የወንድ የዘር ፍሬን ልክ እንደ ዓይን፣ ኩላሊት መለገስ ይቻላልን?

የወንድ የዘር ፍሬ Image copyright Getty Images

የወንድ የዘር ፍሬ በልገሳ መልኩ ሰዎች በሕይወት እያሉ ወይም ከሞቱ በኋላ በልገሳ መልኩ የሚሰጡበት የሕግ ማዕቀፍ ሊኖር እንደሚገባ አንድ ጥናት አመለከተ።

ጆርናል ኦፍ ሜዲካል ኤቲክስ በተሰኘ ጆርናል ላይ የታተመው ይህ ሰፊ ትንታኔ እንደሚለው ወንዶች ከሞቱ በኋላም ሆነ በህይወት እያሉ የዘር ፍሬያቸውን ለሚፈልጉት ሰው/ ሴት የመለገስ መብታቸው ሊከበር ይገባል።

በፈረንጆቹ 2017 በአገረ እንግሊዝ 2 ሺ 345 ህጻናት የተወለዱት በልገሳ በተገኘ የወንድ የዘር ፍሬ ነበር።

ነገር ግን በአገሪቱ የተደረገውን ከፍተኛ ቁጥጥር ተከትሎ የወንድ የዘር ፍሬ ለጋሾች ቁጥር በእጅጉ ቀንሶ የለጋሽ ያለህ አስብሏል።

የወንዱን የዘር ፍሬ ከሞተ በኋላ ከፕሮስቴት እጢ ወይም በቀዶ ሕክምና አማካኝነት በኤሌክትሪክ መሰብሰብ ይችላል። ከዚያም ማቀዝቀዣ ውስጥ ይቀመጥና ለአገልግሎት ሲፈለግ ወጥቶ ጥቅም ላይ እንዲውል ይደረጋል።

ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከሞተ ሰው የሚወሰድ የዘር ፍሬ አዲስ ትውልድ በሚገባ መተካት የሚችልና ጤናማ ህጻናትን ማሳደግ የሚችል ነው ተብሏል። ወንዶቹ ከሞቱ እስከ 48 ሰዓታት የሚወሰደው የወንድ ዘር ደግሞ እጅጉን ጤናማ ነውም ተብሏል።

Image copyright Getty Images

በዘርፉ ጥናት ያደረጉ ሃኪሞች የዘር ፍሬ መለገስ ማለት ልክ አይን ወይም ኩላሊት እንደመለገስ ነው ይላሉ።

እናም ከሞራል አንጻር ለጋሾቹ ፈቃደኛ ከሆኑ በጤና ምክንያት ዘራቸውን መተካት ላልቻሉ ወዳጆቻቸው ወይም ራሳቸው በሆነ አጋጣሚ ግብረ ስጋ ግንኙነት ፈጽመው ልጅ የመውለድ ተስፋቸው የተሟጠጠ ከሆነ ለሚወዷቸው ሰዎች ልገሳ ቢያደርጉላቸው ከዚህ በላይ አስፈላጊ ነገር ሊኖር አይችልም ብለዋል።

ቢሆንም ግን የለጋሽ ቤተሰቦች ፈቃደኝነት እና የለጋሹን ማንነት ሚስጥራዊ አድርጎ ከመያዝ ጋር የሚያያዙ በርካታ ጥያቄዎች ሊነሱ እንደሚችሉም ባለሞያዎቹ ስጋተቸውን ያስቀምጣሉ።

በ2014 በእንግሊዝ በርሚንግሃም ከተማ በ77 ሺህ ፓውንድ የመንግሥት ድጋፍ "ብሔራዊ የወንድ ዘር ባንክ" ተቋቁሞ ነበር።

ከሁለት አመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ ግን ባንኩ በሮቹን ቆላልፎ ለጋሽ መመልመሉን አቁሟል። ባንኩ ከተከፈተ በኋላ 9 ፈቃደኛ የዘር ፍሬ ለጋሾችን ነበር ያገኘው። እንዲያውም አንደኛው ትንሽ ቆይቶ ሃሳቤን ቀይሬያለሁ በማለት ፊርማውን አንስቷል።

በፈረንጆቹ 2005 የተረቀቀው የእንግሊዝ የወንድ ዘር ፍሬ ልገሳ ሕግ ከለጋሾች በተገኘ የዘር ፍሬ የተወለደ ልጅ አባቱን ወይም የአባቱን ቤተሰብ ማናገር የሚችለው 18 ዓሜት ከሞላው በኋላ ነው ይላል።

ከሕግ አንጻር እንዴት ይታያል?

በ1997 አንዲት ሴት ከሞተ ባሏ የዘር ፍሬ ለመውሰድ ባደረገችው ክርክር አሸንፋለች።

ሰውየው ከባለቤቱ ዳያን ጋር ቤተሰብ ለመጀመር ከሞከረ ከሁለት ወር በኋላ በደም የካንሰር በሽታ ይይዛል።

በዚህም ኮማ ውስጥ ገብቶ የዘር ፍሬውን ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ሳይገልጽላት በድንገት ይሞታል። ነገር ግን ቀደም ብሎ በሚስት ጠያቂነት ከመሞቱ በፊት ናሙና ተወስዶ ነበር።

ይህም ሆኖ ግን በ1990 የተረቀቀው ሕግ ባሏ ሳይፈርምላት በመሞቱ የዘር ፍሬውን እንዳትጠቀም ከለከላት።

ክርክሯን የቀጠለችው ሴት በይግባኝ የባሏን ዘር ፍሬ እንግሊዝ ውስጥ መጠቀም ባትችልም በአውሮፓ ሕብረት አባል አገራት ውስጥ መጠቀም እንደምትችል ተበይኖላታል።

ከዚያም በኋላ ማቀዝቀዣ ውስጥ የተቀመጠውን የዘር ፍረውን በመጠቀም አርግዛ 'ሶን ጃኦል' የተባለ ልጅ ወልዳ ለመሳም በቅታለች። በዓመቱም የልጁን አባት ሕጋዊነት በሕግ እንዲታወቅ ለሁለተኛ ጊዜ ተከራክራ አሸንፋለች።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ