እሷ ማናት #11 ቋንቋውን የማይችል እንኳ በትወና ብቃቷ ያጨበጨበላት አርቲስት አበበች አጀማ

አርቲስት አበበች አጀማ

አርቲስት አበበች አጀማ ትውልድ እና እድገቷ በገጠራማው የምዕራብ ሸዋ ዞን ነው። በኦሮምኛ ቋንቋ የቴሌቪዥን ድራማ ላይ በመተወን በስፋት ትታወቃለች።

ብልጭ ድርግም በሚሉት የአፋን ኦሮሞ ቲያትሮች ላይ እንደ ኮከብ የሚስሏት በርካቶች ናቸው። ከአንድም ሁለት ቲያትሮች ላይ ዋና ተዋናይ ሆና ሰርታለች። በበዓል ቀናት በሚዘጋጁ የቴሌቪዥን ጭውውቶች ላይም ቋንቋውን የማይችል እንኳ በትወና ብቃቷ ተዝናንቷል።

አርቲስት አበበች በምትወደው የጥበብ ዓለም አስርት ዓመታት በላይ ስትኖር ብዙ ውጣ ውረዶችን ማለፏን ታስረዳለች። አበበች የ18 ዓመታት የጥበብ ዓለም ጅማሬዋንና ህይወትን እንዲህ በአንደበቷ ታስቃኘናለች።

ተወልጄ ነፍስ ያወቅኩት ገጠር ውስጥ ነው። እኔ በተወለድኩበት ቦታ የሴት ልጅ ጠለፋ በጣም የተለመደ ነበር። ሴት ልጆች ይጠለፉ እና ትምህርታቸውን ከዳር ሳያደርሱ ይዳራሉ። ከዚህ ልትታደገኝ የፈለገችው አክስቴ ወደ አዲስ አበባ መጥተሽ መማር አለብሽ ብላኝ ወደ ከተማ አመጣችኝ።

ከዚያም በአዲስ አበባ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ ተማርኩኝ። ከዚያም ከጓደኛዬ ጋር ሆነን ሥራ ፍለጋ ከተማ ውስጥ እየተዘዋወርን የሥራ ማስታወቂያዎችን ማንበብ ተያያዝነው።

ከዛ የኦሮሚያ የባህል እና ስፖርት ቢሮ በትያትር እና በስነ-ጽሑፍ መማር የሚፈልግ ይመዝገብ የሚል ማስታወቂያ ተመለከትን። ጓደኛዬ ተመዝግበን ካልተማርን አለችኝ። እኔ ግን ሥራ የማግኘት እንጂ ወደ ትምህርት የመመለስ ፍላጎት አልነበረኝም።

በመጨራሻ ግን ተመዝግቤ ከእርሷ ጋር አብሬ መማር ጀመርኩ። እኔ በባህሪዬ በጣም ዓይናፋር ነበረርኩኝና ክፍል ውስጥ እንኳን እቀመጥ የነበረው መጨረሻ መስመር ላይ ነበር።

አንድ አቶ ዲማ አበራ የሚባል መምህር ነበረን። ይህ አስተማሪ 'ነይ ወደፊት ውጪና ተናገሪ' ይለኝ ነበር። እኔም ለራሴ 'ለዚህ ሰውዬ ስል ይሄን ትምህርት ማቋረጥ አለብኝ' እያልኩ እናገር ነበር።

አሁን ላይ ግን ይህን መምህር ሁሌም ከልቤ አመሰግነዋለሁ። የራስ መተማመን ኖሮኝ ወደፊት ወጥቼ አቅሜን እንድጠቀም ያስቻለኝ እሱ ነው። በተለያዩ ድራማዎች እና ቲያትሮች ላይ የተለያዩ ገጸ ባህሪዎችን ተጫውቻለሁ። አንድ ግዜ ሩህሩህ ሆኜ ሌላ ግዜ ደግሞ ጨካኝ የእንጀራ እናት ሆኜ ተውኛለሁ።

የትያትር ሥራ ስጀምር የሚከፈለን 18 ብር ብቻ ነበር። የማገኛትን ይችህን 18 ብር ነበር ለምግብ ሆነ ለሁሉም ወጪዬ መሸፈኛ አደርጋት የነበረው። በዚህ ሙያ ታዋቂ ካደረጉኝ ሥራዎቼ መካከል በፋና ሬዲዮ ለበርካታ ዓመታት የተላለፈው "አባ ጃምቦ" በተሰኘው የሬዲዮ ድራማ ላይ የነበረኝ ተሳትፎ ነው።

ይህ ድራማ የጀመርነው ያለምንም ክፍያ ነው። በሬዲዮው ድራማ ላይ ማህበራዊ ጉዳዮች በጥልቅ ስለሚዳሰሱ በብዙዎች ዘንድ በጣም ተወዳጅ አድርጎታል።

ደንጋ በሚሰኘው ፕሮግራም ላይም በርካታ ሠራዎችን ሰርቻለሁ። በጣም አስደሳች ጊዜ አሳልፌያለሁ። ለጥበብ ሙያ ከነበረን ፍቅር የተነሳ በቂ ክፍያ እንኳ ሳናገኘ ነበር የምንሰራው።

የልምምድ ቦታ አጥተን በቤተ-ክርስቲያን ግቢ ውስጥ ለመለማመድ ሄደን ተባረን እናውቃለን። ዛሬ ላይ ግን የጥበብ ሥራው የተሻለ ደረጃ ላይ ደርሶ፤ ቋንቋ እና ባህላችን አድጎ ስመለከት ከፍተና ኩራት ይሰማኛል።

"ሚስጥሬ ትዕግስቴ ነው"

በጥብበ ውስጥ ለብዙ ዓመታት እንድኖር ያደረገኝ ነገር ትዕግስቴ ነው። ዓላማ አለኝ፤ ይህም የአፋን ኦሮሞ 'አርት' አድጎ ማየት ነው። አሁን ላይ በጎ ለውጥ አይቻለሁ። ይህም የሆነው ሳልሰላች በምወደው ህዝብ ተስፋ ባለመቁረጤ ነው።

አንድ አሁኑ መሠረተ ልማቶች ባልተስፋፉበት ዓመት እየተዘዋወርን በትያትር ህዝቡን የማንቃት ሥራ ስንሰራ ነበር። በኢትዮጵያ እና ኤርትራ መካከል ግጭት ተከስቶ በነበነረበት ጊዜም ድንበር ድረስ ሄደን ሠራዊቱን በጭውውት ስናዝናና ነበር።

ይህን ሁሉ ማድረግ የቻልኩት ለህዝብ በነበረኝ ፍቅፍ ብቻ ነው። የተረፈኝም የህዝብ ፍቅር ነው። ለሙያው እና ለህዝብ ፍቅር እና ክብር ስል ብዙ መስዋትነት ከፍያለሁ።

እንደምሳሌ አንድ ሁሉቆ የሚባል ትያትር በራሳችን ወጪ አዘጋጅተን ከስንት ድካም በኋላ ለማስመረቅ አንድ ሳምንት ሲቀረን መንገድ ላይ ወድቄ እግሬ ተሰበረ። ሆስፒታል ተኝቼ የማስበው ስለ ቲያትሩ ነበር። ሃኪሙ መጥቶ 'ይሄ እግር ሊቆረጥ ይችላል' ሲል ስሰማሁ ተነስቼ ጮህኩበት።

ከዛ ሌላ ሃኪም ተቀይሮ መጥቶ አከመኝ። ሳይሻለኝ ከሆስፒታል ወጥቼ በሁሉቆ ቲያትር ላይ እያነከስኩ ስተውን ነበር። በተደጋጋሚ ሶስት ግዜ ብወድቅም ቲያትሩን ከመስራት አላገደኝም።

የስራ ባልደረባዬ የሆነችው አልማዝ ኃይሌ በአንድ ወቅት እናቷን ሳትቀብር ለህዝብ ክብር ብላ መታ ቲያትር ሰርታለች። እኔም እንደ እርሷ ለህዝብ እና ለሙያው ፍቅር ያለኝ።

ለዚህ ሙያ ስል ተርብያለሁ፤ ተጠምቻለሁ፤ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፊያለሁ። አሁን በደረስኩበት ደረጃም ደስተኛ ነኝ።

ወደ ሙያው መቀላቀል የሚፈልጉ ወጣቶች በተለይ ደግሞ ሴቶች፤ የማይቻል ነገር የለም። ፍራቻን አስወጥታችሁ በችሎታችሁ ተማመኑ። ከዛ ይሳካል።

አጭር የምስል መግለጫ እሷ ማናት? የሚለው ጥንቅራችን ያሰቡበትን ዓላማ ለማሳካት ብዙ ውጣውረዶችን ያሳለፉ ሴቶችን ታሪክ የምናስቃኝበት ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ