የሊቢያ አማፂያን ቁልፍ ጠቀሜታ ያላት ከተማን ተቆጣጠሩ

የሊቢያ ወታደሮች በታንክ ላይ ሆነው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የሊቢያ አማፂያን ቁልፍ ጠቀሜታ አላት የተባለችውን የባህር ዳርቻ ከተማ ሆነችውን ሲርትን መቆጣጠራቸው ተሰማ።

ሲርት እስላማዊ አማፂያን በ2016 ከስፍራው እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው መንግሥት እጅ ነበረች።

ለጄነራል ካሊፍ ሃፍታር ታማኝ የሆኑ ወታደሮች ትሪፖሊን ለመቆጣጠር ከፍተኛ የሆነ ወታደራዊ ጥቃት እየፈጸሙ ነው።

በሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ የምትገኘው ሲርት የሚኖሩና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ግለሰብ ለሮይተርስ እንደተናገሩት በከተማዋ የጄነራል ሃፍታር ታማኝ የሆኑ አማፂያን የደንብ ልብስ የለበሱ ወታደሮች ሲንቀሳቀሱ ተመልክተዋል።

"አሁን በከተማዋ ሰፊ ስፍራን በቁጥጥራቸው ስር አድርገዋል። የተኩስ ድምጽም እየሰማን ነው" ብለዋል።

ይህ የተሰማው የቱርክ ፕሬዝዳንት ጣይብ ኤርዶጋን ጦራቸውን ወደ ሊቢያ ማንቀሳቀስ መጀመራቸውን ከተናገሩ በኋላ ነው።

በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው የትሪፖሊ መንግሥት፣ በቱርክና ኳታር የሚታገዝ ሲሆን ጄነራል ሃፍታር በበኩላቸው የግብጽ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ድጋፍ አላቸው።

የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙዓመር ጋዳፊ በህዝባዊ አብዮት እአአ 2011 ከተገደሉ በኋላ፤ ሊቢያ በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ትገኛለች።

የትኛውም ኃይል ሊቢያን ሙሉ በሙሉ አይቆጣጠረም።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

ጀነራል ካሊፋ ሃፍታር

ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር ናቸው?

ፊልድ ማርሻል ካሊፍ ቤልቃሲም ሃፍታር የአሜሪካ እና የሊቢያ ጥምር ዜግነት ያላቸው የሊቢያ ብሔራዊ ጦር የመሰረቱ እና የሚመሩ ተጽእኖ ፈጣሪ የጦር አለቃ ናቸው።

ጀነራል ካሊፍ የሊቢያ መንግሥት ከሚቀናቀኑ ሁለት ቡድኖች መካከል ከአንደኛው ጋር ጥምረት በመመስረት የትጥቅ ትግል ላይ ይገኛሉ። ጀነራሉ ከወራት በፊት ''አሸባሪዎች እና ወንጀለኛ ቡድኖች'' ባሏቸው አካላት ላይ ጥቃት መሰንዘር ጀምረዋል።

በጦር አዛዡ ጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራው ጦር በወሰደው እርምጃ ቤንጋዚ ከተማን እና በነዳጅ ሃብታቸው የበለጸጉ ደቡባዊ የሊቢያ ክፍሎችን ተቆጣጥሯል።

በሊቢያ በሚፈጸሙ ጥቃቶች ብዙ ንጹሃን ዜጎች ሕይወታቸውን ያጣሉ። በተለይ ደግሞ በመንግሥት ተቋማት እና በእስር ቤቶች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች በርካቶች የተገደሉ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለው መንግሥት በተደጋጋሚ ለሚፈጸሙት ጥቃቶች በጀነራል ካሊፍ ሃፍታር የሚመራውን ቡድን ተጠያቂ ያደርጋል።

ሊቢያ ከ8 ዓመታት በፊት በቀድሞ መሪዋ ሙአመር ጋዳፊ ላይ ተቃውሞ ከተነሳ እና ከተገደሉ በኋላ ሰላም እና መረጋጋት ርቋት ቆይቷል።