የጓንታናሞ ታሣሪዎች ማሰቃያን የፈጠሩት ፍርድ ቤት ቀረቡ

የጓንታናሞ ቤይ እስር ቤት ታሳሪዎች Image copyright Getty Images

በጓንታናሞ ቤይ እሥር ቤት ውስጥ የሚፈፀምውን የስቃይ ዓይነትን የፈጠረው አሜሪካዊው የሥነ-ልቦና ባለሙያ በወታደራዊ የፍርድ ሂደት ላይ ቀርቦ ምስክርነት ሰጠ።

ጄምስ ሚቼል የተሰኘው ግለሰብ ምስክርነት ለመስጠት የወሰንኩት የ9/11 አደጋ ሰለባ ቤሰተቦች በፍርድ ሂደቱ ላይ ስለተገኙ ነው ብሏል።

ዶክተር ሚቼልና የሥራ አጋሩ ብሩስ ጄሰን አጨቃጫቂው የእሥረኞቹ ማሰቃያ መንገዶችን ፈጥረዋል ይባልላቸዋል። ከማሰቃያ መንገዶቹ መካከል 'ዎተርቦርዲንግ' የተሰኘው እሥረኖችን በጨርቅ ሸፍኖ በውሃ ማፈን ይገኝበታል።

ጓንታናሞ ከሚገኙ እሥረኞች መካከል አምስቱ ከ9/11 አደጋ ጋር በተያያዘ ለፍርድ ይቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል። ኻሊድ ሼክ ሞሐመድ በፈረንጆቹ 9/11/2001 የደረሰውን አደጋ እንዳቀነባበሩ ከሚገቱት መካከል ቁንጮው ነው።

ኻሊድ ኩባ በሚገኘው የጓንታናሞ ቤይ ቆይታው እጅግ ተሰቃይቷል ተብሎ ይጠረጠራል። የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤ ፋይሎች እንደሚያሳዩት ግለሰቡ 183 ጊዜ በጨርቅ ተሸፍኖ በውሃ እንዲታፈን ተደርጓል።

የተቀሩት አራቱ - ዋሊድ ቢን አታሽ፣ ራምዚ ቢን አል-ሺብህ፣ አማር አል-ባሉቺ እና ሙስጠፋ አል-ሃውሳዊ ወደ ጓንታናሞ ከመምጣታቸው በፊት በሲአይኤ ሰዎች ብዙ ስቃይ እንደደረሰባቸው ይገመታል።

የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ሲአይኤ መረጃ ለማግኘት ሲል የተጠቀማቸውን የስቃይ ዓይነቶች የሚያሳዩ መረጃዎች ተሸሸገውብናል ሲሉ ይወቅሳሉ።

የ9/11 አደጋ ሰለባ ቤተሰቦች የፍርድ ሂደቱን ለመከታተል የተገኙ ቢሆንም ከተጠርጣሪዎቹ ጋር እንዳይተያዩ በተከለለ ክፍል ውስጥ ሆነው ነው ፍርዱን የሚከታተሉት።

ዶ/ር ሚቼል ለ9/11 አደጋ ሰለባ ቤተሰቦች ክብር ሲሉ እንጂ ለተጠርጣሪዎቹ ሲሉ እንዳልቀረቡ ለፍርድ ቤቱ መናገራቸው ተዘግቧል።

ይህ ከዋናው የፍርድ ሂደት ቀድሞ የሚካሄድ ችሎት ለሁለት ሳምንታት እንደሚቆይና ዋናው የፍርድ ሂደት የዛሬ ዓመት በፈረንጆቹ 2021 እንደሚካሄድ ተነግሯል።

አምስቱም ተጠርጣሪዎች ሽብር እና ግድያን [3ሺህ ሰዎች] ጨምሮ በተለያዩ የጦር ወንጀሎች የተጠረጠሩ ሲሆን ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙ የሞት ቅጣት ይጠብቃቸዋል።

'ዎተርቦርዲንግ' የተሰኘው የማሰቃያ ዘዴ እሥረኞች እጅና እግራቸው ተጠፍሮ ከተንጋለሉ በኋላ ውሃ በአፍን አፍንጫቸው በመልቀቅ መረጃ ለማውጣት የሚከወን ነው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ