"ከእነርሱም ሆነ ከመንግሥት የሰማነው ድምፅ የለም" የታጋች ቤተሰቦች

ካርታ
አጭር የምስል መግለጫ ተማሪዎቹ የታገቱት ከደምቢ ዶሎ ጋምቤላ በሚወስደው መንገድ ላይ ነው

17 የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በጸጥታ ስጋት ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ከታገቱ ሳምንታት ተቆጥረዋል።

ምንም እንኳ የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ኃላፊ ታግተው ከነበሩ አብዛኞቹ ተለቀዋል ቢሉም፤ ቢቢሲ ተማሪዎቹ ስለመለቀቃቸው ምንም አይነት ማረጋገጫ ማግኘት አልቻለም።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት፤ ተማሪዎቹን ያገታቸው ማነው? ከተለቀቁ የት ነው የሚገኙት? ከወላጆቻቸው ጋር ለምን እንዲገናኙ አልተደረገም? ለሚሉ እና ለሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ ስላልሰጡ፤ የጉዳዩ አወዛጋቢነት እንደቀጠለ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ ከቀናት በፊት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ታግተዋል ያሉት የተማሪዎች ቁጥር እና የፌደራል መንግሥት ከእገታው አስልቅቄያለሁ የሚለው ቁጥር ልዩነት፤ በመንግሥት መካከል በራሱ የመረጃ መጣረስ መኖሩን ያሳያል የሚሉ በርካቶች ናቸው።

የመለቀቃቸው ዜና ከመሰማቱ በፊት

ትናንት ያነጋገርነው እህቱ የታገተችበት ወንድም የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በገና ዋዜማ ላይ በሰጡት መግለጫ፤ የታገቱ ተማሪዎች ቁጥር አራት ናቸው ማለታቸውን ተከትሎ፤ መረጃው ስህተት መሆኑን ስለተረዳ ወደ ቢሯቸው አቅንቶ እንደነበር ያስታውሳል።

ወደ ቢሯቸው አቅንቶ እርሳቸውን ባያገኝም "አማካሪያቸው" ላሉት ግለሰብ የተማሪዎቹን ስምና የሚማሩበትን የትምህርት ክፍል ዝርዝር የሚያሳይ ማስረጃ መስጠቱን ይናገራል። "የሰጠናቸው መረጃ ይድረሳቸው፤ አይድረሳቸው ግን አላወኩም" ብሏል።

መረጃውን ለሚመለከታቸው ሌሎች አካላትም እንደሰጡ ይናገራል።

ጃል መሮ ከህወሃት ጋር እየሠራ ነው?

ልጃቸው የታገተችባቸው አባት ደግሞ ከታገቱት 17 የደንቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አንዷ የበኩር ልጃቸው እንደሆነች ይናገራሉ።

ድምጿ ከጆሯቸው ከራቃቸው ሳምንታት አልፈዋል። ልጃቸው በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነበረች።

በትምህርት ምክንያት ከእነርሱ ከራቀች ጀምሮ ያሉበት አካባቢ የስልክ ኔትወርክ ችግር ቢኖርም፤ ቢያንስ በየሦስት ቀኑ በስልክ ይገናኛሉ፤ ቢበዛ በሳምንት ደህንነታቸውን ይጠያየቃሉ። ትንሽ ሰንበት ካለች ይጨንቃቸዋል።

አሁን ግን ድምጿን ከሰሙ ሳምንታት አልፈዋል። የገባችበትን፣ የደረሰችበትን አለማወቃቸውም ግራ አጋብቷቸዋል።

ወደ ደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተመድባ ስትሄድ አላደረሷትም። ከጓደኞቿ ጋር ነበር የሄደችው።

ይሁን እንጅ መታገታቸውን ኅዳር 24 ቀን 2012 ዓ.ም ከሰሙ በኋላ በማግስቱ የተሰወረችባቸውን ልጃቸውን ለመፈለግ ከተማ አቆራርጠው ደምቢ ዶሎ ሄደው ነበር።

እዚያ እንደደረሱ የሚያደርጉት ግራ ቢገባቸውም በቀጥታ ወደ ዩኒቨርሲቲው ማምራታቸውን ይናገራሉ። ከዚያም ወደ ኮማንድ ፖስት በመሄድ እንዳነጋገሯቸው ያስረዳሉ።

"ችግር የለም፤ 'ልጆቹን በድርድር እናስለቅቅላችኋለን' እያሉን ሁለት ሦስት ቀን እዚያው ደንቢ ዶሎ ከተማ አደርን" ይላሉ።

በኋላ ላይ "እናንተንም ከባድ እርምጃ እንዳይወስዱባችሁ አገራችሁ ግቡ፤ እኛ ልጆቹን አፈላልገን እናመጣለን" እንዳሏቸውና የስልክ ቁጥራቸውን ተቀብለው እንደተመለሱ ያስታውሳሉ።

ምን ላይ እንደደረሱ ስልክ እየደወሉ ቢጠይቋቸውም የሚነግሯቸው አዲስ ነገር አልነበረም። የመጀመሪያዎቹ ሳምንታት ልጃቸውም በራሷ ስልክ እንዲሁም "የአጋቾቹ" ነው ባለችው ስልክ ትደውልላቸው ነበር።

እኚህ አባት " ዩኒቨርሲቲውን ሳየው ጫካ ውስጥ ነው፤ አጥር የለውም፤ መንግሥት ራሱ እንዴት አድርጎ ልጆቻችንን እንደሚያስተምራቸው ተገርሜ ነው የመጣሁት" በማለት ቀድመው ቢያውቁ ኖሮ ወደ ዩኒቨርሲቲው እንደማይልኳት በቁጭት ይናገራሉ።

የመለቀቃቸው ዜና ከተሰማ በኋላ

ቢቢሲ ያነጋገረው የታጋች ወንድም ቅዳሜ ዕለት የተላለፈው የተማሪዎቹን መለቀቅ ዜና ከሰማ በኋላ ገጠር ለሚኖሩት ቤተሰቦቻቸው ደውሎ ነግሯቸዋል።

"አትጨነቁ ተለቀዋል እየተባለ ነው፤ በእርግጥ ያልተለቀቀም አለ እያሉ ነው፤ ግን አትጨነቁ" ሲል ነበር ደውሎ ያበሰራቸው።

እርሱ እንደሚለው አለመደወሉ ብቻ እንጅ እስካሁን እንደተገኙ ነው የሚያስቡት፤ በዜናውም እጅግ ተደስተው ነበር።

እርሱም በበኩሉ ዜናውን የሰማ ቀን ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶት ነበር። ወደ ስልኳም ደውሏል፤ ግን ስልኳ አይሰራም።

በተደጋጋሚ ቢደውልም እስካሁን ድምጿን መስማት አልቻለም።

ኦባማ፡ ሴቶች ከወንዶች የተሻሉ ናቸው

በቄለም ወለጋ ዞን የደህንነት ባለሙያ በታጣቂዎች ተገደሉ

የጠቅላይ ሚንስትር ጽ/ቤት ኃላፊ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ቀርበው ከታገቱት መካከል አብዛኞቹ መለቀቃቸውን ከተናገሩ በኋላ "በደስታ ፈነጠዝኩ! ቤተሰቡ ሁሉ ተደሰተ።" ያሉን ደግሞ ልጃቸው የታገተችባቸው አባት ናቸው። እንዲህ ነበር ያወጉን፦

እኛ ገጠር ነው የምንኖረው ቴሌቪዥንም የለን፤ ባህር ዳርና ሌሎች ከተሞች የሚኖሩ የታጋች ቤተሰቦች ናቸው እየደወሉ የነገሩን።

መልዕክቱ ከተላለፈ በኋላ ልጆቻችን በእጃችን ሊገቡ ነው ብለን ተደስተን ነበር።

ሰሞኑን ግን መንግሥት ድምጻቸውን ስላላሰማን እየተጨናነቅን ነው።

አርሶ አደሮች ነን፤ በጭንቀት ሥራ መሥራት አልቻልንም፤ ወደ ቤት ስሄድም ሆነ አንዳንድ ቦታም ወጣ ስል የሰማው ሰው በሙሉ ለቅሶ ነው። "እንዴት ነው? ድምጿን አልሰማችሁም ወይ? መቼ ነው የሚመጡት?" እያሉ ይጠይቃሉ።

እኛ ግን ምንም መልስ የለንም። ቁርጡን ስላላወቅነው ሁልጊዜ ለቅሶ ላይ ነው ያለነው። እስካሁን ምንም የሰማነው ድምፅ የለም።

ከቤተሰብ ባገኘነው መረጃ መሠረት ታግተው ያሉ ተማሪዎች ስምና ይማሩበት የነበረው ትምህርት ክፍል ዝርዝር የሚከተለው ነው፦

 • በላይነሽ መኮንን ደምለው - ኢኮኖሚስት 1ኛ ዓመት
 • ሳምራዊት ቀሬ አስረስ - ጋዜጠኝነት 2ኛ ዓመት
 • ዘውዴ ግርማው ፈጠነ - ኢኮኖሚክስ 3ኛ ዓመት
 • ሙሉ ዘውዴ አዳነ - ሳይኮሎጅ 2ኛ ዓመት
 • ግርማቸው የኔነህ አዱኛ - ባዮሎጅ 3ኛ ዓመት
 • ስርጉት ጌትነት ጥበቡ- ተፈጥሮ ሳይንስ 1ኛ ዓመት
 • ትዕግስት መሳይ መዝገቡ - 12ኛ ክፍል ተማሪ (የአካባቢው ተማሪ)
 • መሠረት ከፍያለው ሞላ- ተፈጥሮ ሳይንስ 3ኛ ዓመት
 • ዘመድ ብርሃን ደሴ- ተፈጥሮ ሳይንስ 3ኛ ዓመት
 • ሞለሞን በላይ አበበ- ጋዜጠኝነት 3ኛ ዓመት
 • ጤናዓለም ሙላቴ ከበደ- አግሪ ሳይንስ 2ኛ ዓመት
 • እስካለሁ ቸኮል ተገኘ- ኬሚስትሪ 3ኛ ዓመት
 • አሳቤ አየለ አለም- ቬተርናሪ ሳይንስ 3ኛ ዓመት
 • ቢተውልኝ አጥናፍ አለሙ - ኮምፒዩተር ሳይንስ 3ኛ ዓመት
 • ግርማው ሐብቴ እማኘው- መካኒካል ኢንጅነሪንግ 3ኛ ዓመት
 • አታለለኝ ጌትነት ደረሰ- ተፈጥሮ ሳይንስ 1ኛ ዓመት
 • ክንዳየሁ ሞላ ገበየሁ- ተፈጥሮ ሳይንስ 1ኛ ዓመት

የመንግሥት አካላት ምላሽ

ጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት

ቢቢሲ የተማሪዎቹን መታገት ከሰማበት ጊዜ አንስቶ የተለያዩ የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊዎችን ለማግኘት ጥረት እያደረገ ነው። ይሁን እንጅ የተሰጠው ምላሽ የለም።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፤ ዝርዝር መረጃ እንዲሰጡን በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸው ባለመነሳቱ ልናገኛቸው አልቻልንም።

አማራ ክልል

የአማራ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌትነት ይርሳውን፣ የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገርን ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረግነው ሙከራ ምላሽ አላገኘም።

የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከሳምንት በፊት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ፤ "አራት ተማሪዎች ታግተው እንደሚገኙ መረጃው አለኝ" ማለታቸው ይታወሳል።

ታግተው የሚገኙት ተማሪዎች ከወላጆቻቸው ጋር በስልክ አልፎ አልፎ እንደሚገናኙ ጭምር ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳደሩ ተማሪዎቹ ተለቀው ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲቀላቀሉ ከአባ ገዳዎች፣ ከአካባቢው ማኅበረሰብ እና ከሚመለከተው የመንግሥት አካል ጋር ውይይት እያደረግን ነው ብለው ነበር።

ከዚያ በኋላ ግን ያሉት ነገር የለም።

ኦሮሚያ ክልል

ስለታገቱት ተማሪዎች በድጋሜ የጠየቅናቸው የኦሮሚያ ክልል የአስተዳደር እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኮሎኔል አበበ ገረሱ ጋር ያደረግነው የስልክ ልውውጥ የሚከተለው ነው፦

ታግተው የነበሩና አሁን ተለቀቁ ስለተባሉ ተማሪዎች ለመጠየቅ ነው ደወልኩት

ኮሎኔል አበበ፡ "አላውቅም፤ እኔ የሰማሁት ነገር የለም"

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት በሰጠው መግለጫ አብዛኞቹ መለቀቃቸውን ሰምተናል። በእናንተ በኩል የምታውቁት ምንድን ነው ?

ኮሎኔል አበበ፡ ለምን እነርሱን አትጠይቋቸውም ?

እርስዎም ለአንድ ዓለም አቀፍ ሚዲያ ተማሪዎቹ በመንግሥት እጅ እንደሚገኙ ገልፀዋል። ምንድን ነው ያለው እውነት?

ኮሎኔል አበበ፡ታዲያ እርሱን ለምን አትጠቀሚም

ተጨማሪ ጥያቄዎች ስላሉኝ ነው. . .

ኮሎኔል አበበ፡ እሽ 8፡00 ሰዓት ደውይ፤ አሁን ሥራ ላይ ነኝ ከዚያ በኋላ በተደጋጋሚ ብንደውልም የእጅ ስልካቸውን ሳያነሱልን ቀርተዋል።

የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ዴሬሳ ተረፈ በበኩላቸው ታፍነው የተወሰዱ ተማሪዎች የሉም፤ "ታፍኖ የተወሰደ ተማሪ የለም" ከማለት ውጪ ማብራሪያ መስጠት አለመፈለጋቸውን ከዚህ በፊት መዘገባችን ይታወሳል።

ማን ምን አለ?

ተማሪዎቹ ከታገቱ በኋላ መንግሥት ተማሪዎቹን ለማስለቀቅ የወሰደው እርምጃ የለም በማለት በርካቶች የተቃውሞ ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።

ከእነዚህ መካከል የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ፓርቲ (አብን) ባወጣው መግለጫ የታገቱ ተማሪዎች እንዲለቀቁ እና ጥቃት አድራሾቹ ለሕግ እንዲቀርቡ መጠየቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ዛሬ በገፁ ላይ ባወጣው መግለጫም፤ የታገቱት ተማሪዎች ምንም ዓይነት ጉዳት ሳይደርስባቸው እንዲለቀቁ መንግሥት የሚጠበቅበትን ኃላፊነት በአስቸኳይ እንዲወጣ መጠየቁ ይታወቃል።

የአማራ ክልል ሴቶች ፌደሬሽን በተማሪዎቹ ላይ እየተፈፀመ ያለውና ኢ-ሰብዓዊ ተግባራት እንዲቆሙ፤ ጥፋተኞችም ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል።

የአማራ ሴቶች ፌደሬሽንና እና የአማራ ሴቶች ማህበር ዛሬ በሰጡት መግለጫም የደምቢ ዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ላይ ያለውን አቋም መንግሥት ግልፅ ማድረግ እንዳለበት ጠይቀዋል።

የአማራ ዴሞክራሲ ኃይል ንቅናቄ (አዴኃን) በተማሪዎቹ ላይ የተፈፀመውን ድርጊት አውግዞ፤ ይህ የመንግሥት ችግር እንደሆነ እንደሚያምን ገልጿል።

'የታገቱት ተማሪዎች ይለቀቁ' የሚል ዘመቻም በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተካሄዱ ነው፤ መንግሥት መፍትሄ እንዲሰጥም እየተጠየቀ ነው።

የጠቅላይ ሚንስትሩን ካቢኔዎች 50 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን በማስታወስ፤ በደህንነት ስጋት የዩኒቨርሲቲ ግቢ ለቀው ወደ ትውልድ ቀያቸው ሲያመሩ የታገቱ ሴት ተማሪዎች ትኩረት አለማግኘት በመጥቀስ ብስጭት አዘል አስተያየቶች አሁንም እንደቀጠሉ ናቸው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ