የንድፈ ሐሳብ ትምህርትን ወደ ተግባራዊ ዕውቀት ለመለወጥ የሚተጋው የፈጠራ ባለሙያ

ናኦል ዳባ
የምስሉ መግለጫ,

ናኦል ዳባ

ናኦል ዳባ ይባላል። የከፍተኛ ትምህርቱን በአሜሪካ ሲከታተል ቆይቶ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሰ ከአንድ ዓመት በላይ ሆኖታል።

ሕልሙና ዓላማው የፈጠራ ሥራውን ማጠናከርና በዘርፉ ላይ ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች መርዳት እንደሆነ ይናገራል።

ናኦል ያጠናው ቲዮረቲካል ፓርቲክልስ ፊዚክስና ኢኮኖሚክስ ነው።

ወደ አገር ቤት ከተመለሰም በኋላ ያሉትን ተጨባጭ ሁኔታዎች በማጥናት በሳተላይት ሳይንስ ዘርፍ ላይ ለመሥራት ከፍተኛ ፍላጎት አድሮብኛል ሲል ነግሮናል።

በዚሁ መሰረት በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይና ሌሎች ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች በተገኙበት የፈጠራ ሥራውን አሳይቷል።

ይህንን ፈጠራውን እውን ለማድረግ በብዙ ውጣ ውረድ ውስጥ ማለፉን የሚናገረው ናኦል፤ በተለይም የሳይንስና ኢኖቬሽን ሚኒስቴር፣ ዶ/ር ጌታሁን እንዳበረታቱት ያስታውሳል።

ናኦል በሚኒስትር መሥሪያ ቤቱ ቴክኒካል ዘርፍ ላይ የሚሠሩ ሠራተኞች እንዳበረታቱት በማስታወስ፤ በአዕምሮው ውስጥ የነበረውን የፈጠራ ሐሳብ በግሉ ለመሥራት መወሰኑን ለቢቢሲ ተናግሯል።

"በልቤ ውስጥ ያለውን የፈጠራ ሥራ በግሌ መተግበር ስፈልግ አንድ ነገር ወደ አዕምሮዬ መጣ፤ ይኸውም ለሳተላይት ዘርፍ ፍላጎት ያላቸው ተማሪዎችን አሰባስቤ እነሱን እያስተማርኩ ለምን ከእነርሱ ጋር አልሠራም የሚል ነበር፤ ከዚያ በኋላም ወጣቶቹን አሰባስቤ በሁለት ሳምንት አንዴ በቪዲዮ ኮንፍረንስ ማስተማር ጀመርኩ" በማለት የፈጠራ ሥራውን መጀመሩን ያብራራል፡፡

ከዚያም በኋላ ወጣቶቹን በንድፈ ሐሳብ ያስተማራቸውን ትምህርት ወደ ተግባር በመቀየር ትንሽ ሳተላይት (cubesat) ከተማሪዎቹ ጋር መሥራት መጀመሩን ይናገራል።

ሥራውም ሰምሮለት ከሜቲዎሪዮሎጂ ኤጀንሲ ጋር በመሆን ትንሸ ሳተላይት ወደ ሰማይ አስወንጭፎ ተገቢውን መረጃ እና ምሥል ማሰብሰብ ችሏል።

"ሳተላይቷ 37 ኪሎ ሜትር ወደ ላይ በመወንጨፍ የተለያዩ መረጃዎችንና የቪዲዮ ምሥሎችን ካሰባሰበች በኋላ በምዕራብ ሸዋ ወደ አምቦ አካባቢ አረፈች" ይላል ናኦል።

ከዚያም በኋላ አንዲት ልጅ ሳተላይቷን መሬት ላይ አግኝታ ለአባቷ በመስጠቷንና ሊደብቋት ዳድተው እንደነበር ናኦል ያስታውሳል።

"እኔ በጂፒኤስ እከታተላት ስለነበር የት እንዳረፈች በመለየቴ ደርሼባት ከሰባሰበችው መረጃ ጋር አግኝቻታለሁ።"

የትኛውም አዲስ ፕሮጀክት በሚሠራበት ሰዓት ጥቃቅን ያልተሟሉ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ የሚለው ናኦል፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በሠራው የሰው አልባ አውሮፕላንም ደስተኛ መሆኑን ይናገራል።

"የመጀመሪያ ዓላማዬ ወጣቶቹን ምን ያህል አነሳስቻለሁ የሚል ነበር፤ በዚህ በኩል ከተለያዩ ሰዎች ባገኘሁት ግብረ መልስ እንደተሳካልኝ አረጋግጫለሁ። በሌላ በኩል ደግሞ ሰው አልባ አውሮፕላኗን ወደ ሰማይ በማስወነጭፍበት ሰዓት ሊኖሩ የሚችሉ ኃላፊነቶች በሙሉ ወስጄ ነበር በዚህም ተሳክቶልኛል" ይላል።

ይህንን የሰው አልባ አውሮፕላን የሠራው በራሱ ወጪ መሆኑን የሚናገረው ናኦል፤ ውጤታማ በመሆኑ ለበለጠ ሥራ እንዳነሳሳው ይናገራል።

"ብዙ ጊዜ የዚህ አገር ትምህርት በንድፈ ሐሳብ ላይ ያተኩራል። የኔ አላማ ደግሞ በንድፈ ሐሳብ የተማሩትን እንዴት በተግባር ማዋል እንደሚቻል ለማሳየት ነበር ተሳክቶልኛል"

በየትኛውም የሥራ መስክ ውጤታማ ለመሆን በቅድሚያ ሥራውን መውደድ እንደሚያስፈልግ የሚናገረው ናኦል፤ እርሱም ለሥራው ያለውን ፍቅር ያብራራል።

ከዚህም በተጨማሪ ምን ላይ ትኩረት ባደርግ የበለጠ ማሕበረሰቡን ልረዳ እችላለሁ የሚል የዘወትር ሃሳብ እንዳለው በመግለጽ ወጣቶችን እንዴት ልረዳ እችላለሁ የሚለውም የዘወትር ሃሳቡ መሆኑን ያብራራል።

እነዚህ ሐሳቦች ለፈጠራ ሥራው እንዳነሳሱትም ጨምሮ ገልጧል።

ይህንኑ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ የሰው አልባ አውሮፕላን መሥራት ብቻ ሳይሆን፣ ለመሥራት የሚያስችል ድርጅትም ማቋቋሙን ይናገራል።

በዚሁ መሠረት ኤን ጄት ማኑፋክቸሪንግ (NJT Manufacturing) የተሰኘ ኩባንያ አቋቁሟል።

ኩባንያውም ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች አሉት የሚለው ናኦል፤ ቀዳሚው ዓላማ ሰው አልባ አውሮፕላንን በኢትዮጵያ ውስጥ ማምረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በዘርፉ ፍላጎት ያላቸው ወጣቶችን በማሳተፍ ድጋፍ ማድረግ መሆኑን ያስረዳል።

በተለይም ስለ ፈጠራ ማዕከሉ ሲያብራራ ወጣቶች የፈጠራ ሥራ የሚሠሩበት፣ ሰብረው የሚለማመዱበት፣ በአዕምሯቸው ያለው ወደ ተግባር የሚለውጡበት ነው ይላል።

በተመሳሳይም ማዕከሉ ቴክኖሎጂን ከውጪ አገር በማስገባት ሰው አልባ አውሮፕላን በአገር ውስጥ የሚመረትበት መሆኑን ያስረዳል።

እንደ ቻይና፣ እስራኤልና አሜሪካ ያሉ አገራት የሰው አልባ አውሮፕላን ቴክኖሎጂን ከአገራቸው ማስወጣት እንደማይፈልጉ የሚናገረው ናኦል፤ "እኛው በራሳችን የሚያስፈልጉን መሳሪያዎች ከውጪ በማስገባትና ሰብረን ቢሆን ተምረን በአገር ውስጥ ማምረት መቻል አለብን" ይላል።

የሰው አልባ አውሮፕላን ፈጠራ አዲስና ብዙ ጠቀሜታዎች እንዳሉት የሚናገረው ናኦል፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ሰዎች ይህንን ተረድተው በዘርፉ ቢሳተፉ ኢትዮጵያ ብዙ ጥቅሞች ልታገኝ እንደምትችል ያብራራል።

ለወደፊት በሰው አልባ አውሮፕላን የእቃ ማመላለስ አገልግሎትና የግብርና ዘርፉን በሰው አልባ አውሮፕላን ቴክኖሎጂ ለመደገፍ እቅድ እንዳለው ይናገራል።

በዓለም ላይ እንደ ቦይንግ ያሉ ትልልቅ ኩባንያዎች ከእንደነዚህ ዓይነት ትንንሽ ፈጠራዎች በመነሳት ትልልቅ ነገሮችን እንደሚሠሩ የሚያስታውሰው ናኦል፤ ኢትዮጵያም በዚህ ቴክኖሎጂ ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚያስፈልጋት ይናገራል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሰው አልባ አውሮፕላንን አስመልክቶ ዝርዝር የሆነ የተቀመጠ ሕግ አለመኖሩን በመግለጽ ይህ በዘርፉ ላይ ለመሰማራት ፍላጎት ላላቸው አካላት እንቅፋት በመሆኑ እንደሚያሳስበው ያነሳል።

ከዚህ ውጪ ቴክኖሎጂ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተቀያየረ ስለሚሄድ በኢትዮጵያም ሰው አልባ አውሮፕላንና ሳተላይት በብዙ መንገድ ሊረዱ ስለሚችሉ እነዚህ ቴክኖሎጂዎችን በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ጽኑ ፍላጎት እንዳለው ለቢቢሲ ገልጧል።