ርዕደ መሬት፡ እውን አዲስ አበባ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ ነበር?

አዲስ አበባ Image copyright Getty Images

ሰኞ ጥር 11/2012 ንጋት አካባቢ መሬት ስትነዘር ሰምተናል ያሉ ሰዎች በማሕበራዊ ድር-አምባዎች ያጋጠማቸውን ሲያጋሩ ነበር።

'አፍሪካ ኢንስቲቲዩት' የተባለ አንድ ገፅም ኢትዮጵያ ውስጥ የመሬት መንቀጥቀት ተከስቶ እንደነበር የሚጠቁም አንድ ድረ-ገፅ አያይዞ ትዊተር ላይ ፅፎ ነበር።

እውን አዲስ አበባም ሆነ በኢትዮጵያ ሌሎች ሥፍራዎች የመሬት መንቀጥቀት ተከስቶ ነበር?

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦፊዚክስ፣ ሳይንስና አስትሮኖሚ ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት አታላይ አየለ [ፒኤችዲ] የመሬት መንቀጥቀጥ ተመራማሪ ናቸው።

ተመራማሪው፤ በፉሪ፣ በኢትዮጵያና ኬንያ ድንበር ያሉ ጣቢያዎችን ጨምሮ ከአምስት የተለያዩ ጣቢያዎች በተገኘ መረጃ መሠረት በምሥራቅ ኢትዮጵያ መኢሶ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጥ ተከስቶ እንደነበር አጣርተናል ይላሉ። የአዲስ አበባ ነዋሪዎች የተሰማቸው የመኢሶው ንዝረት ነው ሲሉ ያስረዳሉ።

«መኢሶ አካባቢ በሪክተር ስኬል 5 የሚገመት የመሬት መንቀጥቀጥ ተፈጥሯል። ይህ የሆነው ዛሬ [ጥር 11/2012] 12 ሰዓት አካባቢ ነው። አዲስ አበባ ውስጥም ቢሆን ሰዎች ሊሰማቸው ይችላል። በተለይ ፎቅ ላይ ያሉ ሰዎች የበለጠ ሊሰማቸው ይችላል። በሪክተር ስኬል 5 ማለት እንግዲህ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል አይደለም፤ ነገር ግን ሰዎች ሊሰሙት ይችላሉ።»

በተለይ አዋሽና አሰበ-ተፈሪ አካባቢ የመሬት መንቀጥቀጡ ጎልቶ የተሰማ ሲሆን፤ አዲስ አበባ ደግሞ ለስምጥ ሸለቆ ቅርብ በመሆኗ መሰል ክስተቶች ይሰሟታል።

ከዚህ በፊት መሰል የመሬት መንቀጥቀጦች በስምጥ ሸለቆ አካባቢዎች ተከስተው ንዝረቱ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ሲያስደነግጥ ይህ የመጀመሪያው አይደለም ይላሉ ባለሙያው።

«2009 አንኮበር አካባቢ የተከሰተ የመሬት መንቀጥቀጥ ነበር። ባልሳሳት 4.7 ሪክተር ስኬል አካባቢ ነበር የተመዘገበው። ታኅሣሥ ውስጥ ነበር። የዛኔም አዲስ አበባና ሌሎች አካባቢዎች ንዝረቱ ተሰምቶ ነበር።»

አሁን በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ምናልባት መሬት ላይ ያሉ ቤቶችን ያፈርስ ይሆናል እንጂ ብዙ ጉዳት አያደርስም ይላሉ። የደረሰ ጉዳት እንዳለ ገና አለማረጋገጣቸውንም ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል የመሬት መንቀጥቀጥ ያስተናገደችው 1953 ላይ ሲሆን ካራቆሬ ተበሎ በሚጠራው አካባቢ የተከሰተው መሬት መንቀጥቀጥ በሪክተር ስኬል 6.5 ተመዝግቧል። በወቅቱ በደረሰ አደጋ 30 ሰዎች መሞታቸውም ተዘግቦ ነበር።

ምንም እንኳ አንዳንድ አካባቢዎች በታላቁ ስምጥ ሸለቆ ውስጥ ቢገኙም የመሬት መንቀጥቀጥ ኢትዮጵያን ይህን ያህል የሚያሰጋት አይደለም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ