ታላቁ ሕዳሴ ግድብ፡ ኢትዮጵያ፣ ግብፅ እና ሱዳን በመሠረታዊ ጉዳዮች ላይ መስማማታቸው ተነገረ

ታላቁ ሕዳሴ ግድብ Image copyright Grand Ethiopian Renaissance Dam

በዩናይትድ ስቴትስ አደራዳሪነት ዋሽንግተን ላይ ሲካሄድ የቆው የኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የሦስትዮሽ ውይይት ፍሬያማ እንደነበር ተነግሯል።

ሦስቱ ሃገራት እንዲሁም አሜሪካ እና የዓለም ባንክ በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ እንዳመለከቱት በሕዳሴው ግድብ ሙሊት እና ሌሎች መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት በሚያደርሱ ነጥቦች ላይ ተግባብተዋል።

የአሜሪካው ገንዘብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት በድረ-ገፁ ባወጣው መግለጫ ላይ የሃገራቱ ውሃ ሚኒስትሮች ባደረጉት ውይይት እንዲሁም ቀደም ብሎ በተደረጉ ውይይቶች ላይ ተመሥርቶ ከስምምነት ተደርሷል።

ሃገራቱ አደራዳሪዎች በተገኙበት በሚከተሉት ነጥቦች ላይ 'ለመስማማት' ለቅድመ ስምምነት ደርሰዋል።

  • የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ውሃ ሙሊት የናይል ወንዝን ውሃ ፍሰት ባገናዘ መልኩ የታችኛው ተፋሰስ ሃገራትን የውሃ ክምችት ከግምት ውስጥ ባስገባ መልኩ እንዲከወን
  • የውሃ ሙሊቱ በክረምት እንዲሆን - በጠቅላላው ሙሊቱ ከሐምሌ እስከ ነሐሴ ባለው ወቅት እንዲሆንና አስፈላጊ ከሆነ በመስከረም ወርም እንዲቀጥል
  • የመጀመሪያው ዙር ውሃ ሙሊቱ ከባሕር ወለል በላይ እስከ 595 ሜትር ድረስ እንዲሆንና በኃይል ማመንጨቱ ወቅት ግብፅና ሱዳን በድርቅ ቢጎዱ ሀኔታዎች ከግምት እንዲገቡ ወይም የውሃ ሙሊቱ እንዲቀነስ
  • የሁለተኛው ዙር ውሃ ሙሊቱ ሦስቱ ሃገራት በሚስማሙበት ሁኔታ፤ የናይል ወንዝን በማይጎዳ መልኩ፤ የኢትዮጵያን ኃይል የማመንጨት ፍላጎት አሟልቶ፤ የግብፅና ሱዳንን በድርቅ መመታት አለመታት አገናዝቦ እንዲከወን
  • ሦስተኛውና ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስደው ውሃ ሙሊትም ከላይ የተቀመጡትን ቅድመ-ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዲሆን
  • ሦስቱ ሃገራት ለዘለቄታው የሚስማሙበት ሁኔታ እንዲመቻችና ግጭት ቢፈጠር የሚፈቱባቸው መንገዶች እንዲበጁ

ሚኒስትሮቹ፤ ሦስቱም ሃገራት ለአጭር ጊዜ ወይም ረዘም ላለ ጊዜ የሚቆይ ድርቅን በመቋቋም ረገድ የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው ተስማምተዋል።

ሚኒስትሮቹ ከጥር 19-20 ዋሽንግተን ዲሲ ላይ ተገናኝተው በአባይ ግድብ ሙሊት ዙሪያ የተጠናከረ ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስማምተዋል። እስከዚያ ባለው ጊዜ ቴክኒካዊና ሕጋዊ ውይይቶች እንደሚከናወኑም ታውቋል።

የሦስቱ ሃገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በድንበር ዘለል ትብብር አስፈላጊነት ዙሪያ ጠንከር ያለ አቋም አንፀባርቀው ስምምነቱ እንዲፀና የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል ይላል- የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር ድረ-ገፅ ላይ የወጣው መግለጫ።

የዋሽንግተኑ ስምምነት የሕዳሴ ግድብን በተመለከተ በኢትዮጵያና ግብፅ መካከል ያለውን ውጥረት ያረግበዋል ተብሎ ይጠበቃል።

5 ቢሊዮን ዶላር ያወጣል የተባለለት የሕዳሴ ግድብ 'ፕሮጀክት' ሲጠናቀቅ በአፍሪቃ ትልቁ እንደሚሆን ይጠበቃል። 6 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨትም ከግድቡ የሚጠበቅ ተግባር ነው።

የሦስቱ አገራት የውሃ ሚንስትሮች በህዳሴው ግድብ የውሃ አሞላል እና አለቃቀቅ ጉዳይ ውይይት ሲያደርጉ ሕዳር ላይ በዋሽንግተን ካደረጉት ድርድር አንስቶ ይህ ለአምስተኛ ጊዜ ነው።

በኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን የውሃ ሚንስትሮች በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ትናንት ታህሳስ 29 ቀን 2012 ዓ. ም በአዲስ አበባ ያካሄዱት የሦስትዮሽ ቴክኒካዊ ስብሰባ ያለስምምነት መጠናቀቁ ይታወቃል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ