ለ18 ሰዓታት በረዶ ውስጥ ተቀብራ የቆየችው የ12 ዓመት ታዳጊ በህይወት ተገኘች

ካሽሚር ውስጥ ለ18 ሰዓታት በረዶ ውስጥ ተቀብራ የቆየችው ልጃ ገረድ በሕይወት ተገኘች Image copyright Reuters

በፓኪስታን ካሽሚር ግዛት ውስጥ ለ18 ሰዓታት በረዶ ውስጥ ተቀበራ የቆየችው ታዳጊ በህይወት ተገኘች።

በአካባቢው በድንገት የተከሰተ የበረዶ ናዳ ውስጥ ለ18 ሰዓታት ተቀብራ የቆየችው የ12 ዓመቷ ሳሚና ቢቢ በህይወት መገኘት አነጋጋሪ ሆኗል።

ታዳጊዋ ሳሚና ቢቢ በመኖሪያ ቤቷ ውስጥ ሳለች ነበር ደንገተኛ የበረዶ ናዳ መኖሪያ ቤቱን የዋጠው።

ምንም እንኳ የታዳጊዋ ህይወት ቢተርፍም በርካታ የሳሚና የቤተሰብ አባላት በድንገተኛ አደጋው ህይወታቸው አልፏል።

ይህ ያልጠበቀችው አደጋ ሲያጋጥማት "እዚያው እሞታለሁ" ብላ ሰግታ እንደነበርለሬውተርስ ተናግራለች።

በአካባቢው የተከሰተው የበረዶ ናዳ እና የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 74 ሰዎችን ገድሏል።

በሕንድ የምትተዳደረው ካሽሚርና አፍጋኒስታን ተመሳሳይ ችግር እያስተናገዱ ነው።

Image copyright Mary Evans Picture Library
አጭር የምስል መግለጫ ካሽሚር

'የሆነው ሁሉ ቅጽበት ውስጥ ነበር'

ከአደጋው የተረፉት የሳሚና እናት እንደሚሉት ከሆነ ድንገተኛው የበረዶ ናዳ ሲከሰት የቤተሰቡ አባላት አንድ ላይ ተሰባስቦ እሳት እየሞቀ ነበር።

"ምንም ድምጽ አልሰማንም ነበር። ሁሉም ነገር በቅጽበት ውስጥ ነበር የተከሰተው" ይላሉ የሳሚና እናት። ልጃቸው በሕይወት አገኛለሁ የሚለው ተስፋቸው ተመናምኖ እንደነበረ ለሬውተርስ ተናግረዋል።

የፓኪስታን የአደጋ መከላከል ባለስልጣን እንደገለጸው በመላው አገሪቱ በበረዶ በተመቱ አካባቢዎች ከ100 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በሕንድ በኩል ደግሞ በተመሳሳይ አደጋ 8 ሰዎች ሞተዋል።

ካሽሚር 138 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የምትሸፍን ሲሆን ሃይቆቿ፤ ሜዳዎቿና በበረዶ የተሸፈኑ ተራራዎቿ የውበቷ ምንጮች ሲሆኑ በቀሪው ዓለም ዘንድም እውቅና አሰጥተዋታል።

ሕንድና ፓኪስታን እአአ 1947 ላይ ነጻነታቸውን ከተቀዳጁ በኋላ አካባቢው ለሁለት ተከፍሎ የውዝግብ ምንጭ ሆኗል።