ከኢትዮጵያ ለአረብ አገራት በሕገ ወጥ የሚሸጡት አቦ ሸማኔዎች

አቦ ሸማሌ ከግልገሏ ጋር Image copyright Hoberman Collection
አጭር የምስል መግለጫ አቦ ሸማሌ ከግልገሏ ጋር

በየወሩ ቢያንስ አራት የአቦ ሸማኔ ግልገሎች በሕገ ወጥ የዱር እንስሳት አዘዋዋሪዎች አማካኝነት ከሃገር ሊወጡ ሲሉ ደንበር ላይ እንደሚያዙ ተነገረ።

የኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን እንዳስታወቀው፤ ግልገሎቹ በቅደሚያ ከኢትዮጵያ ወደ ሶማሊላንድ ሃርጌይሳ ከተወሰዱ በኋላ በየመን በኩል ወደ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች ተወስደው ይሸጣሉ።

በኢትዮጵያ የዱር እንስሳት ጥበቃ ባለስልጣን የእንስሳት እና የእንስሳት ውጤቶች ሕገ-ወጥ ዝውውር እና ቁጥጥር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዳንኤል ጳውሎስ፤ አቦ ሸማኔዎቹን ባለጸጋ አረቦች የቤት እንስሳ አድርገው ያሳድጓቸዋል።

Image copyright ኢዱጥባ
አጭር የምስል መግለጫ በህገ ወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ ከተያዙት አቦ ሸማኔዎች አንዱ

አቶ ዳንኤል ጨምረው እንደተናገሩት፤ አቦ ሸማኔዎቹ ግብይት የሚፈጸመው በጥቁር ገብያ ላይ ስለሆነ የተተመነ ቋሚ ዋጋ የላቸውም። ይልቁንም ገዥን እና ሻጭ በተስማሙበት ዋጋ ግልገሎቹ ይሸጣሉ።

አብዛኛውን ጊዜ ከኢትዮጵያ በሕገ-ወጥ መንገድ የሚያወጡት ሰዎች አንድ የአቦ ሸማኔ ግልገልን ከ10ሺህ እስከ 15ሺህ የኢትዮጵያ ብር ይሸጣሉ።

ግለገሎቹ አረብ ሃገራት ከደረሱ በኋላ ግን ዋጋቸው እጅጉን ከፍ እንደሚል አቶ ዳንኤል ገልጸዋል።

ከአሾ ሸማኔ በተጨማሪ የአንበሳ ደቦሎችም የሕገ-ወጥ እንስሳት አዘዋዋሪዎች ሰለባ ናቸው። አቶ ዳንኤል ከወራት በፊት አንድ ኢትዮጵያዊ ሶማሊላንድ ላይ የአንበሳ ደቦል ይዞ መገኘቱን ተናግረዋል። "የአንበሳ ደቦሏን ከሶማሊላንድ አምጥተን በእኛ መጠለያ ውስጥ እንድትቆይና እንድታገግም አድርገናል" ብለዋል።

በተያያዘ ዜና ከሁለት ቀናት በፊት የሳዑዲ ባለስልጣናት የአቦ ሸማኔ ግልገሎችን በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለማስገባት የሞከሩ በርካታ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋላቸውን አስታውቃል።

የሳዑዲ ፖሊስ ግልገሎቹ መነሻቸው የአፍሪካ ቀንድ ሃገራት በተለይም ኢትዮጵያና ሶማሊያ ናቸው ብሏል።

የእንስሳት መብት ተከራካሪዎች እንደሚሉት ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ እንስሳት በሕገ-ወጥ ዝውውሩ ወቅት በሚደርስባቸው እንግልት ህይወታቸው ያልፋል። በተጨማሪም ሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች በኢትዮጵያ እና በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት ውስጥ ለሚገኙት እንስሳት ከፍተኛ ስጋት ናቸው ተብሏል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ