የሱዳን ሽግግር መንግሥት ወታደሮች ከአል-ባሽር ታማኞች ጋር ተጋጩ

የሱዳን ወታደሮች ከአል-ባሽር ታማኞች ጋር ተጋጩ Image copyright AFP

የሱዳን ጦር ሠራዊት ከቀድሞው ፕሬዝደንት ኦማር አል-ባሽር ታማኝ ወታደሮች ጋር ተጋጭቷል።

ማክሰኞ ረፋዱ ላይ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የተኩስ እና ፍንዳታ ድምፆች ተሰምተዋል። ምክንያቱ ደግሞ ወታደራዊው ኃይል 'ጀኔራል ኢንተለጀንስ ሰርቪስ' የተሰኘውን የስለላ መሥሪያ ቤት መክበብ ነበር።

ምንም እንኳ በመሥሪያ ቤቱ የሚሠሩ ሰዎች ከደመ-ወዝ ክፍያ ጋር በተያያዘ ቅሬታ ነበራቸው፤ እሱን ለማርገብ የተወሰደ እርምጃ ነው ቢባልም በሱዳን በቅርቡ የተከናወነውን ለውጥ ለማደናቀፍ የተደረገ ሙከራ አድርገውም የቆጠሩት አሉት።

የሽግግር መንግሥቱ አባል የሆኑት ጀኔራል ሞሐመድ ሐማድ ዳጋሎ [ሐሜቲ] የቀድሞውን የስለላ መሥሪያ ቤት ዋና ኃላፊ ሳላህ ጎሽ ብጥብጡን አቀሳስረዋል ሲሉ ይወቅሳሉ።

ጄኔራሉ ድርጊቱ መፈንቅለ-መንግሥት ነው ባይባልም የምንታገሰው አይደለም ብለዋል።

የሱዳን ለውጥ በኦማር አል-ባሽር ታማኝ አገልጋዮች እንዳይደናቀፍ ስጋት አለ። ተንታኞች፤ ሕዝቡ ለውጡን ይፈትናሉ ብሎ የሚያስበው በፊት ጠንካራ እጅ የነበራቸው የባሽር ሰዎች ናቸው ይላሉ።

የስለላ መሥሪያ ቤቱ ወታደሮች ማህበራዊ ድር-አምባ ላይ የለጠፏቸው ተንቀሳቃሽ ምስሎች ከባድ የጦር መሣሪያዎች ወደ ሰማይ ሲተኮሱ ያሳያሉ።

ሮይተርስ የተሰኘው የዜና ወኪል ያነጋገራቸው ነዋሪዎች በሰሜኑ የካርቱም ክፍል ተኩስ እና ፍንዳታ ሰምተናል፤ የቀድሞ ወታደሮች አውሮፕላን ማረፊያው አካባቢ ያለ ሕንፃ ይዘው አለቅ ማለታቸውን አይተናል ይላሉ።

ኤኤፍፒ የተሰኘው የዜና ወኪል ደግሞ አምስት ሰዎች በግርግሩ ምክንያት ቆስለዋል ሲል ዘግቧል።

ለሰዓታት ከቆየ ግርግር በኋላ የመንግሥት ወታደሮች በቀድሞ የባሽር ታማኝ አገልጋዮች ተይዘው የነበሩ ሕንፃዎችን በቁጥጥራቸው ሥር ማዋላቸው ተዘግቧል።

የሱዳን ተቃውሞ ቀኝ እጅ የነበረው እንቅስቃሴ እንዲህ ዓይነት ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች ሕብረተሰቡ ላይ ሽብር ይነዛሉና ጥንቃቄ ይደረግባቸው ብሏል።

ባለፈው የፈረንጆቹ ዓመት ለወራት የዘለቀው አል-ባሽርን ለመጣል የተደረገው እንቅስቃሴ የ170 ሱዳናውያንን ሕይወት ቀጥፏል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ