ሳዑዲ አራቢያ የዓለማችን ቱጃሩን ሰው ስልክ ጠልፋለች የተባለውን አስተባበለች

ሳዑዲ አራቢያ ጄፍ ቤዞስን ሰልለሻል የተባልኩት በሃሰት ነው እያለች ነው Image copyright Getty Images

የሳዑዲ አራቢያው ልዑል አልጋ ወራሽ የዓለማችን ሃብታሙን ሰው ስልክ ሰልለዋል የሚል ጠንካራ ክስ ቀረቦባቸዋል።

ሳዑዲ አራቢያ ግን ወቀሳው ሃሰት ነው፤ ልዑል አልጋ ወራሼ እንዲህ ዓይነት ተግባር አልፈፀሙም ትላለች። ዘገባዎች ግን ልዑል አልጋ ወራሹ ይጠቀሙበት በነበረ ቁጥር የተላከ መልዕክት የሃብታሙን ሰው ስልክ መረጃ ለመበርበር ሙከራ አድርጓል እያሉ ነው።

ዩናትድ ስቴትስ የሚገኘው የሳዑዲ ኤምባሲ እየወጡ ያሉት ዜናዎች ግራ አጋቢ ናቸው፤ ሊመረመሩ ይገባል የሚል መግለጫ አውጥቷል።

የዓለማችን ሃብታሙ ሰው ስልክ ከጋዜጠኛ ጃማል ካሾግጂ ግድያ ጋር ግንኙነት አለው የሚሉ ዘገባዎችም ወጥተው ነበር። ቱጃሩ ጄፍ ቤዞስ፤ ጃማል ካሾግጂ ይሠራበት የነበረው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ባለቤት ናቸው። ከጋዜጠኛው ግድያ ጋር በተያያዘ ዋሽንግተን ፖስት የሳዑዲ መንግሥትን እና ልዑል አልጋ ወራሹን የሚተቹ በርካታ ጽሑፎችን አስነብቧል።

የእንግሊዙ 'ጋርድያን' ጋዜጣ እንደዘገበው የጄፍ ቤዞስ ስልክ የተጠለፈው ቱጃሩ ከሳዑዲው ልዑል የዋትስአፕ መልዕክት ከደረሳቸው በኋላ ነው። ፋይናንሻል ታይምስ የተባለው ጋዜጣ ደግሞ የቢሊዬነሩ ስልክ ከዋትስአፑ መልዕክት በኋላ መረጃ ማሾለክ መጀመሩን ዘግቧል።

የዋሽንግተኑ የሪያድ ኤምባሲ በትዊተር ገፁ የተባለውን ሁሉ ሃሰት ናቸው ካለ በኋላ ዘገባዎቹ እንዲጣሩ እናደርጋለን ብሏል።

የጄፍ ቤዞስ ግዙፍ ድርጅት የሆነው አማዞን ኪቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ እሰካሁን ምላሽ አልሰጠም።

ናሽናል ኢንኳየረር የተሰኘ አንድ የበይነ-መረብ ጋዜጣ ስለ ጄፍ ቤዞስ መረጃ ካወጣ በኋላ ነው የልዑል አልጋ ወራሹ ጣልቃ ገብነት መሰማት የጀመረው። ባለፈው ዓመት ጄፍ ቤዞስ የበይነ-መረቡን ጋዜጣ ግላዊ መረጃዬን አውጥቷክ ሲል መክሰሳቸው አይዘነጋም። ከዘገባው በኋላ ነው ቤዞስና ባለቤቱ ማኬንዚ መለያየታቸው የተሰማው።

ሳዑዲ የቤዞስን ስልክ ጠልፋለች ተብላ ስትወቀስ ይህ የመጀመሪያዋ አይደለም። ቱጃሩ ቤዞስ የቀጠረው አንድ መርማሪ ሪያድ ስልኩን ለመጥለፍ ሞከራለች የሚል መረጃ ባለፈው መጋቢት አውጥቶ ነበር።

የግል መርማሪው ሳዑዲ የቤዞስን ስልክ የጠለፈችው ከጋዜጠኛ ጃማል ካሾግጂ ግድያ ጋር በተያያዘ ሳይሆን አይቀርም የሚል እምነት አለው።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ