱጉ ለምትገኘው የቢቢሲ ጋዜጠኛ እንደተናገረችው "እኔ ረማዳንንም፣ ኢድ አል-አድሃንም፣ ገናንም ግጥም አድርጌ ነው የማከብረው።"

የፎቶው ባለመብት, CLAIR MACDOUGALL

የምስሉ መግለጫ,

ቡርኪናፋሶ በሃይማኖት መቻቻል መልካም ስም ነበራት

በገና ዕለት የካቶሊክ ካቴድራል በአጥቢያው ምዕመናን ይሞላል።

እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ወታደሮች ታዲያ ቤተ ክርስቲያኒቱ በር ላይ ዘብ ይቆማሉ። ምክንያቱ ደግሞ ጽንፈኛ ጂሃዲስቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አብያተ ክርስቲያናትንና አንዳንድ ሙስሊሞችን ጭምር ዒላማ ማድረጋቸው ነው።

ይህን ስጋት ተከትሎ ከሰሞኑ ቀሳውስት ለምዕመኖቻቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።

ትልልቅ ቦርሳ ይዛችሁት አትምጡ። አንዳች የተለየ እንቅስቃሴ ስታስተውሉ ለፖሊስ ሹክ በሉ ብለዋል።

ከካቴድራሉ አቅራቢያ በርካታ ሰዎች የገና ዛፍ ላይ የውሸት በረዶ የሚመስል ፕላስቲክ እየጠመጠሙበት ይታያሉ።

በገና ዕለት ክርስቲያኑ ዴኒስ ልጁን አይሪስን ወደ ኪንግ ክራይስት ቤተክርስቲያን ይዞ ይሄዳል።

"ሃይማኖቴ የሚያስተምረኝ ፍቅርንና ሕዝቦችን ከነፍጥርጥራቸው መቀበልን ነው" ይላል የክርስትና አማኙ ዴኒስ። "በዚህ ድርጊቴ ሊዳኘኝ የሚችለው ፈጣሪ ብቻ ነው።"

የሆነስ ሆነና የልጃቸው ሃይማኖት ምን ሊሆን ነው?

የአይሪስ ወላጆች እንደሚሉት ልጃቸው አይሪስ ስታድግ የመረጠችውን ሃይማኖት እንድትከተል መብቷ የእርሷና የእርሷ ብቻ ነው። እስከዚያው ግን ሁለቱንም ሃይማኖቶች ማየት፣ ከቤተሰቧ ፍቅርን መመገብ አለባት።

አባቷ ዴኒስም ሆነ እናቷ አፎሳቶ በልጃቸው ማንኛውም የወደፊት ውሳኔ ደስተኞች ለመሆን ዝግጁ ናቸው። ምክንያቱም ዴኒስ እንደሚለው "ፍቅር እኮ ከሁሉም ሃይማኖት በላይ ነው።"