ስክሪኑ የሚታጠፈው አዲሱ ሞቶሮላ ስልክ በጉጉት እየተጠበቀ ነው

ሞቶሮላ

የፎቶው ባለመብት, VCG

ከዓመታት በፊት ዝነኛም ቄንጠኛም የነበረች ስልክ ነበረች። ታጣፊዋ ሞቶሮላ። በአገር ቤት ብቻም ሳይሆን በመላው ዓለም ለቅጥነቷና ለታጣፊነቷ ሲሉ ብዙዎች ይወዷት ነበር።

ይቺ ስልክ በአዲሱ የፈረንጆች ዓመት ተመልሳ እንደምትመጣ የሞቶሮላ ኃላፊዎች ቃል ቢገቡም እርግጡን ቀን አልቆረጡላትም። ዋጋ ግን ተተምኖላታል ከወዲሁ።

ሞቶሮላ ኒውሬዘር የሚል ስም የተሰጣት ይቺ ታጣፊ የእጅ ስልክ ከድሮዋ ታጣፊ ሞቶሮላ የሚለያት ስክሪኗ እንዳልበላ አንጀት እጥፍ ዘርጋ ማለቱ ነው።

ይቺ ስልክ በተለይ አሜሪካኖች እጅግ ጓጉተው ሲጠብቋት ነበር። ተመርታ ለ'ጥብስ' ትደርሳለች የተባለውም ትናንት ዲሴምበር 26 ነበር።

ሞቶሮላ ለጊዜው ምክንያቱ ይፋ ባልሆነ ሰበብ ትንሽ ታገሱኝ ብሏል፤ ደንበኞቹን።

ታጣፊ ስክሪን ያላት ነውሬዘር ሞቶሮላ ገበያ ስትወጣ 1500 ዶላር ወይም 1170 ዩሮ ተመን ይኖራታል። በኛ ወደ 50ሺህ ብር ይጠጋል ይሄ ዋጋ።

ይቺ ስልክ ከራስጌዋ ጎንበስ ብላ ሆዷ አካባቢ ታጥፋ የቁመናዋን ግማሽ ማከል የምትችል ናት። በስልክ የሚያናግሩት ሰው ሲያናድድዎ ጆሮው ላይ ተበሳጭቶ ስልኩን ለመደርገም ምቹ ናትም ተብሏል።

ከዚህ ቀደም አገር ቤት ትታወቅ የነበረችው ሞቶሮላ ስማርትፎን አልነበረችም። አንድሮይድ ሲስተምም አልተበጀላትም ነበር። ታጣፊነቷም የተበጀላት ከብሎን ሐዲድ እንጂ ከስክሪን አልነበረም። አሁንስ?

የፎቶው ባለመብት, Bennett Raglin

የቢቢሲው ባልደረባችን ክሪስ ፎክስ ይቺን ለገበያ ያልቀረበች ቄንጠኛ ስልክ ለማየትና በዚያውም ዘገባ እንዲሰራ የሞቶሮላ ኩባንያ ለ24 ሰዓት ብቻ ስልኳን እንዲይዛት ዕድል ሰጥቶት ነበር።

እሱ እንዳስተዋለው ከሆነ ነውራዘር ሞቶሮላ ስክሪኑ ሲታጠፍ ከዋናው የስልክ ሽፋን ጋ ይላቀቃል። በስክሪኑና በሞቶሮላው መሀልም የተወሰነ ክፍተት ይታያል። ስክሪኑ ሲታጠፍ መጠነኛ ድምጽ ያሰማል።

ከዚህ ውጭ ግን ስልኳ አጓጊና በተለይ ቅንጡ ስልክ ለሚወዱ ነፍስ ናት ብሏል።

ነገሩ ከባድ ይመስላል። ስክሪን መስታወት ነው። ሞቶሮላ ታጣፊ ስክሪን ሠራ ስንል መስታወት እንዲታጠፍ አደረገ ማለታችን ነው። መስታወት ግን ይታጠፋል እንዴ?

የቢቢሲ የቴክኖሎጂ ጋዜጠኛ ዞዬ ክሌይማን እንደምትለው ከዚህ ወዲህ የስልክ አምራቾች የውድድር ሜዳ የሚሆነው ተጣጣፊነት ነው። ተጣጣፊነት ደግሞ ለሃርድዌር አምራቾች ትልቁ ፈተና ሆኖ ይቆያል። ብዙዉን ጊዜ ተጣጣፊና ቀጭን የሆነ ቴክኖሎጂ ተሰባሪነቱም ያንኑ ያህል ነው የሚሆነው ትላለች ዞዬ።

ያም ሆኖ ለዚች ለሞቶሮላ ራዘር ታጣፊ ሞዴል የታየው ጉጉት የሚነግረን ነገር ቢኖር የደንበኞች ፍላጎት ወዴት እንዳዘነበለ ነው።

አዳዲስና ታሳቢ ምርቶች በሚቀርቡባቸው የቴክኖሎጂ አውደ ርዕዮች ውስጥም ይኸው ተንጸባርቋል። ማንኛውም የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያ ቀላል፣ ዘናጭና ተጣጣፊ እንዲሆን ፍላጎት አለ። ይህን ፍላጎት ለማሟላት ደግሞ ቀላል አልሆነም። ሲሳካም ዋጋው ሰማይ ይነካል።

በዚህ ወር ኢስኮባር ኩባንያ ተጣጣፊ ስልኮችን ወደ ማምረት እገባለሁ ዋጋቸውም 349 ዶላር አይበልጥም ሲል ተናግሯል። ኢስኮባር በኮሎምቢዊው ሞገደኛ የአደገኛ እጽ አዘዋዋሪ ወንድም በፓብሎ ኢስኮባር የተቋቋመ ግዙፍ ኩባንያ ነው።