ያለፉት አስር ዓመታት ከፍተኛ ሙቀት የነበረበት ሆኖ ተመዘገበ

የምድር ሙቀት ጨምሯል Image copyright Getty Images

ዓለማችን አይታ የማታውቀው ከፍተኛ ሙቀት ባለፈው አስር ዓመት ማስመዝገቧ ተነገረ።

ሦስት ዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎች ባካሄዱት ጥናት መሠረት፤ እስከ ፈረንጆቹ 2019 መገባደጃ ድረስ የነበረው 10 ዓመት፤ ከፍተኛ የሙቀት ክብረወስን የተመዘገበበት ዘመን ሆኖ አልፏል።

እነዚህ ተቋማት ያጠኑት መረጃ እንደሚያሳየው ከ1850 ወዲህ የመጀመሪያው ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበው ባለፈው ዓመት ነው።

ያለፉት አምስት ዓመታት ከ170 ዓመታት በኋላ በተከታታይ ዓመታት የሙቀት መጠን የጨመረባቸው ዓመታት ናቸው። እነዚህ አምስት ዓመታት በአማካይ እያንዳንዳቸው አንድ ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ጨምረዋል። 2020ም እንደዚሁ ሊቀጥል ይችላል ተብሏል።

2016 ደግሞ በኤል ኒኖ ምክንያት ከፍተኛ ሙቀት የተመዘገበበት ዓመት ሆኖ አልፏል ተብሏል።

መረጃው እንደሚያሳየው ከ1850 እስከ 1900 ከነበረው አንጻር ሲታይ በ2019 የሙቀት መጠን በ1.05 ዲግሪ ሴንት ግሬድ ከፍ ብሏል።

በመሆኑም ሦስቱ ተቋማት ተቀራራቢ ግን የተለያየ መረጃ ቢያመጡም በ2019 ግን ዓለም ከቅድመ ኢንዱስትሪ ዘመን በኋላ ቢያንስ በ1.1 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ መሞቋን ይስማማሉ።

በሰዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚለቀቀው የካርበን ልቀት ለሙቀት መጠን መጨመር ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል ተብሏል።

በዚህ ሳምንት የሚታተሙ መረጃዎች እንደሚሉት ደግሞ በየብስ ላይ ብቻ ሳይሆን ባለፈው ዓመት ውቅያኖስ ውስጥ ያለው ሙቀትም በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ መሰረት የያዝነው የፈረንጆቹ 2020 ዓመትም ከፍተኛ የሙቀት መጠን የሚመዘገብበት ዓመት እንደሚሆን ሳይንቲስቶች ተንብየዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ