ደቡብ አፍሪካዊው ከ2 ወራት በላይ የተሰቀለ በርሜል ላይ በመኖር የዓለም ክብረ ወሰንን ሰበረ

ደቡብ አፍሪካዊው 2 ወር በርሜል ውስጥ

ደቡብ አፍሪካዊው ጎልማሳ የተሰቀለ በርሜል ላይ ከሁለት ወራት በላይ ተቀምጦ በመኖር የዓለም ክብረ ወሰንን ሰበረ።

ጎልማሳው 25 ሜትር ከፍታ ባለው ለዚሁ ተግባር ተብሎ በተዘጋጀ ባላ ጫፍ ላይ በተቀመጠ በርሜል ላይ ለሁለት ወራት በመኖር ከዓለም ተወዳዳሪ የሌለው ግለሰብ ሆኗል።

በዓለም ክብረወሰንነት ተይዞ የነበረው የተመሳሳይ ጀብዱ ክብረ ወሰን 54 ቀናት ነበር። ደቡብ አፍሪካዊዉ ክሩገር የዛሬዋን ሰኞ ጨምሮ 67 ቀናትን 'በርሜል መኖሪያዬ' ብሎ ምድርን ወደታች አቀርቅሮ እያየ ከርሟል።

ራሱን በርሜል ላይ ሰቅሎ በማቆየት ተወዳዳሪ ያልተገኘለት ጎልማሳው ከዚህ ቀደምም ከ22 ዓመት በፊት የነበረውን ክብረ ወሰን የሰበራው ራሱ ነበር። በ1997 (እ.አ.አ) ክብረ ወሰኑን አሻሽሎ 54 ቀናት ያደረገው ራሱ ቬርኖን ክሩገር ነበር።

አሁን ክብረወሰኑን ያሻሻለበት በርሜል 500 ሊትር የመያዝ አቅም ያለው ሲሆን አንድ ሜትር ከፍታና ግማሽ ሜትር ደግሞ የጎን ስፋት እንዳለው ክሩገር ተናግሯል።

ምግብን ጨምሮ ሁሉም የሚፈልገው ነገር በቅርጫት ታስሮ ይላክለታል፤ እርሱ ደግሞ ከላይ ሆኖ በገመድ በመጎተት በተላከለት ነገር የበርሜል ቤቱን ፍላጎት ያሟላል።

በዚህ ሂደት ታዲያ አድናቂህ ነን ያሉ ግለሰቦች ለጊዜው ሚስጥር ያደረጋቸውን የተለያዩ ሰጦታዎች እንደሚልኩለት የተናገረው ክሩገር ከህጻናት የሚላኩ ከረሜላዎችን ሁሉ መቀበሉን ያስታውሳል።

በርሜሉ ውስጥ መኖር ከጀመረ ከቀናት በኋላ ስፖርት የሚያሰሩት ሰዎች መኖራቸውን ገልጿል። "ሁልጊዜ ጠዋት ሰዎች መጥተው ለግማሽ ሰዓት እራሴን እንዳፍታታ ያደርጉኛል" ያለው ክሩገር ከዚያ በኋላ በአንጻሩም ቢሆን ኑሮ እንደቀለለለት ይናገራል።

ባላው በንፋስ ወቅት የተወሰነ ቢንቀሳቀስም ብዙም አያስፈራኝም ብሏል። ክሩገር እንደሚለው ልቡን በፍርሃት የሚያርደው ግን በደመና ወቅት የሚሰማው ከፍተኛ የመብረቅ ድምጽ ነው።

በነእዚህ 67 ቀናት ውስጥ ታዲያ ለክሩገር ሁሉም ነገር ቀላል ባይባልም መፍትሔው ግን የሚከብድ አልነበረም። ከነገሮች ሁሉ ክሩገርን ያስቸገረው ጎኑን በእንቅልፍ ማሳረፍ አለመቻሉ እንደነበር ለቢቢሲ ተናግሯል።

"ምንም እግሬን መዘርጋት አልችልም፣ ጠርዙ ላይ ጋደም ማለት እፈልጋለሁ ግን እርሱም ስስ በመሆኑ ሲወጋኝ ያመኝና ወዲያውኑ እነቃለሁ" በማለት ለመተኛት ይቸገር እንደነበር ገልጿል።