ሕመምና ረሃብ የጎዳቸው የሱዳን አንበሶች ሁኔታ ቁጣን ቀስቅሷል

የታረዙት የሱዳን አንበሶች ሁኔታ ቁታን ቀስቅሷል Image copyright AFP

በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም በሚገኝ 'ፓርክ' ውስጥ የሚገኙ ረሃብ ያገረጣቸውና የታመሙ አንበሶችን እንታደግ የሚል ጥሪ በማሕበራዊ ድር-አምባዎች ላይ በርትቷል።

ኤኤፍፒ የተሰኘው የዜና ወኪል እንደዘገበው ዕለተ እሁድ ሁኔታው ያሳሰባቸው ሱዳናውያን ወደ ፓርኩ በማቅናት የአንበሶቹን ሁኔታ ጎብኝተው ተመልሰዋል። ይህ የሆነው ደግሞ የከሲታዎቹን አንበሶች ገፅታ የሚያሳይ ፎቶ ድር-አምባዎች ላይ ከተለቀቀ ወዲያ ነው።

ንቅናቄውን ያስተባበረው ኦስማን ሳሌህ "ባየሁት ነገር እጅግ ተደናግጫለሁ፤ አጥንታቸው ገጦ ሳይ ዓይኔን ማመን ነው ያቃተኝ" ሲል ሃዘኑን ገልጿል።

አምስቱ አናብስት በካርቱሙ አል-ቁሬሺ ፓርክ ከከተሙ ብዙ ጊዜ ሆኗቸዋል። ከፍርግርግ ጀርባ የሚገኙት እኒህ አናብስት የምግብና የመድኃኒት እጥረት እጅግ እንዳጎሳቆላቸው ፎቶዎችን ተመልክቶ መረዳት ይቻላል።

የፓርኩ ባለሥልጣናት እና የሕክምና ሰዎች አንበሶቹ ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከነበራቸው ክብደት ሁለት ሶስተኛውን አጥተዋል ይላሉ።

ከኦስማን የትዊተር ጩኸት በኋላ ከአናብስቱ አንዷ በደረሰባት ሕመም ወደ ሕክምና ተቋም መወሰዷ ተነግሯል።

«በፀና የታመመችው አንበሳ ዛሬ ጠዋት ወደ ሶባ ክሊኒክ ለሕክምና እርዳታ መወሰዷን ሰምቻለሁ። እነሱ እየተሻላት ነው ብለው ቢነግሩኝም እውነታውን ማወቅ አይቻልም» ሲል ፅፏል።

ሰዎች ለአናብስቱ የምግብ እርዳታ ማድረግ መጀመራቸውም ተሰምቷል። አናብስቱን ከፓርኩ ለመታደግም የፊርማ ማሰባሰብ መጀመሩ ተሰምቷል።

የካርቱም ከንቲባ ፅ/ቤት የሚያስተዳደረው ፓርክ ከግል ባለሃብቶች እርዳት የሚያገኝ ቢሆንም የምጣኔ ሃብት ውድቀት እና የኑሮ ግሽበት ያደቀቃት ሱዳን አንበሶቿን መመገብ የቻለች አትመስልም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ