በአዲስ አበባ ዙሪያ ሕገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ በአሳሳቢ ሁኔታ መጨመሩ ተነገረ

በሕገወጥ ተሰርተው እየፈረሱ ያሉ ቤቶች

በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚገኙ የኦሮሚያ ልዩ ዞኖች ውስጥ ሕገ-ወጥ የቤቶች ግንባታ አሳሳቢ በሆነ ሁኔታ እየጨመረ መምጣቱን በኦሮሚያ ክልል የመሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ኃላፊ ዶ/ር ሚልኬሳ ሚደጋ ለቢቢሲ ተናገሩ።

ኃላፊው አክለውም በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ልዩ ዞኖች እየተካሄደ ያለው ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ የፖለቲካ ፍላጎትን ተንተርሶ የሚካሄድ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

"በዚህ ሕገወጥ ቤቶች ግንባታ ላይ የተሰማሩ ሰዎች 'ሰባት ጊዜ ፈርሶ ያልተገነባ ቤት ቤት አይሆንም' የሚል ብሂል መያዛቸው የችግሩን ስር መስደድና ተደጋጋሚነት መኖር ያሳያል" ብለዋል።

በዚህም ምክንያት ግለሰቦች የሰሩት ቤት ሲፈርስባቸው መልሰው ይገነባሉ የሚሉት ኃላፊው "በሰባተኛው ይጸድቅልሀል ብለው እርስ በእርስ ይበረታታሉ" በማለት ይህም ትልቅ ፈተና እንደሆነባቸው ይናገራሉ።

ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ከአዲስ አበባ አስተዳደር የፖሊስ ኮሚሽኖች ተወጣጥቶ የተዋቀረ ግብረ ኃይል በቅርብ ቀናት ውስጥ በአዲስ አበባ እና በአዲስ አበባ ዙሪያ የተፈጸሙ ሕገ-ወጥ ግንባታዎችን ለማፍረስ እንደሚንቀሳቀስ የአዲስ አበባ ከንቲባ ጽ/ቤት ማስታወቁ ይታወሳል።

ዶ/ር ሚልኬሳ ሚደጋ በአዲስ አበባ ዙሪያ ስለሚካሄዱ ሕገ-ወጥ ግንባታዎች "በልዩ ዞኑ ሕገ ወጥ ግንባታዎችን የሚያካሄዱት ቤት አልባዎች [ዝቅተኛ ኑሮ የሚኖሩ] አይደሉም። የሕገ-ወጥ ግንባታውን እያካሄዱ ያሉት ሐብት ያላቸውና የፖለቲካ ዓላማ ያነገቡ አካላት ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ ነው" ሲሉ ይገልጻሉ።

ዶ/ር ሚልኬሳ አክለው ይህንኑ ዓላማ ለማሳካት ቀን ከሌት የሚተጉ ደላላዎችም የዚሁ የመሬት ሕገወጥ ወረራ አካል ናቸው ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ የቤተ እምነቶችን በመገንባት ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራውን የማካሄድ አንዱ አካል አድርገው የሚንቀሰሳቀሱ አካላት እንዳሉ ጨምረው ይገልጻሉ።

የምስሉ መግለጫ,

ሚልኬሳ ሚደጋ (ዶ/ር)

በኦሮሚያ ክልል የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ አንዳንድ ግለሰቦችም በጥቅም ትስስር ምክንያት ወራራው ላይ በመሳተፋቸው ችግሩን ለመፍታት እንቅፋት እንደሆነባቸው ዶ/ር ሚልኬሳ ጨምረው አስረድተዋል።

በልዩ ዞኑ ውስጥ ያሉ ነዋሪዎች በአሳሳቢ ሁኔታ እየተካሄደ ያለውን ይህንን ሕገ-ወጥ የመሬት ወረራና ሰፈራ ለመከላከል የራሳቸውን ድርሻ ካልተወጡ ጉዳዩ አሳሳቢ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።

"ለምሳሌ ለገጣፎን እንደታለፈ በሕገ-ወጥ የመሬት ወረራ የተገነባች 44 የምትባል ከተማ ተመስርታለች፤ በተመሳሳዩ በሌሎች ገጠር ከተሞችም ቀጥሎበታል" በማለት የሁኔታውን አሳሳቢነት ያብራራሉ።

ከፌዴራል ፖሊስ፣ ከኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ከአዲስ አበባ አስተዳደር የፖሊስ ኮሚሽኖች ተወጣጥቶ የተዋቀረ ሕግ አስከባሪ ግብረ ኃይል ከጥር 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሕግ ማስከበር ዘመቻውን፣ በ116 የአዲስ አበባ ወረዳዎች እንደሚጀምር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ለሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኀን መናገራቸው ይታወሳል።

የአዲስ አበባ ፖሊስ፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የኦሮሚያ ፖሊስና የአዲስ አበባ አጎራባች ከተሞችና ወረዳዎች አመራሮችን አጣምሮ የያዘው ግብረ ኃይል በተቀናጀና በተጠናከረ መንገድ ሕግ የማስከበር ዘመቻውን በመጀመር፣ ሕገ-ወጥ የመሬት ላይ ግንባታዎችን እንደሚያፀዳና በማያዳግም ሁኔታ ኃላፊነቱን እንደሚወጣ ጨምረው አስረድተዋል።