የቱርካዊው የእግር ኳስ ኮከብ ጉዞ ከታዋቂ ፖለቲከኛነት እስከ ታክሲ ሹፌርነት

የቱርካዊው የእግር ኳስ ኮከብ ጉዞ ከታዋቂ ፖለቲከኛነት እስከ ታክሲ ሹፌርነት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ሃካን ሱኩር በቱርክ እግር ኳስ ታሪክ በርካታ ጎሎችን ያስቆጠረ ተጫዋች ነው። እስካሁንም የሚድርስበት አልተገኘም። በአንድ ወቅት በአውሮጳ እግር ኳስ አሉ ከሚባሉ ተጫዋቾችም አንዱ ነበር።

አሁን ግን አሜሪካ ውስጥ የታክሲ ሹፌር ሆኗል፤ መፃሕፍትም ይሸጣል። እንዴት?

ከአንድ የጀርመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረገው የ48 ዓመቱ ሳኩር ሕይወቱ ባልተጠቀ መንገድ እንዴት እንዲህ ሊሆን እንደቻለ ያስረዳል።

ሱኩር፤ ከቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶዋን ጋር ያለኝ ቅራኔ ነው ለዚህ ያበቃኝ ይላል። ከእንገድልሃለን ማስፈራሪያ ጀምሮ እስከ ገንዘብ ክልከላ ድረስ የዘለቀ እርምጃ እንደተወሰደበት ይዘክራል።

«ምንም ነገር የለኝም። ኤርዶዋን ሁሉን ነገር ወስዶብኛል። ነፃነቴን ገፎኛል። ሃሳቤን ነፃ ሆኜ መግለፅ ተሳነኝ፤ ሠርቼ መብላት አልቻልኩም።»

በፈረንጆቹ ከ92-2007 ባለው ጊዜ ሳኩር ለቱርክ 112 ጊዜ ተሰልፎ የተጫወተ ሲሆን 51 ጎሎችን አስቆጥሯል። ቱርክ በ2002 የዓለም ዋንጫ ሶስተኛ ስትወጣ የቡድኑ አባል ነበር።

ለእንግሊዙ የእግር ኳስ ክለብ ብላክበርን ይጫወት የነበረው ሱኩር፤ የእግር ኳስ ሕይወቱን አብዛኛውን ጊዜ ያሳለፈው ጋላታሳራይ ለተሰኘው የቱርክ ክለብ በመጫወት ነበር።

ሱፐር ሊግ በመባል በሚታወቀው የቱርክ እግር ኳስ ሊግ እንደ ሱኩር ብዙ ጎል ያገባ እስካሁን አልተገኘም።

ሱኩር ጫማ ሲሰቅል ወደ ፖለቲካ ገባ። በግሪጎሪያን አቆጣጠር 2011 ላይ ምርጫ የኤርዶዋንን ፓርቲ ወክሎ ተዋዳድሮ በማሸነፉ በላይኛው ምክር ቤት የሕዝብ እንደራሴ ለመሆን በቃ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ነገር ግን ፌቱላህ ጉሌን ከተሰኘው የኤርዶዋን ዋነኛ ተቀናቃኝ ድርጅት ጋር ተያይዞ ስሙ ይነሳ ነበር። የቱርክ መንግሥት ደግሞ 2016 ላይ ለተከሰተውና በርካታ ሰዎችን ለቀጠፈው የቱርክ የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ ድርጅቱን ተጠያቂ ያደርጋል።

ሱኩር በወቅቱ አሜሪካ ነበር። የመፈንቅለ-መንግሥት ሙከራውንም አጣጥሏል። ነገር ግን የቱርክ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተጨዋቹ የፌቱላህ አባል ነው፤ አሁን በጥገኝነት አሜሪካ ይገኛል ሲል ዘገበ።

ዘገባው ሱኩር፤ ሳን ፍራንሲስኮ በተሰኘችው የአሜሪካ የሃብታሞች ከተማ 3 ሚሊዮን ዶላር በሚያወጣ ቤት ውስጥ ይኖራል፤ የራሱ ካፌም አለው ሲል አተተ።

«እርግጥ ነው ካሊፎርኒያ ውስጥ ካፌ ነበረኝ። ነገር ግን የማላውቃቸው ሰዎች ካፌዬን መጎብኘት ጀመሩ። አሁን የኡበር ሹፌር ነኝ።»

ቱርክ ውስጥ ያሉ ቤቶቹ፣ ቢዝነሶቹም ሆኑ የባንክ አካውንቶቹ በኤርዶዋን መንግሥት እግድ እንደተጣለባቸው ይናገራል። የመንግሥትን ወቀሳም ያጣጥላል።

ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት ኒው ዮርክ ታይምስ ከተሰኘው ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረገው ሱኩር «ሃገሬን እወዳለሁ፣ ሕዝቡን እንዲሁ። ምንም እንኳ ስለኔ ያላቸው አተያይ የተጣመመ ቢሆንም» ብሏል።

በወቅቱ ዘገባው የኤርዶዋን መንግሥትን ጨቋኝነት ያሳያል በሚሉ ሰዎች ዘንድ ትኩረት አግኝቷል።

2018 ላይ የአርሴናሉ አማካይ ሜሱት ኦዚል ከፕሬዝደንት ኤርዶዋን ጋር ፎቶ በመነሳቱ ነቀፌታ አስተናግዶ ነበር። ኤርዶዋን፤ ኦዚል ሲሞሸር ሚዜው ሆነው መታየታቸውም አይዘነጋም።