ለማርስ የተጻፈው ብሔራዊ መዝሙር

ኦስካር ካስቴሊኖ

ሕንዳዊው የቀድሞ የሶፍትዌር ባለሙያ አሁን ኦፔራ ሙዚቃ ዘንድ ስሙን የተከለ ባለሙያ ነው። ይህ ደግሞ ለማርስ ብሔራዊ መዝሙር እንዲጽፍና እንዲያቀናብር አሳጭቶታል።

ማን የብሔራዊ መዝሙር የሌለው አለ? ሀገራት? የእግር ኳስ ቡድኖች? የፖለቲካ ፓርቲዎች? የነጻነት ታጋዮች? ሁሉም ሕልማቸውን ያዘለ፣ ትግላቸውን የሳለ ብሔራዊ መዝሙር ያዘጋጃሉ።

ኦስካር ካስቴሊኖም በዩኬ ማርስ ሶሳይቲ ለቀይዋ ፕላኔት ብሔራዊ መዝሙር እንዲያዘጋጅ የቤት ስራ የተሰጠው ይህ ሁሉ ከግምት ገብቶ ነው።

ዓላማው የሰው ልጅ አንድ ቀን በፕላኔቷ ላይ መኖር ቢጀመር የራሱ የሆነ ብሔራዊ መዝሙር ያስፈልገዋል የሚል ነው።

ሰዎች ሲሰሙትም ሆነ ሲዘምሩት ይላል ኦስካር ካስቴሊኖ "ልጆቻችን፣ ልጆቻቸው ያለንን መጻኢ እድል እንዲያስቡ፣ እንዲያልሙ እፈልጋለሁ።"

ይህንን እንዲያስቡ የሚፈለገው ግን ምድርን ለቅቆ በማርስ ስለመኖር፣ ማርስን መርገጥና ማርስ ላይ መኖርን መልመድ ያለውን ውስጣዊ ትፍስህት ብቻ ሳይሆን፣ አብረው ህልምን የማሳካት ብርቱ ጥረትን እንዲያስቡም እንደሚፈለግ ይናገራል።

የብሔራዊ መዝሙሩ ግጥም እንዲህ የሚሉ ስንኞች አሉበት።

'Rise to mars men and women'

'Dare to dream Dare to strive!'

'Bulid a home for our children'

'Make this desert come alive'

ኦስካር ካስቴሊኖ ያደገው በሕንድ የሒማሊያ ተራራማ ግርጌዎች አካባቢ ነው። ባደገበት አካባቢ ከዋክብት ፍንትው ብለው ይታዩ ነበር ሲል የልጅነት ትውስታውን ለቢቢሲ አጋርቷል።

ግጥሞቹን ለመጻፍ ይህ የልጅነት ትውስታው እንደረዳው በመግለጽ ሁሌም ከከዋክብቱ ባሻገር ስልጣኔ የሚሉት ነገር ይኖር ይሆን? እንደው ሰውስ ይኖር ይሆን? ሌላ ንፍቀ ዓለምስ አለ? የሚሉ የልጅነት ጥያቄዎቹን ያስታውሳል።

ዩኬ ማርስ ሶሳይቲ፣ ማርስ በሚገባ እንድትጠናና እዚያ ሰው ልጅ ቤቱን ሰርቶ እንዲከትም የሚሰሩ ሰዎች የተሰባሰቡበት ድርጅት ነው። ኦስካር ለማርስ ብሔራዊ መዝሙር እንዲጽፍ የተነገረውም በተቋሙ መሆኑን የድርጅቱ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሮበርት ዙብሪን ይናገራሉ።

የተሳካ እንቅስቃሴ ሆኖ ብሄራዊ መዝሙር ሳይኖረው የቀረ ማን ነው? ብለው የሚጠይቁት ፕሬዝዳንቱ ሙዚቃ ነፍስን እንደሚወዘውዝ በማስታወስ መዝሙሩን ለማዘጋጀት መወሰናቸውን ይናገራሉ።

"ማርስ ላይ ደሳሳ ጎጆ ቀልሰን፣ ወልደን ከብደን መኖር ስንጀምር ትልቅ ስኬት ነው" የሚለው ኦስካር፣ በፕላኔቶች መካከል እየተመላለሱ የሚያቀርቡት ዓይነት ትርዒት ነው በማለት ስሜቱን ይገልፃል።

በምድር ያሉ በማርስ ከሚኖሩ ጋር በአንድነት የሚዘምሩት ብሔራዊ መዝሙር።

ይህ ብሔራዊ መዝሙር ስለማርስ ብቻ አይደለም። የሰው ልጅ ትልቅ እመርታን ማሳየቱን የሚያወድስ ጭምር ነው። ይህ ብሔራዊ መዝሙር ሰዎች እንዲያልሙ፣ ትልቅ እንዲያስቡና ማርስንና ከማርስ ባሻገር አሻግረው እንዲመለከቱ እንደሚያነሳሳቸው እምነት አለን ሲልም ሃሳቡን ያጠቃልላል።