የዚምባብዌው ቢሊየነር ለዶክተሮች ደሞዝ ሊከፍሉ ነው

ስትራይቭ ማሲዪዋ Image copyright Getty Images

የዚምባብዌ ጀማሪ ዶክተሮች ከአራት ወራት የስራ ማቆም አድማ በኋላ ወደስራቸው ለመመለስ ተስማምተዋል። የመመለሳቸው ምክንያት ደግሞ በቴሌኮም ዘርፍ ላይ የተሰማራ አንድ ዚምባብዌያዊ ቢሊየነር ደሞዝ እንደሚከፍላቸው በመግለጹ ነው።

የዶክተሮቹ የስራ ማቆም አድማ በሀገሪቱ ታሪክ እጅግ ረጅሙ የተባለ ሲሆን የዚምባብዌን የጤና ዘርፍ በእጅጉ አሽመድምዶታል ተብሏል።

መቀመጫቸውን እንግሊዝ ያደረጉት ቢሊየነሩ ስትራይቭ ማሲዪዋ ለእያንዳንዱ ዶክተር በአበል መልክ በየወሩ 300 ዶላር ለመክፈልና በተጨማሪ ደግሞ የመጓጓዣ ወጪያቸውንም ለመሸፈን ቃል ገብተዋል።

ወገኖቹን ለመርዳት ጠመኔ የጨበጠው ኢትዮጵያዊው ሐኪም

ከአንደኛ ክፍል ዲግሪ እስኪጭኑ ከልጃቸው ጋር የተማሩት አባት

በስራ ማቆም አድማው ላይ የተሳተፉት አብዛኛዎቹ ዶክተሮች በወር ከ 100 ዶላር ያነሰ የሚከፈላቸው ሲሆን የቢሊየነሩ ውሳኔ በርካቶችን የሚያስደስት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ቢሊየነሩ ስትራይቭ ማሲዪዋ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት የዶክተሮቹን ወጪ የሚሸፍኑ ሲሆን ከዚህ በኋላ ስለሚፈጠረው ነገር ግን እስካሁን የታወቀ ነገር የለም ተብሏል።

''በዚምባብዌ ዶክተሮቹ የስራ ማቆም አድማ ማድረግ ከጀመሩበት ቀን አንስቶ በህክምና እጥረት ምክንያት ዜጎች ሕይወታቸው አልፏል'' ሲል የዚምባብዌ ከፍተኛ ዶክተሮች ማህበር አስታውቋል።

የስራ ማቆም አድማውንም ''የዘር ማጥፋት ነው'' ሲል ገልጾታል።

ወላጆች ለልጆቻቸው የሚመኟቸው ኢትዮጵያዊ መምህር

ጀማሪ ዶክተሮቹ ስራቸውን ያቆሙት እጅግ ዝቅተኛ ነው ባሉት ወርሀዊ ደመወዝ ምክንያት ነው። በአሁኑ ሰአት ሀገሪቱ የገባችበት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ደግሞ የቢሊየነሩ ድጎማ ሲቆም ምን ይፈጠር ይሆን የሚለውን ጥያቄ እጅግ አስፈሪ አድርጎታል።

ከዚሁ ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ጋር በተያያዘ የሀገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዚምባብዌያውያን ያለባቸው እዳ በዚምባብዌ ዶላር ብቻ እንደዲከፈል ወስኗል። በዚህም መሰረት አንድ የዚምባብዌ ዶላር ከአንድ የአሜሪካ ዶላር ጋር እኩል ዋጋ ይኖረዋል ማለት ነው።

በሺዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ዶላሮችን ከባንክ የተበደሩ የዚምባብዌ ዜጎችም ዕዳቸውን ሲከፍሉ በዚምባብዌ ዶላር ይከፍላሉ ተብሏል።

ተያያዥ ርዕሶች