የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ወተታቸውን ሊከላከሉ ነው

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ Image copyright AFP
አጭር የምስል መግለጫ የኬንያው ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ

ኬንያ ከ'ምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ' ውጭ የሚመጣን ወተት በተለየ መንገድ ነው የማያው ብላለች።

በአገር ውስጥ ያሉትን የወተት አምራቾቼን ገበያ እያሳጣና ተስፋ እያስቆረጠ ስለሆነ ከምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ውጭ ተመርቶ ወደ ኬንያ የሚገባውን የወተት ምርት 16 በመቶ ግብር በማስከፈል ማሽመድመድ እፈልጋለሁ እያለች ነው።

የሚገርመው ነገር ግን ይህ የማስፈራሪያና የዛቻ መግለጫ የተሰጠው በፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ አማካኝነት መሆኑ ነው። እርሳቸው ደግሞ ኬንያ ውስጥ 'የወተት ንጉስ' ናቸው። አብዛኛው ኬንያዊ የኡሁሩ ኬንያታ ወተት ጠጭ ነው። "ብሩክሳይድ ዴይሪስ" የተሰኘው የእርሳቸው ቤተሰብ የወተት ምርት ኬንያ ውስጥ ትልቁና በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ የሆነው ነው።

ፕሬዝዳንቱ ታዲያ "አላማዬ በወተት ገበያው መካከል ላይ የሚገቡ ደላሎችን ከጨዋታ ውጭ በማድረግ የአምራቾችን ኪስ ማፈርጠም ነው" ብለዋል። በዚህ መሃል እርሳቸው ቀዳሚ የእርምጃው ተጠቃሚ መሆናቸውን ባይናገሩም ከውጭ የሚመጣው ወተት በግብር ምክንያት ከገበያ ውጭ ሲደረግ የእርሳቸው ምርት የአገሪቱን ገበያ እንደሚቆጣጠር ግልጽ ነው።

ርምጃው ለዘርፉ 10 ሚሊዮን ዶላር ተጨማሪ በጀት መመደብንም ይጨምራል። ይህ ገንዘብ በዋናነት ለብሔራዊ ወተት አቀናባሪው ማሕበር የሚሰጥ ሲሆን በገንዘቡ ከአምራቾች ከፍተኛ ወተት ገዝቶ ወደ ዱቄት ወተት በመቀየር ለገበያ እንዲያቀርብ ለማስቻል ነው።

የተፈቀደው ተጨማሪ በጀት የማቀነባበር አቅሙን በተለይ ከናይሮቢ ውጭ በሚገኙት ሁለት ፋብሪካዎቹ ላይ ተግባራዊ ያደርጋል ተብሎም ይጠበቃል።

ተያያዥ ርዕሶች