የሩስያ መንግሥት ስራ ለቅቂያለሁ ብሏል። ምን ማለት ይሆን?

ፑቲን Image copyright Reuters

የሩስያ መንግሥት ሥራ ለቅቋል። ይህ የሆነው ደግሞ ፕሬዝደንት ፑቲን ሕገ-መንግሥታዊ ለውጥ ያሻል የሚል ሃሳብ ካቀረቡ በኋላ ነው። ለመሆኑ የዚህ ትርጉሙ ምንድነው?

ሕገ-መንግሥታዊ ለውጡ በሕዝበ-ውሳኔ አብላጫ ድምፅ ካገኘ ሩስያ ከፕሬዝደንታዊ የመንግሥት አስተዳደር ወደ ፓርላሜታሪያዊ ትቀየራለች ማለት ነው።

ፕሬዝደንት ፑቲን በግሪጎሪያን አቆጣጠር 2024 ላይ ሥልጣን በቃኝ እንዲሉ ሕገ-መንግሥቱ ያዝዛል። ነገር ግን ለአራት የስልጣን ዘመናት ሩሲያን ያስተዳደሩት ፑቲን አዲስ መላ ይፈልጋሉ እንጂ ሥልጣን በቃኝ ይላሉ ተብሎ አይታሰብም ይላሉ ተንታኞች።

ፑቲን በዓመታዊው ሃተታቸው ላይ ነው አዲሱን ዕቅዳቸውን ይፋ ያደረጉት። ከንግግራቸው በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዲሚትሪ ሜድቬዴቭ ፑቲን ያቀረቡት ሃሳብ እንዲፀድቅ በማሰብ የሩስያ መንግሥት ሥልጣን ለቅቋል ሲሉ ተደመጡ።

«በጣም ያልጠበቅነው ነገር ነው የሆነው» ሲሉ አንድ ምንጭ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የፑቲን ሃሳብ ምንድነው?

በዓመታዊው የላዕላይና ታህታይ ሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት መክፈቻ ላይ ንግግር ያሰሙት ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ ከፕሬዝደንታዊ ወደ ፓርላሜንታዊ ስርዓት በሚደረግበት ሽግግር ላይ ሕዝበ-ውሳኔ እንደሚደረግ አሳውቀዋል።

ይህ ማለት ፑቲን፤ ሩስያ ከፕሬዝደንታዊ አስተዳደር ልክ እንደ ኢትዮጵያ በፓርቲ ወደ ሚመረጥ ጠቅላይ ሚኒስቴርነት አስተዳደር እንደትሸጋገር ይሻሉ ማለት ነው። አሁን ባለው የአስተዳደር ሥርዓት በፕሬዝደንቱ የሚመረጡት ጠቅላይ ሚኒስትር የረባ ሥልጣን የላቸውም።

ሌላኛው የፑቲን ሃሳብ 'ስቴት ካውንስል' የተሰኘው ምክር ቤት አቅም እንዲጎለብት ነው። ፑቲን የሚመሩት ይህ ምክር ቤት በክልል ኃላፊዎችን ያዋቀረ ነው።

ፑቲን ካነሷቸው ሌሎች ሃሳቦች መካከል የዓለም አቀፍ ሕጎችን ጫና መቀነስ፣ የፕሬዝደንት ሥልጣን ላይ መቆያ ጊዜ እንዲራዘም ማድረግ፣ የሌላ ሃገር ዜግነት ወይም የሥራ ፈቃድ ያላቸው ፖለቲከኞች ጉዳይ ይገኙበታል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሜድቬዴቭ የሩስያ መንግሥት ሥልጣን ለቅቋል ብለው ሲያውጁ ከአጠገባቸው ፕሬዝደንት ፑቲን ነበሩ። ማሻሻያው ያስፈለገው የሕግ አውጭውን፣ ተርጓሚውንና አስፈፃሚውን አሠራር ለመናጥ ነው ሲሉም ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን ያመሰገኑት ፑቲን እሳቸው በሚመሩት የብሔራዊ ደህንነት ምክር ቤት በምክትልነት እንዲያገለግሏቸው ጠይቀዋል። አክለውም የሩስያ ቀረጥ አግልግሎት መሥሪያ ቤት ኃላፊ ሚካይል ሚሹስቲን የሜድቬዴቭን ቦታ ተክተው እንዲሰሩ ሾመዋል።

የሩስያ ሕገ-መንግሥት አንድ ፕሬዝድንት በተከታታይ ከሁለት ጊዜ በላይ እንዲያገለግል አይፈቅድም። ፑቲን ሁለት ጊዜ ካገለገሉ በኋላ ታማኝ አገልጋያቸው እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሜድቬዴቭ ለአራት ዓመታት ፕሬዝደንት ሆነው አገልግለዋል። በወቅቱ ፑቲን ጠቅላይ ሚኒስትር ነበሩ፤ ሥልጣኑ የነበረው በእሳቸው እጅ ነው የሚሉ በርካቶች ቢሆኑም።

ተቃዋሚዎች ፑቲን ያሰቡት ሕገ-መንግሥታዊ ማሻሻያ የሥልጣን ጊዜያቸው እያበቃ ስለሆነ ያዘጋጁት ድራማ እንጂ ለውጥ ታስቦ አይደለም ይላሉ።

በፈረንጆቹ 1999 ላይ ፕሬዝደንት ቦሪስ የልቲስንን ተክተው ሥልጣን የያዙት ፑቲን በፕሬዝደንትነትና በጠቅላይ ሚኒስትርነት ሃገራቸው ለ20 ዓመታት አገልግለዋል። መንበራቸውን እንዲሁ በቀላሉ ይለቃሉ ብሎ ማሰብ ዘበት ነው የሚሉ በርካቶች ናቸው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ