አሠልጣኝ አብርሃም መብራህቱ፡ "የመጣውን በጸጋ መቀበልና መዘጋጀት ነው"

የእግር ኳስ ደጋፊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 2022 የሚካሄደው የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የምድብ ድልድል ተጋጣሚዎች ታውቀዋል። በዚህም መሰረት ኢትዮጵያ በምድብ 7 ከጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምባብዌ ጋር ተደልድላለች።

የምድብ ድልድሉ በግብጿ ዋና ከተማ ካይሮ ይፋ የተደረገ ሲሆን የየምድቦቹ አሸናፊዎች በዕጣ ድልድል እርስ በርስ ጨዋታ ያደርጋሉ። የደርሶ መልስ ጨዋታውን ማሸነፍ የቻሉ 5 ሃገራት በኳታሩ የዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክለው ይጫወታሉ።

ዋልያዎቹ ባሳለፍነው መስከረም ወር ላይ በባህር ዳር ስታዲየም ከሌሴቶ አቻቸው ጋር ያለምንም ግብ ቢለያዩም የመልስ ጨዋታዋን በሌሴቶ አድርገው አንድ አቻ መለያየታቸው ይታወሳል።

ከሜዳ ውጭ ባገባ በሚለው ህግ መሰረትም ኢትዮጵያ ወደቀጣዩ ዙር በማለፍ የምድብ ድልድል ውስጥ መግባቷን አረጋግጣ ነበር።

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ የሆኑት አብራሃም መብራህቱ፤ ቡድኑ ያለበትን ደረጃ ስመለከትና ተጋጣሚዎቻችንን ስመለከት ቀለል ያሉ ሀገራት ቢደርሱን ብዬ አስቤያለው ይላሉ።

''ቀደም ሲል ለዓለም ዋንጫ በማለፍ ታሪክ ውስጥ ተደጋጋሚ ታሪኮችን ያስመዘገቡ ሀገራት ባይደርሱን ብለህ ታስባለህ፤ ነገር ግን የምድብ ድልድሉ በዕጣ የሚወጣና ከሰዎች ንክኪ ውጪ ስለሆነ የመጣውን በጸጋ መቀበልና መዘጋጀት ነው የሚጠቅመው'' ብለዋል።

እንደ ጋና እና ደቡብ አፍሪካን የመሰሉ በዓለም ዋንጫ ጥሩ የሚባል ልምድ ካላቸው ሀገራት ጋር የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እንደሚመደብ ባያስቡም እንደ አሰልጣኝ ግን ለጥሩውም ለመጥፎውም ነገር ተዘጋጀውተው እንደነበር አሰልጣኙ አክለዋል።

''በተደጋጋሚ የዓለም ዋንጫን ከተሳተፈችው ጋና እና በአዘጋጅነት እንኳን ቢሆንም የዓለም ዋንጫ ልምድ ካላት ደቡብ አፍሪካ ጋር መመደባችን ጨዋታዎቹን ትንሽ ፈታኝ ያደርጋቸዋል። ያም ቢሆን ግን ውድድር ውስጥ እስከገባን ድረስ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እና ከምድባችን አንደኛ ሆኖ ለመጨረስ ምድቡን የሚመጥን ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል ብዬ አስባለሁ።''

''የምድብ ድልድሉ ይፋ ከተደረገ በኋላ በርካታ መገናኛ ብዙሀን እድለኞች እንዳልሆንንና ከባድ ምድብ ውስጥ እንደገባን ሲዘግቡ ሰምቻለው፤ እኔ ግን እንደዛ አላስብም። የትኛውንም ምድብ መፍራት የለብንም፤ ከፈራን ደግሞ ከነጭራሹ ባንገባባት ነው የሚሻለው። ስለዚህ በልበ ሙሉነት ውድድሩን መጀመር ይኖርብናል።''

አሰልጣኙ አክለውም ''በአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ኮትዲቯርን በባህርዳር ዓለማቀፍ ስቴዲየም ማሸነፋችን እንደዚህ አይነት ከባድ ቡድኖችን መቋቋም እንደምንችል ማሳያ ሊሆን ይችላል። ይህንን እንደ ሞራል ስንቅ ተጠቅመን በይቻላል መንፈስ መግባት ይኖርብናል'' ብለዋል።

''በተጨማሪነትም እነዚህን ሀገራት አሸንፎ ወደቀጣዩ ዙር ለማለፍ ለኮትዲቯር ካደረግነው ዝግጅት የተሻለ ዝግጅት ማድረግ ይኖርብናል። ሁሉም ባለድርሸ አካላት ሊረባረቡ ይገባል፤ ምድቡን የሚመጥን በቂ ዝግጅትና የአቋም መለኪያ ማድረግ ይኖርብናል።''

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከዋናው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ጋር ለአስር ዓመታት የተጫወተው አዳነ ግርማ በበኩሉ '' የምድብ ድልድሉን ወረቀት ላይ ስታየው ከባድ ነው የሚመስለው። ነገር ግን በቅርቡ እንኳን ሳይታሰብ ኮትዲቯርን ማሸነፋችን ቡድኑ ምን ያክል ጠንካራ እንደሆነ ማሳያ ነው፤ ሊታለፍ ይችላል'' ይላል።

በአዳነ ግምት በሜዳ ላይ ከደጋፊ ጋር የሚደረጉ ጨዋታዎች እጅግ ወሳኝ ናቸው። እሱ እንደሚለው ዋልያዎቹ በሜዳቸው የሚያደርጓቸው ጨዋታዎችን በጥንቃቄና ግብ ባለማስተናገድ መጨረስ አለባቸው።

ወደተቃራኒ ቡድን ሀገራት በሚሄዱ ጊዜ ደግሞ በተቻለ መጠን ነጥብ ይዞ ለመውጣት መሞከር አለባቸው፤ ቡድኑም ሕብረት ሊኖረው ይገባል ብሏል።

ከምድብ ተጋጣሚዎች ጥሩ የሆነ ዓለም አቀፍ ልምድና ብቃት ጋር በማነጻጸር የዋልያዎቹ ወቅታዊ አቋም ምን ይመስላል? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ዋና አሰልጣኙ፤ ''እንግዲህ የወቅቱ አቋም መለኪያ ሊሆን የሚችለው የፊፋ ወርሃዊ ደረጃ ነው። በዚህም መሰረት በተለይ ከሁለቱ ሀገራት ጋር ያለን ልዩነት በጣም የሰፋ ነው፤ በሌላ በኩል ከኮትዲቯር ያደረግነውን ጨዋታ ስንመለከትና እነሱ ያደረጓቸውን የመጨረሻ ጨዋታዎች ስንመለከት ጥሩ የሚባል አቋም ላይ እንዳለን ይሰማኛል'' የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

በአሁኑ ሰአት በፕሪምየር ሊጉ እየተሳተፈ በሚገኘው ወልቂጤ ከተማ በተጫዋችነትና በምክትል አሰልጣኝነት እየሰራ የሚገኘው አዳነ ግርማ ''የአሁኑ አሰልጣኝ በጣም ጥሩ ቡድን ሰርተዋል፤ ነገር ግን ተጫዋቾች ቶሎ ቶሎ ሲቀያየሩ አስተውላለሁ። አሰልጣኙና የስልጠና ቡድኑ ባጠቃላይ ይህንን ነገር ቢያስተካክሉ ቡድኑ ይበልጥ የመተዋወቅና በደንብ የተዋሀደ እንዲሆን ይረዳዋል ብዬ አስባለሁ'' ይላል።

አሰልጣኙ በበኩላቸው ''የሀገራችን ሊግ ወጥ ካለመሆን ጋር ተያይዞ ተጫዋቾች አቋማቸው ሊዋዥቅ ይችላል፤ እኔ ደግሞ ወቅታዊ አቋሙ ጥሩ ያልሆነ ተጫዋች ለብሄራዊ ቡድኑ ልጠራ አልችልም። ነገር ግን ኮትድቯርን ያሸነፈውን ቡድን በተቻለ መጠን ጠብቆ ለማስቆየት ግን ጥረት እናደርጋለን'' ብለዋል።