ቻይና ውስጥ የተከሰተው ተላላፊና ገዳይ ቫይረስ አሜሪካ ደረሰ

ቻይና ውስጥ የተገኘው ቫይረስ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ መሆኑ ተረጋገጠ Image copyright KEVIN FRAYER

ቻይና በግዛቷ የተገኘው ቫይረስ የበለጠ ሊስፋፋ እንደሚችል ባለስልጣናቷ እያስጠነቀቁ ነው።

በቅርቡ በቻይና ተከስቶ 9 ሰዎችን ለህልፈት የዳረገው ቫይረስ አሁን ካለበት በላይ ሊስፋፋ እንደሚችል የአገሪቱ ባለስልጣናት ማረጋገጣቸውን ይፋ አድርገዋል።

በውሃን ግዛት እስካሁን በተደረገው ምርመራ 440 ሰዎች በበሽታው መያዛቸው ታውቋል።

አሁን በሚወጡ መረጃዎች መሰረት ቫይረሱ በበርካታ የቻይና ግዛቶች ተስፋፍቷል። ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተደረገ መስፋፋት ስለሆነ ቀጣይ ብዙ ግዛቶችን በአጭር ጊዜ ያዳርሳል ተብሎ በትልቁ ስጋትን በመፍጠሩ ነው የባለስልጣናቱ ማስጠንቀቂያ ያስፈለገው።

ከቻይና ውጭም በተለያዩ የዓለም አገራት ቫይረሱ ተሻግሮ መገኘቱ ደግሞ አሳሳቢነቱን ጨምሮታል። ከነዚህ አገራት መካከል ደቡብ ኮሪያና ታይላንድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ናቸው። የተደረገው ምርመራ ቻይና ውሃን ግዛት የተነሳው ቫይረስ ከእሲያ አህጉር ወጥቶ ሌላ አህጉር ገብቷል። ቫይረሱ አሜሪካ መግባቱ ተረጋግጧል።

ባለስልጣናትም አሁን ቫይረሱ በከፍተኛ ደረጃ እየተዛመተ ያለበት ወቅት መሆኑን አምነው ቻይና ከፍተኛ ክትትል ማድረግ እንዳለበት አስጠንቅቀዋል።

ትናንት በተደረገው ምርመር መሰረት በቫይረሱ ዙሪያ አንድ ተጨማሪ ግኝት ተገኝቷል። ቫይረሱ ከሰው ወደ ሰው እንደሚተላለፍ ተረጋግጧል። ይህ ደግሞ ሁኔታውን እጅግ ውስብስብና አደገኛ ያደርገዋል ተብሎ ተሰግቷል።

'የአደጋው ፍጠነት'

ቫይረሱ ከተከሰተ በኋላ በመንግሥት ደረጃ ትናንት በተሰጠው ይፋዊ መግለጫ፤ የቻይና ምክትል የጤና ሚንስትር እንዳረጋገጡት የቫይረሱ ዋነኛ መተላለፊያ በመተንፈሻ አካላት አማካኝነት ነው ብለዋል።

ቫይረሱ ከየት እንደመጣ ለማወቅ የሚደረገው ጥረት እስካሁን ምንም ውጤት አላስገኘም።

በተለይ ሰሞኑን የቻይና አዲስ ዓመት የሚከበርበት ወቅት መሆኑና በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች ወደ ውጭ አገራት የሚጓዙ በመሆናቸው የቫይረሱን ስርጭት ያፈጥነዋል በማለት ባለስልጣናት ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል።

የአዲስ ዓመት በዓሉ በሽታውን ማስፋፋት ብቻ ሳይሆን ለመቆጣጠር የሚደረገውን ሂደት አስቸጋሪ እንደሚያደርግም ምክትል ሚንስትሩ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም በሽታውን ለመቆጣጠር ሲባል ጠንከር ያሉ ርምጃዎች ሊወሰዱ ይችላሉ ተብሏል።

በውሃን ግዛት ሰዎች እንዳይሰሰባሰቡ ማስጠንቀቂያ የተሰጠ ሲሆን የዶሮና ሌሎች የዱር እንስሳት ግብይትም ለጊዜው ታግዷል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ