እውን ሶስተኛው የዓለም ጦርነት ይቀሰቀስ ይሆን? እና ሌሎች ጥያቄዎች ሲመለሱ

ቴህራን አደባባይ የወጡ ኢራናውያን ቁጣቸውን የአሜሪካንን ባንዲራ በማቃጠል ገልፀዋል Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ ቴህራን አደባባይ የወጡ ኢራናውያን ቁጣቸውን የአሜሪካንን ባንዲራ በማቃጠል ገልፀዋል

አርብ ታኅሣሥ 24/2012 ዓ.ም. ኢራን አለኝ የምትላቸውን የጦር ጄኔራል አሜሪካ በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት ገደለች።

ጄኔራል ሶሌይማኒ መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ የተለያዩ የጦርነት 'ኦፕሬሽኖችን' በማፋፋም ይታወቃሉ፤ ለዋሽንግተንና ቴህራን መፋጠጥም እንደ ምክንያት ይቆጠራሉ።

የቢቢሲው መከላከያና ዲፕሎማሲ ተንታኝ ጆናታን ማርከስ ዓለማችን ወደ ሶስተኛው ዓለም ጦርነት እያመራች ይሆን ወይ የሚለውን ጥያቄ ምላሽ እንዲህ አሰናድቷል።

ጉዞ ወደ ሶስተኛው የዓለም ጦርነት?

Image copyright Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ ቃሲም ሶሌይማኒ የኢራን ኩድስ ኃይል መሪ ነበሩ

የጄኔራል ቃሲም ሶሌይማኒን መገደል ብዙዎች የሶስተኛው ዓለም ጦርነት መባቻ ሲሉ ገልፀውታል። እርግጥ ነው ግድያው እንዲሁ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።

የጀኔራሉ መገደል ግን ለሶስተኛው የዓለም ጦርነት መንስዔ አይሆንም። በጀኔራል መገደል ድራማ ውስጥ ያሉት አሜሪካ እና ኢራን ብቻ ናቸው። ምናልባት ሩስያ እና ቻይና በዚህ ግርግር ውስጥ እጃቸው ገብቶ ቢሆን ኖሮ ሁኔታው አስጊ ይሆን ነበር። ነገር ግን ሩስያም ቻይናም የጀኔራሉ መገደል አያገባቸውም።

ነገር ግን የሶሌይማኒ መገደል መካከለኛው ምሥራቅን እንደሚንጥ ሳይታለም የተፈታ ነው። ኢራን የአፀፋ ምላሽ እንደምትሰጥም የታመነ ነው። ይህ ደግሞ ከአሜሪካ ሌላ ምላሽ ሊያመጣ ይችላል።

ኢራን በምላሹ የአሜሪካ ጥቅም ያለበት አካባቢን ልታጠቃ ትችላለች። በዚህ መካከል የሚፈጠረው የጦርነት ሰርግና ምላሽ አስጊ ሊሆን ይችላል።

የጀኔራሉ ግድያ ሕጋዊ ነውን?

Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ ሶሌይማኒ ኢራቅ ውስጥ ባግዳድ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ አቅራቢ ነው የተገደሉት

ዩናይትድ ስቴትስ ጀኔራሉን የገደልኩት ኢራቅ ውስጥ ለሞቱ አሜሪካውያን ወታደሮች ተጠያቂ ስለሆነ ነው ትላለች። አሜሪካ በኢራቅ መንግሥት ጥያቄ መሠረት ባግዳድ ውስጥ ወታደሮች እንዳሠፈረች አይዘነጋም።

ሶሌይማኒ የበርካታ አሜሪካውያን ደም በእጁ አለ ብላ የምታምነው አሜሪካ ጄኔራሉ የሚመሩትን የኩድስ ጦር አሸባሪ ድርጅት ስትል ትወነጅላለች። ይህ ደግሞ የሰውየው መገደል በአሜሪካ ዘንድ ሕጋዊነት እንዲላበስ ያደርገዋል።

የኖትር ዳም ሕግ ት/ት ፕሮፌሰሯ ኤለን ኦኮኔል መሰል ግድያ ሕጋዊ አግባብነት የለውም ይላሉ። «ግድያው ሕጋዊ ሊሆን የሚችለው የተባበሩት መንግሥታትን ቻርተር የተከተለና ግልፅ የሆነ ጥቃትን ለመከላከል ብቻ ሲሆን ነው።»

«ኢራን የአሜሪካን ልዑላዊነት አጥቅታ አታውቅም። አሜሪካ ሶሌይማኒ ጥቃት ያደርስብኛል ብላ በሰው ምድር መግደሏ አግባብነት የለውም። ይህ ማለት አሜሪካ ሕጋዊ ያልሆነ ግድያ ከመፈፀም አልፋ፤ ኢራቅ ውስጥ ያልተገባ ጥቃት ፈፅማለች።»

የጄኔራሉ ግድያ ትራምፕ ለፖለቲካ ጥቅማቸው ያደረጉት ይሆን?

Image copyright Reuters

እርግጥ ነው ጊዜው ትራምፕ ግድያውን የፈፀሙት ሆን ብለው ነው ብሎ ለመውቀስ አመቺ ነው። ቀጣዩ ጊዜ የአሜሪካ ምርጫ የሚካሄድበት ነውና። ወጣም ወረደ ሁኔታው ለትራምፕ ዕድልም ፈተናም ነው።

ፔንታገን ኢራቅ ውስጥ ያሉ የአሜሪካ ካምፖች ጥቃት እየደረሰባቸው ነው፤ ወደፊትም ሊደርስባቸው ይችላል ሲል ይወቅሳል። ትራምፕ በያዙት የምርጫ ዘመን ማስረገጥ የሚፈልጉት በመካከለኛው ምሥራቅ ምንም ዓይነት አሜሪካዊ ሕይወትም ሆነ ንብረት ላይ ጥፋት አለመድረሱን ነው።

ምንም እንኳ ትራምፕ ወሬያቸው ላይ ኃይለኝነት ቢስተዋልባቸውም እንዲህ ዓይነት እርምጃ ይወስዳሉ ብሎ የገመተ ያለ አይመስልም።

ኢራን የኒውክሌር መሣሪያዋን ለአፀፋ ምላሽ ትጠቀምበት ይሆን? አቅሙስ አላት?

Image copyright EPA

ኢራን የኒውክሌር መሣሪያ አቅም የላትም። ነገር ግን ኒውክሌር የማብላላት አቅሙም ችሎታውም አላት። ኢራን ሁሌም ኒውክሌር የማብላላው ለቦምብ አይደለም እንዳለች ነው።

ነገር ግን አሁን ኢራን በአውሮፓውያኑ 2015 ላይ ለተፈረመው ስምምነት አልገዛም ማለቷን ተከትሎ ምናልባትም ኒውክሌር እንደ አዲስ ማብላላት ትጀምራለች የሚል ስጋት አለ።

2015 ላይ ዩናይትድ ኪንገደም፣ ፈረንሳይ፣ ሩስያ፣ ቻይና፣ ጀርመን እና የአውሮጳ ሕብረት እንዲሁም አሜሪካ ሆነው የደረሱት ስምምነት ኢራን ኒውክሌር ማብላላቷን እንድትገታ ያስስባል።

ፕሬዝደንት ትራምፕ ስምምነቱ ከምርጫ ቅስቀሳቸው ጀምሮ ሲያጣጥሉት ከርመው ሥልጣን ከጨበጡ በኋላ ከስምምነቱ ሃገራቸውን ማግለላቸው አይዘነጋም።

ጄኔራል ሶሌይማኒ ኢራቅ ውስጥ ምን እያደረጉ ነበር?

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ ቃሲም ሶሌይማኒ (በስተግራ) 2015 በተካሄደው የአይኤስን ማጥፋት ዘመቻ ላይ የተነሱት ፎቶ

ሶሌይማኒ ኢራቅ ውስጥ ምን ሢሠሩ እንደነበር በውል አይታወቅም። ኢራን ጎረቤት ሃገር ኢራቅ ውስጥ ያሉ የሺያ ሚሊሻዎችን እንደምትደግፍ ይታወቃል። ከሶሌይማኒ ጋር የተገደሉት አቡ ማሕዲ አል-ሙሃንዲስ በአሜሪካ የጦር መንደሮች ላይ ለደረሱ ጥቃቶች ተጠያቂ የሆነው ካታይብ ሂዝቦላህ መሪ ናቸው።

በአሜሪካና ኢራን ጥል ውስጥ ኢራቅ መከራዋን እያየች ነው። የኢራቅ መንግሥት ከአሜሪካም ሆነ ከኢራን ድጋፍ ይቀበላል። ወታደሮቿ በምድሯ ጥቃት እየደረሰባት ያለው አሜሪካ ኢራቅን ትኮንናለች።

የኢራቅ መንግሥት ግድያውን ኮንኖታል። አልፎም ሟቾቹን 'መስዋዕት' ሲል ገልጿቸዋል።

ኢራንና አሜሪካ ኢራቅ ውስጥ ምን አጋጫቸው?

ኢራን የሺያ ሙስሊሙ የኢራቅ መንግሥት ወዳጅ ናት። አልፋም በተዘዋዋሪ የኢራቅን ወታደራዊ ኃይል ትዘውራለች ተብላ ትታማለች። አሜሪካ ደግሞ ኢራቅ ውስጥ 5 ሺህ ገደማ የጦር ሠራዊት አላት። ዋነኛ ዓላማቸው ደግሞ አይኤስን መዋጋትና የኢራቅ ጦርን መደገፍ ነው።

እነዚህ ሁለት የውጭ ኃይሎች ኢራቅ ውስጥ የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር መገፋፋት ከጀመሩ ሰንበትበት ብለዋል።

አሁን ዋነኛው ጥያቄ የሶሌይማኒ መገደል አሜሪካ በኢራቅ ያላትን ጥቅም የበለጠ እንድታስጠብቅ ያደርጋት ይሆን ወይ ነው።