አሜሪካ ሕዝብና ቤት ቆጠራዋን ከ600 ሰዎች በታች ከሚኖሩባት ግዛት ጀምራለች

590 ሰዎች ብቻ የሚኖሩባት የአሜሪካ ክፍለ ግዛት Image copyright CENSUS BUREAU

አሜሪካ፤ የፈረንጆቹ 2020 ሕዝብና ቤት ቆጠራ ቶስኩክ ቤይ በተባለ ገጠራማ የድንበር ክፍለ-ግዛት ጀምራለች።

አሜሪካ ሕዝብ የምትቆጥረው በየ10 ዓመቱ ነው። ብዙ ጊዜ ቆጠራው የሚጀምረው ከመጋቢት ወር አጋማሽ ጀምሮ ቢሆንም ቆጣሪዎች ወደ አላስካ ግዛት በማቅናት ሰው ይኖር ይሆን የሚለውን ያጣራሉ።

ቆጣሪዎች ከይፋዊው የቆጠራ ቀን አስቀድመው ወደ አላስካ የሚያቀኑበት ምክንያት ቅዝቃዜው ከጠነከረ በሚል ነው።

የሕዝብና ቤት ቆጠራ ኃላፊው ስቲቨን ዴሊንግሃም ወደ ግዛቲቱ አቅንተው የ90 ዓመቷን የጎሣ መሪ ሊዚ ኔጉርያርን በመመዝገብ ቆጠራውን አንድ ብለዋል።

የአላስካ ግዛት ሰዎች ተበታትነው የሚኖሩ ለቆጠራ እጅግ ከባድ ነው። በረዶው እግር ከመዋጡ በፊት የሚጀምሩትም ለዚህ ነው። ቆጣሪዎች በውሻ የሚጎተት ተንሸራታች ጋሪ ይጠቀማሉ።

ቶስኩክ ቤይ የተባለው የአላስካ ክፍለ-ግዛት ደግሞ ከግዛቲቱ ማዕከል 800 ሜትር ርቆ የሚገኝ ነው። የዛሬ 10 ዓመት በተደረገው ቆጠራ የነዋሪዎች ቁጥር 590 ነበር። አሁን ምናልባት 661 ሊሆን ይችላል የሚል ግምት አለ።

Image copyright CENSUS BUREAU

ቶስኩክ ቤይ የሚኖሩ ጎሣዎች ዩፒክ ይባላሉ። ወ/ሮ ሊዚ ኔጉርያርን እና ሌሎች የጎሣ አባላት ዩግቱን በተሰኘ ቋንቋ ይግባባሉ።

20 የተለያዩ ቋንቋዎች በሚነገሩባት አላስካ የሕዝብና ቤት ቆጠራ ሰዎች አስተርጓሚ ይዘው ነበር የሚንቀሳቀሱት። ዘንድሮ ግን የመመዝገቢያ ወረቀቶች ዩፒክን በተለያዩ ቋንቋዎች እንዲታተሙ ተደርገዋል።

ሕዝብና ቤት ሊቆጥሩ ቶስኩክ ቤይ የከተሙት የቆጠራ ሰዎች ሰውን እና እንስሳቱን ከመዘገቡ በኋላ የቀረበላቸውን ምግብና መጠጥ እያጣጣሙ በጎሣው ሰዎች ዳንስ ሲዝናኑ አምሽተዋል።

የቆጠራ መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ ይህን ማድረግ ያስፈለገን በሌሎች ግዛቶች የሚኖሩ አሜሪካውያን ስለ አላስካ እንዲያውቁ ስለምንፈልግ ነው ይላሉ።

የሕዝብ ምዝገባውን በረዶ ውስጥ በሚኖሩ ሰዎች የጀመረው የቆጠራ መሥሪያ ቤት መዝጋቢዎችን በመቅጠር ላይ ይገኛል። ከ300 ሺህ እስከ 500 ሺህ ሰዎች ለዚህ ሥራ ሊቀጠሩ ይችላሉ ተብሎ ይገመታል።

ሕዝብ ቆጣሪ ሆነው ለመመዝገብ እስካሁን 1.8 ሚሊዮን ሰዎች የሥራ ማመልከቻ ማስገባታቸው ታውቋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ