ቻይና በዚምባብዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ጠየቀች

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በዚምባብዌ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ,

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር በዚምባብዌ

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚንስትር፤ አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በዚምባብዌ ላይ የጣሉትን ማዕቀብ እንዲያነሱ ጠይቀዋል።

ሚንስትር ዋንግ ይ፤ በዚምባብዌ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ምንም ዓይነት ዓለም አቀፋዊ አግባብነት የሌለው ነው ብለዋል። ሚንስትሩ ይህንን ያሉት ዚምባብዌን እየጎበኙ ባሉበት ወቅት ነው።

"አንዳንድ ተቋማትና ሀገራት በዚምባብዌ ላይ የጣሉት ማዕቀብ ዓለም አቀፋዊ መሰረት የሌለውና የዚምባብዌን የመልማትና የማደግ መብት የሚጻረር ነው" ብለዋል ሚንስትር ይ ከብሉምበርግ ጋር በነበራቸው ቆይታ።

የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ይ ወደ ዚምባብዌ ያመሩት ቅዳሜ ሲሆን በአፍሪካ በሚኖራቸው ቆይታም አምስት አገራትን የመጎብኘት መርሐ ግብር ይዘው ነው የመጡት። ቀደም ብለው ጂቡቲ፣ ኤርትራና ግብጽን የጎበኙ ሲሆን በቀጣይ ደግሞ ቡሩንዲን ጎብኝተው የአፍሪካ ቆይታቸውን ያጠናቅቃሉ።

ዚምባብዌያዊያን የተጣለባቸውን ማዕቀብ ለማስነሳት አንዱ ግፊት የመፍጠሪያ መንገድ በማድረግ ባለፈው ጥቅምት ወር ባለስልጣናቱ ዓመታዊ በዓል እስከማዘጋጀት ደርሰው ነበር።

አሜሪካና የአውሮፓ ሕብረት በዚምባብዌ የሚታየው ዴሞክራሲ፣ የሰብዓዊ መብት አያያዝና የሚዲያ ነጻነት ከመጠን በላይ በመንግሥት ጫና ውስጥ የሚገኝ ነው በማለት ነው ማዕቀቡን የጣሉት። በማዕቀቡም ግለሰቦችንና ኩባንያዎችን ኢላማ ተደርገዋል።

አሜሪካ፤ ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋን ጨምሮ በ85 ግለሰቦች ላይ የጉዞና የፋይናንስ ማዕቀብ ጥላለች። 56 የዚምባብዌ ኩባንያዎችም ተመሳሳይ ማዕቀብ ተጥሎባቸዋል።

የአውሮፓ ሕብረትም በተመሳሳይ በግለሰቦችና በኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ ጥሏል። ማዕቀቡ በቀድሞው ፕሬዝዳንት ሙጋቤ ዘመን የተጣለ ቢሆንም አሁን ነባራዊ ሁኔታዎች መቀየራቸውን ለመገምገም በሚቀጥለው የካቲት ወር ቀጠሮ ተይዞለታል።