የምሽት ክበብ ሙዚቃ አጫዋቹን በጥይት የመቱት የፓርላማ አባል ክስ ተመሰረተባቸው

ባቡ ኦዊኖ Image copyright ባቡ ኦዊኖ

ባቡ ኦዊኖ የተባሉት የኬንያ የሕዝብ እንደራሴ ባለፈው አርብ ምሽት መዝናኛ ክለብ ውስጥ ሙዚቃ አጫዋቹን በጥይት መምታታቸውን ተከትሎ በግድያ ሙከራ ክስ ተመሰረተባቸው።

የኬንያ ፖሊስ የሕዝብ እንደራሴውን በሳምንቱ መጨረሻ ላይ በቁጥጥር ሥር እንዳዋላቸው አስታውቆ ነበር። ፖሊስ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ባይሰጥም በቦቢ አዊኖ የፌስቡክ ገጽ ላይ የሰፈረው ጽሑፍ የሕዝብ እንደራሴው በግለሰቦች ከተከበቡ በኋላ ራሳቸውን ለመከላከል ለመተኮስ ተገደዋል ይላል።

ቅዳሜና እሁድን በፖሊስ ቁጥጥር ስር የነበሩት ባቡ ኦዊኖ ሰኞ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን በቀረበባቸው የመግደል ሙከራ ክስ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ አስረግጠው ተናግረዋል።

የፓርላማ አባሉ የምሽት ክበብ ሙዚቃ አጫዋቹን በጥይት መቱ

ኬንያ ሳንቲሞቿ ላይ የነበሩ መሪዎችን በእንስሳት ቀየረች

ጉዳዩን የሰሙት ዳኛ ፍራንሲስ አንዳዪ የሕዝብ እንደራሴው ለተጨማሪ አንድ ሳምንት በፖሊስ ቁጥጥር ስር እንዲቆዩና ጉዳዩ በደንብ እንዲጣራ ውሳኔ ማስተላለፋቸው ታውቋል።

የገዢው መንግሥት ተቀናቃኝ የሆነው የኦሬንጅ ፓርቲ አባል የሆኑት ባቡ አዊኖ ከክስተቱ በኋላ "ተቀናቃኞቼ የግድያ ዛቻ እና ሙከራ እያዳረሱብኝ እንደሆነ ለፖሊስ በተደጋጋሚ ሪፖርት አድርጌያለሁ፤ አሁንም የተፈጠረው ከዚሁ ጋር የተገናኘ ነው። ብዛት ያላቸው የተቆጡ ወጣቶች ከበቡኝ። ከዚያም የተኩስ ልውውጥ ተደረገ" ብለዋል በፌስቡክ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ።

ባቡ አዊኖ ይህን ይበሉ እንጂ በምሽት መዝናኛ ክበብ ውስጥ የተቀረጸው የሲሲቲቪ ካሜራ ምስል ያሳየው የተለየ ነበር። ኬ24 የተባለው ቴሌቪዥን ያወጣው ተንቀሳቃሽ ምስል፤ የሕዝብ እንደራሴው በክበቡ ውስጥ ከጥቂት ሰዎች ጋር ሆነው ሺሻ እያጨሱ እየተዝናኑ ሳለ አንድ ወጣት ይጠጋቸዋል። ከዚያም ከቅርብ ርቀት በሽጉጥ መትተው ይጥሉታል።

ከሌላ ሲሲቲቪ ካሜራ የተገኘው ምስል ደግሞ፤ በጥይተ ተመትቷል የተባለውን ወጣት ሁለት ሰዎች እጅ እና እግሩን ይዘው ሲያወጡት ኬ24 አሳይቷል።

ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ወተታቸውን ሊከላከሉ ነው

የሕዝብ እንደራሴው ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ ከፍተኛው የእድሜ ልክ እስራት ሊፈረድባቸው እንደሚችል ተገምቷል። በጥይት የተመታው ሙዚቃ አጫዋች (ዲጄ) ናይሮቢ በሚገኝ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት ጥይቱ አንገቱ ውስጥ በመግባቱ ቀዶ ህክምና ተደርጎለታል።

በቅርቡ የኬንያ ፖሊስ በወንጀል ለሚጠረጠሩ የመንግስት ኃላፊዎች ልዩ ጥበቃ እንደማያደርግ ማስታወቁ የሚታወስ ሲሆን እኚሁ የህዝብ እንደራሴም ሕጉ ተግባራዊ የሚደረግባቸው የመጀሪያው ሳይሆኑ እንደማይቀሩ ተገምቷል።

ተያያዥ ርዕሶች