ሜጋንና ሃሪ ያለፈቃድ ፎቶ የምታነሱን ሰዎች ወዮላችሁ የሚል ማስጠንቀቂያ አስተላልፈዋል

ሜጋንና ሃሪ 'ተደብቃችሁ ፎቶ የምታነሱን ወዮላችሁ' ብለዋል Image copyright EPA

'የሱሴክስ ዱክና ዳቸስ' የተሰኘ ንጉሣዊ ስም ያላቸው ልዑል ሃሪና ባለቤቱ ሜጋን፤ በድብቅ ፎቶ የሚያነሷቸውን ሰዎች አስጠንቅቀዋል።

ሜጋን፤ ካናዳ ውስጥ ልጇኝ ከፊት አዝላ ሁለት ውሾች በገመድ እያንሸራሸረች የምትታይበት ፎቶ ሾልኮ ከወጣ በኋላ ነው ጥንዶቹ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክታቸውን ያሰሙት።

መኖሪያቸውን በካናዳዋ የቫንኮቨር ደሴት ያደረጉት ሜጋንና ሃሪ ፎቶግራፈሮቹ ነፃነታችንን እየተጋፉ ነው ሲሉ ወቅሰዋል።

የሜጋን ፎቶ የተነሳው ሲከታተሏት በነበሩና በዛፍ ተከልለው ባነሷት የካሜራ ሰዎች ነው ተብሏል። ጥንዶቹ ፎቶ አንሺዎቹን ሊከሱ እንደሚችሉም አሳውቀዋል።

የጥንዶቹ ጠበቆች 'ፓፓራዚ' የሚባሉት ድብቅ ጋዜጠኞች ረዥም ርቀት ተመዝግዛጊ ሌንስ በመጠቀም ጥንዶቹ ቤት ውስጥ የሚያከናውኑትን ተግባር ለማንሳት የሚጥሩ ብዙዎች ናቸው ሲሉ ወቅሰዋል።

በካናዳዋ ብሪቲሽ ኮሎምቢያ ግዛት ሕግ መሠረት ሜጋን የግል ነፃነቴ ተገፍቷል ካለችና ከተረጋገጠ መክሰስ ትችላለች። ነገር ግን የፕረስ ነፃነትም ከግምት ውስጥ ይገባል።

ሜጋንና ሃሪ ከእንግሊዝ ንጉሣዊ ቤተሰብ ራቅ ብለን መኖር እንፈልጋለን ማለታቸውን ተከትሎ ዩናይትድ ኪንግደም በጥንዶቹ ዜና ተጠምዳ ነበር። በስተመጨረሻም የንግስቲቱን ይሁንታ ካገኙ በኋላ መኖሪያቸውን ካናዳ አድርገዋል።

Image copyright Getty Images

ባለፈው ማክሰኞ ሜጋን የስምንት ወር ልጇ አርቺን በደረቷ አዝላ ከሁለት ውሾች ጋር ቫንኮቨር ደሴት የሚገኝ ፓርክ ውስጥ ስትንሸራሸር በካሜራ ዕይታ ሥር ቀርታለች።

ባለቤቷ ሃሪ በዩኬ-አፍረቃ መዋዕለ ንዋይ መድረክ ላይ ለመሳተፍ እንግሊዝ ቆይቶ ዕለተ ማክሰኞ ነው ካናዳ የገባው።

ሜጋንና ልዑል ሃሪ ከመጋቢት ወር ጀምሮ ንጉሣዊ ካባቸውንና መጠሪያቸውን አውልቀው ጥለው እንደ ማንኛውም ሰው ወ/ሮ እና አቶ መባል ይጀምራሉ ተብሏል።

የልዑል ሃሪ እናት የሆነችው ልዕልት ዳያና በሞተርብስክሌት ሲከታተሏት ከነበሩ 'ፓፓራዚዎች' ስታመልጥ ሳለች ባጋጠማት የመኪና አደጋ ህይወቷ ማለፉ አይዘነጋም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ