ናይጄሪያ፡ በርካቶች መርሳት ያልቻሉት ጦርነት ሲታወስ

ናይጄሪያ፡ በርካቶች ሊረሱት የሚፈልጉት የእርስ በርስ ጦርነት ሲታወስ Image copyright MIRRORPIX

ከአንድ ሚሊዮን በላይ ናይጄሪያውያንን ቀጥፏል። የዛሬ 50 ዓመት ያበቃው የናይጄሪያው የእርስ በርስ ጦርነት። ጦርነቱ ናይጄሪያ ላይ ጥሎ ያለፈው ጠባሳ ግን አሁንም አለ።

ባያፍራ በተሰኘችው ግዛት ምክንያት የተነሳው ጦርነት ናይጄሪያውን ሊረሱት የሚፈልጉት ቢሆንም ለኢግቦ ሰዎች ግን የሕይወት ጉዳይ ነው።

በግሪጎሪ አቆጣጠር 1967 ላይ ናይጄሪያ ውስጥ ሁለት ጊዜ የመፈንቅለ መንግሥት ሙክራ ተደረገ፤ ይህንን ተከትሎ አንድ ሚሊዮን ገደማ የኢግቦ ሰዎች ወደ ደቡብ ምስራቅ ናይጄሪያ ተመሙ፤ ነፃነታቸውንም አወጁ።

ይህ ያልተዋጠለት የወቅቱ የናይጄሪያ መንግሥት ጦርነት አወጀ። ከ30 ወራት ጦርነት በኋላ ባያፍራ እጅ ሰጠች። ጥር 7/1970 ጦርነቱ በይፋ ማብቃቱ ተነገረ።

መንግሥት በጦርነቱ ማንም አላሸነፈም፤ ማንም አልተሸነፈም ቢልም የኢግቦ ልጆች ግን ስለ ጦርነቱ እየተነገራቸው ነው ያደጉት።

ከጦርነቱ ከተረፉት መካከል ክርስቶፈር ኤጂኮ አንዱ ናቸው። ጦርነቱ ሲጀመር በናይጄሪያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበር። የማውቃቸው ተማሪዎች ሁላ በጦርነቱ ተሳትፈዋል ይላል።

የባያፍራን ጦር ተቀላቅሎ የናይጄሪያ ጦር እንዲሰልል ተሾመ። የ76 ዓመቱ ክሪስ ራሳችንን እንደ አስማት ሰሪ ነበር የምንቆጥረው ይላሉ።

«የምንዋጋው ከሰለጠኑ ወታደሮች ጋር ነበር። እኛ ግን የሁለት ቀናት ሥልጠና ነበር ተሰጥቶን ወደ ጦርነት የገባነው፤ ረሃቡም አለ። በእንደዚህ ዓይነት ሁኔታ ጦርነት መግጠም በጣም ከባድ ነው።»

ነገር ግን የኢግቦ ጦር ታዋቂውን የጦር ጄኔራል አሕማዱ ቤሎን ገደለ። ይህ ደግሞ ለአፀፋ ምላሽ ዳረገ። የመንግሥት ጦር የኢግቦ ሰዎችን በጅምላ መግደል ያዘ። በዚህም በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አለቁ፤ የቀሩቱ ደግሞ ምስራቃዊ ክፍለ ሃገር ወደ ሚባለው ክፍል ተሰደዱ።

የወቅቱ የምስራቃዊ ክፍለ ሃገር መሪ ኤሜካ ኦጆኩ ነበር። ይህ ያስመረረው ኦጆኩ ምስራቃዊውን ክፍል ለመገንጠል እንቅስቃሴ ጀመረ። ኦጆኩ ዩኒቨርሲቲዎች ድረስ እየሄደ ተማሪዎችን በመመልመል ለነፃ እንውጣ ጦርነት ያዘጋጅ ነበር።

ተማሪዎቹን ለማጋዝ ሄሊኮፕተር ይመጣ እንደነበር የሚያወሱት ክሪስ ተማሪዎች እንዴት እየሮጡ ወደ ሄሊኮፕተሯ ይገቡ እንደነበር አይዘነጉም።

የመጀመሪያው የጦርነት ዓመት የመንግሥት ጦር የውቅያኖስ ዳር ከተማ የሆነችው ፖርት ሃርኮርትን ተቆጣጠረ። ወደ ባያፍራ ምግባን መሰል ምርቶች እንዳይገቡ ከለከለ። ረሃቡ በጣም ከመፅናቱ የተነሳ ሰዎች ዓይጥ እያየዙ ይበሉ እንደነበር ክሪስ ያስታውሳሉ። ነገር ግን መሃል የባያፍራ ጦር ወሳኝ የሆነ ድል የመንግሥት ጦር ላይ ተቀናጀ።

«ያኔ ትንሽ ተስፋ ተሰምቶን ነበር። ከውጭ ኃይል እርዳታ እስክናገኝ ድረስ መጠበቅ ያዝን።»

በ1969 መጨረሻ ግን ለኢግቦዎች ሁሉም እንዳልሆነ ሆነ።

ጦርነቱ ሲያበቃ የዛኔው ወጣቱ ክሪስ ለሁለት ዓመታት ያላቸውን ቤተሰቦቹን ፍለጋ መኳተን ያዘ። በወቅቱ የተሰጠውን የእርዳታ ሩዝ ሰብስቡ ቤተሰቦቹ ይገኙበት ይሆናል ወዳለው አካባቢ ጉዞ ጀመረ።

Image copyright Getty Images

ረሃብ ቢያዳክመውም ሩዙን በጀርባው እንደተሸከመ ቤተሰቦቹን ፍለጋ ቀጠለ። ጓደኞቹና የትምህርት ቤት አጋሮቹ በጦርነቱ ምክንያት አልቀዋል። እሱማ ሞቷል ብለው ተስፋ የቆረጡ ቤተሰቦቹን ግን አገኛቸው። ከጀርባው ያዘለው ሩዝ ደግሞ ደስታውን እጥፍ አደረገው።

በወቅቱ በረሃብ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር በጥይት ከሞቱት እንደሚበልጥ ይነገራል።

ይማርበት የነበረው ዩኒቨርሲቲ እንደ አዲስ ሲከፈት ክሪስ አጎ ከጥቂት ወራት በኋላ ተቀላቅሎ በዕፅዋትና አፈር ሳይንስ ድግሪውን ጫነ።

ክሪስ ኦጎና ጓደኞቹ በጦር አለቃቸው ተመርተው ባይዋጉ ኖሮ ጦርነቱ 30 ሰዓታትም አይፈጀም ነበር ይላሉ ሌላኛው የጦርነቱ ተሳታፊ ፌሊክስ።

በወቅቱ ባያፍራ የራሷ መገበያያ ገንዘብ ነበራት። ነገር ግን በጦርነቱ ምክንያት ብዙዎች ያከማቹት ቤሳ ከጥቅም ውጭ ሆነ።

በወቅቱ የመገንጠል እነቅስቃሴውን ሲያራምድ የነበረው የጦር መሪው ኤሜካ ኦጆኩ በግሉ አውሮፕላኑ ወደ አይቮሪ ኮስት ማምለጥ ችሏል። 13 ዓመታት ያክልም በስደት ሊኖር ግድ ሆነ፤ በስተመጨረሻ ግን የናይጄሪያ መንግሥት ምሕረት አድረጎለት ወደ ሃገር ቤት ተመለሰ።

2011 ላይ ሕይወቱ ያለፈችው ኦጁኩ በወታደራዊ ሥነ-ሥርዓት ነው እንዲቀበር የተደረገው። የወቅቱ የናይጄሪያ ፕዝደንት ጉላክ ጆናታንን ጨምሮ ሌሎች ባለሥልጣናት በቀብር ሥነ-ሥርዓቱ ላይ ተገኝተዋል።

የባያፍራ ጦርነት 50 ዓመታት ደፈነ። ናይጄሪያ አሁንም አንድነቷን ለማስጠበቅ እየታገለች ነው። የኢግቦ ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሌሎች ማሕበረሰቦች ናይጄሪያ እንደ አዲስ መዋቀር አለባት የሚል ድምፅ ያሰማሉ።

ማንም ግን ስለ ጦርነቱ ማውራት አይፈልግም። መንግሥትም ቢሆን የመገንጠል ሙከራ ተደርጎ የሆነውን አይታችኋል ማለት አልተጠበቀበትም። ሁሉም የገፈቱ ቀማሽ ናቸው እና።

ተያያዥ ርዕሶች