ምርጫውን ነሃሴ 10 የማካሄድ ሃሳብ ቅሬታ ተነሳበት

የምርጫ ቦርድ ውይይት

የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የዘንድሮው ምርጫ የድምፅ መስጫ ቀን ነሃሴ 10/2012 እንዲሆን ሃሳብ አቅርቧል።

ቦርዱ የድምፅ መስጫ ቀንና ሌሎች ከምርጫ ጋር የተገናኙ ክስተቶች የሚከወኑበትን የጊዜ ሰሌዳ ለውይይት ክፍት አድርጓል።

ቦርዱ፤ የፓለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት አስተያየትና ግብዓት እየሰጡበት የሚገኝ ሲሆን፤ በውይይቱ እየተሳተፉ የሚገኙት ባለድርሻ አካላት ምርጫው በነሃሴ ወር እንዲካሄድ መታቀዱ ትክክል አይደለም ብለዋል።

ከታኅሣሥ 22 ጀምሮ እስከ መጋቢት መባቻ ድረስ የክልል ምርጫ ቢሮዎች የሚደራጁበት ነው ተብሏል።

ከመጋቢት 29 እስከ ሚያዚያ 28 ያለው የአንድ ወር ጊዜ ለመራጮች ምዝገባ ሊውል እንዲሚችል ቦርዱ ያወጣው ፍኖተ ካርታ ያሳያል። ከሚያዚያ አጋማሽ እስከ 26 ባለው ጊዜ ደግሞ ዕጩዎች ይመዘገባሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች በይፋ የምረጡን ዘመቻቸውን የሚጀምሩት ሚያዚያ 27 ሲሆን፤ ነሃሴ 05 ደግሞ የማብቂያ ጊዜ እንዲሆን ሃሳብ ቀርቧል።

የምርጫው ቅድመ ውጤት ከድምፅ መስጫው ቀን ማግስት ነሃሴ 11-15 ባለው ጊዜ ይፋ እንደሚሆን የቦርዱ ረቂቅ ሰሌዳ ያሳያል። እስከ ነሃሴ ባለው ጊዜ የቦርዱ የተረጋገጠበት ውጤት ማሳወቂያ ጊዜ ነው ተብሏል።

ቦርዱ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ላይ ተወያይቶ ውሳኔ እንደሚያሳልፍ ይጠበቃል።

በተሳታፊዎች የተሰጡ አስተያየቶች

ነሃሴ ወር ክረምት መሆኑን ተከትሎ ምርጫውን ማካሄድም ሆነ መራጮች ድምጽ ለመስጠት ከባድ ያደርግባቸዋል የሚሉ አስተያየቶች ተነስተዋል።

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ት ብርቱኳን ሚደቅሳ በበኩላቸው በተቋሞች ላይ በተደረጉ ለውጦች ምክያት ምርጫውን በግንቦት ማካሄድ ከባድ አድርጎታል ብለዋል።

የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ፤ ከብሔራዊ ሜትሮሎጂ የአየር ትንበያዎችን ተቀብለው ከረቂቅ የጊዜ ሰሌዳው ጋር እንደሚያጠናቅሩትና በክረምት ወቅት ለመኪኖች አስቸጋሪ በሆኑት መንገዶች ላይ የሃገር መከላከያ ሠራዊት መኪኖችን መጠቀም እንደሚቻል ጠቁመዋል።

ወ/ት ብርቱኳን ምርጫውን በቀጣዩ ዓመት መስከረም ወይም ጥቅምት ወራት ላይ ማድረግ ሕጋዊ ስለማይሆን ወደፊት ማራዘም እንደማይቻል ተናግረዋል።

ኢዜማን ወክለው በውይይቲ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ ዋሲሁን ተስፋዬ "የእጩ ምዝገባ ለ13 ቀናት ብቻ መደረጉ በጣም ያንሳል ብለዋል"።

የምርጫ ቦርድ ረቂቅ የጊዜ ሰሌዳ የእጩዎች ምዝገባ ከሚያዚያ 13-ሚያዚያ 26 እንደሚካሄድ አስቀምጧል።

ወ/ት ብርቱኳን ግን ለእጩዎች ምዝገባ 13 ቀናት በቂ መሆናቸውን ገልጸው፤ ተጨማሪ ጊዜ የሚያስፈልግ ሆኖ ከተገኘ የጊዜ ሰሌዳውን ዳግም መመልከት እንደሚችሉ ተናግረዋል።

ኦነግን ወክለው በውይይቱ ላይ የተሳተፉት አቶ ቀጄላ መርዳሳ በበኩላቸው "በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍል ውስጥ የደህንነት ችግር አለ። ብዙ ቦታዎች በኮማንድ ፖስት ሥር ነው እየተዳደሩ ያሉት" በማለት የደህንነት ጉዳይ አስጊ መሆኑን ጠቁመዋል።

ከኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ የመጡት አቶ ሙላቱ ገመቹ ደግሞ፤ ቦርዱ የምርጫ አስፈጻሚዎችን ማንነት ይፋ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ት ብርቱኳን ለጥያቄዎቹ ምላሽ ሲሰጡ፤ "መንግሥት ኃላፊነቱን እንዲወጣ እናሳውቃለን። የፖለቲካ ፓርቲዎች ችግር በሚያጋጥማቸው ወቅት የገጠማቸውን ችግር ለመቅረፍ ስንሰራ ነበር። አሁንም ቢሆን እራሱን የቻለ 'ዴስክ' በማቋቋም የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚገጥሟቸውን ችግሮች ለመቅረፍ እንሰራለን" ብለዋል።

ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ የሆኑት አቶ ልደቱ አያሌው ሃገሪቱ ጨርሶ ምርጫ የማካሄድ ቁመና ላይ አይደለችም ብለዋል።

አቶ ልደቱ ሀሳባቸውን ሲያስረዱ "የመጀመሪያው ህዝቡ ከአምባገነናዊ ስርዓት ወደ መዋቅራዊ ስርዓት ለመሸጋገር የጠየቃቸው ጥያቄዎች ገና አልተፈቱም። እኚህ ጥያቄዎች ደግሞ በምርጫ ምላሽ የሚያገኙ አይደሉም። በድርድር የሚፈቱ ናቸው። በብሔራዊ መግባባት የሚፈቱ ናቸው። ይህን ሳንፈታ ወደ ምርጫ መግባት ወደ ቅድመ 2010 ነው የሚወስደን" ብለዋል።

"ሰላም እና የሕግ የበላይነት በሌሉበት ሁኔታ ነጻ እና ፍትሃዊ ምርጫ ማካሄድ አይቻልም። ህዝብ መቁጠር ያልቻለ መንግሥት እንዴት አድርጎ ነው ምርጫ ማካሄድ የሚችለው?" ሲሉም ይጠይቃሉ።

የቦርዱ ሰብሳቢ ለአቶ ልደቱ ጥያ ምላሽ ሲሰጡ፤ አቶ ልደቱ ያነሷቸው ስጋት አዘል ጥያቄዎች ምርጫ ቦርድን እንደማይመለከት ተናግረዋል።

"ምርጫ ማካሄድ ግዴታ ነው። ጉድለቶች ቢኖሩም ኃላፊነት ወስደን እናስፈጽማለን። በአዋጅ የተጣለብንን ግዴታ ነው የምናስፈጽመው" ብለዋል።

"ይሁን እንጂ መሳሪያ እየተተኮሰ ሰዎች ድምጻቸውን ይስጡ አንልም። የሚኖሩ የጸጥታ ችግሮችን ለመንግሥት እናሳውቃለን። ፖለቲካ ፓርቲዎችም ደጋፊዎቻቸው ስለ ሰላም ማስገንዘብ ይኖርባቸዋል"

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ደግሞ፤ ምርጫውን የሚታዘቡት ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች እነማን ናቸው ብለው ላቀረቡት ጥያቄ፤ ወ/ት ብርቱኳን፤ "አውሮፓ ሕብረት ምርጫውን እንዲታዘብ ጥሪ ቀርቦለታል። እነሱም በቅርቡ ምላሻቸውን ያሳውቁናል" ብለዋል።

በሌላ በኩል ገዢውን ፓርቲ ወክለው በውይይቱ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት አቶ አለሙ ስሜ፤ ፓርቲያቸው ቦርዱ ባቀረበው የምርጫ ሰሌዳ እንደሚስማማ ተናግረዋል።

አቶ አለሙ "የጊዜ ሰሌዳው አግባብ ነው። ሰኔ እና ሐምሌ አርሶ አደሮች ሥራ የሚበዛባቸው ወራት ስለሆኑ ሐምሌ ላይ እንዲካሄድ መደረጉ ትክክል ነው፤ እኛም እንስማማበታለን" ብለዋል።

አቶ አለሙ "ከውጪ ሆኖ የሃገራችንን ሰላም የሚነሳ የለም። እየረበሹ ያሉት ሃገረ ውስጥ ያሉት ናቸው። . . . መንግሥት ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚጠበቅበትን ይወጣል" ካሉ በኋላ "ሃገራችንን አረጋግተን ምርጫውን እናስፈጽም'' በማት ጥሪ አቅርበዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ