የጥምቀት በዓል፡ ከበዓሉ አከባባር ጋር በተያያዘ ጎንደር እና ሐረር የተከሰተው ምንድነው?

ሐረር Image copyright Eric Lafforgue/Art in All of Us

በሐረር ከጥምቀት በዓል አከባበር ጋር በተያያዘ አለመረጋጋት ተፈጥሮ እንደነበር ተሰምቷል። በዚሁ ዙሪያ የሐረሪ ክልል የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ ናስር ይያ ስለተፈጠረው ነገር ማብራሪያ እንዲሰጡን ጠይቀናቸዋል።

ኃላፊውም ''የጥምቀት በዓልን ምክንያት በማድረግ የእምነቱ ተከታዮች በዓሉን ለማክበርና አካባቢውን ለማስዋብ የተለመደ እንቅስቃሴያቸውን በሚያደርጉበት ወቅት በዓሉን የማይመለከትና ሕግ የማይፈቅደውን ባንዲራ ለመስቀል ሙከራ ያደረጉ በመኖራቸው አለመረጋጋት ተከስቶ ነበር'' ብለዋል።

''ይህንን ተከትሎም ትናንት የሀይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ የአካባቢው ወጣቶችና ቄሮዎችን በማስተባበርና የጸጥታ ኃይሎችንም በማቀናጀት ችግር እንዳይፈጠር ማድረግ ችለናል'' ሲሉ አስረድተዋል።

ኃላፊው እንዳሉት፤ አንድ ሁለት ሰዎች ሰንደቅ አላማውን ለመስቀል በሚሞክሩበት ወቅት ሌሎች ደግሞ 'ይህን አትሰቅሉም' በሚል ግርግር ተፈጥሮ ነበር።

''እነዚህ [ግርግሩን የፈጠሩት] ሰዎች እምነትን ከእምነት ማጋጨት፤ ሕዝብን ከሕዝብ ማጋጨት ነው እቅዳቸው። በሁሉም አካባቢዎች ታቦት በሰላም ወጥቶ ይገባል። ነገር ግን መስጂድና ቤተክርስቲያን በቅርበት በሚገኙባቸው አካባቢዎች ችግር ለመፍጠር ተሞክሯል'' ብለዋል።

ትናንት በሐረር አለመረጋጋት እንደነበርና ተኩስም እንደተሰማ በስፋት እየተነገረ መሆኑን የጠቀስንላቸው ኃላፊው፤ ጠዋት ላይ አንዳንድ ግርግሮች ተፈጥረው የነበሩ ቢሆንም ከሰዓት ከተማው መረጋጋቱን መሆኑን ነግረውናል።

''ዛሬ ታቦት በሚገባበት ወቅት አራተኛ በተባለው አካባቢ ተገቢ ያልሆነ ጭፈራና ንብረት ላይ ድንጋይ መወርወር ጀምረው ነበር። አካባቢው ቤተ ክርስቲያንም መስጂድም ያለበት ከመሆኑ አንጻር በሀይማኖት ስም የተደረገው ነገር ተገቢ አይደለም። ነገር ግን ተፈጥሮ የነበረው ነገር በቁጥጥር ስር ውሏል'' ሲሉ አስረድተዋል።

ንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት ውጪ እስካሁን የተጎዳ ሰው አለመኖሩን ኃላፊው ተናግረዋል። አቶ ናስር የጉዳት መጠኑን በትክክል ለመግለጽ ባይችሉም፤ ወደ ስምንት የሚጠጉ ቤቶች ድንጋይ ተወርውሮባቸው መስታወቶች እንደተሰባበሩ ያስረዳሉ።

ትናንት ጠዋት ታቦት የሚሸኙ ሰዎች መንገድ ተዘግቶባቸዋል ስለመባሉ የተጠየቁት የጸጥታ ቢሮ ኃላፊው፤ '' ማንም መንገድ የተዘጋበት የለም፤ ማንም መንገድ የዘጋም የለም" ብለዋል።

''ታቦት እንዳያልፍ አልተከለከለም፤ መንገዱም ክፍት ነው። ይሄ ተግባር ውዥንብር ለመፍጠርና ሕዝቡን በእምነት ስም ለማነሳሳት የሚደረግ ጥረት ነው'' ሲሉም አብራርተዋል።

ከሁለቱ ቀናት ክስተት ጋር በተያያዘ እስካሁን ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውንና ምዕመናን በዓሉን አክብረው ወደቤታቸው ገብተው፣ ከተማዋም ሰላማዊ እንቅስቃሴዋን እንደቀጠለች አቶ ናስር ነግረውናል።

ጎንደር

የጥምቀት በዓል ማዕከል እንደሆነች የሚነገርላት የጎንደር ከተማም ከጥምቀት በዓል ጋር በተያያዘ አሳዛኝ ክስተት አስተናግዳለች።

በጎንደር ጥንታዊው የአፄ ፋሲል ገንዳ አካባቢ እየተካሄደ የነበረው የጥምቀት በዓል ታዳሚያንን እንዲያስተናግድ ተሰድሮ የነበረ የእንጨት ርብራብ ተደርምሶ ቢያንስ 10 ሰዎች ሕይታቸውን ማጣታቸው ተዘግቧል። ቀላልና ከባድ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውም አሉ።

Image copyright AFP

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በዓሉን ለመደታደም በሺዎች የሚቆጠሩ ጎብኝዎች ወደ ጎንደር አቅንተው ነበር ብሎ ዘግቧል።

ከአዲስ አበባ ወደ ጎንደር የጥምቀት በዓልን ለማክበር የሄደው ሳሙዔል ባህሩ በአደጋው የተጎዱ ሰዎች በቃሬዛ ወደ ሆስፒታል ሲወሰዱ ተመልክቻለሁ ይላል። ከባለቤቱ ጋር ጥምቀትን ለማክበር የሄደው ሳሙዔል ከአደጋው በኋላ ከፍተኛ ድንጋጤ እንደነበር ይናገራል።

የጎንደር ከተማ ሰላም እና ፀጥታ ኃላፊ አቶ ተስፋ መኮንን የእንጨት ርብራቡ በ'ባለሙያዎች' የተሠራ ነው፤ አደጋው የተከሰተው በእንጨት ርብራቡ ደካማነት አይመስለኝም ብለዋል።

"ወጣቶች ወደ ላይ ወጥተው ማክበር ፈልገው ሲወጡ እንጨቱ መሸከም ከሚችለው በላይ ሆኖበት ነው የተደረመሰው።»

የአማራ ክልል ፖሊስ ቃል-አቀባይ ኮማንደር መሠረት ደባልቄ 100 ያክል ሰዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፤ አብዛኛው ቀላል ጉዳት ነው፤ የሞቱ ሰዎች ቁጥር የጠራ መረጃ የለኝም ሲሉ ሰኞ አመሻሹን ላይ ተናግረዋል።

ተጎጂዎች ወደ ጤና ተቋማት ተወስደው ሁኔታው ከተረጋጋ በኋላ በዓሉ እንዲቀትል ተደርጓል።

ተያያዥ ርዕሶች